የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ሊቀ-መንበር ከሥራ አስፈጻሚ አባላት እየተወዛገቡ ነው
ቅዳሜ፣ መጋቢት 14 2016የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ታስሮ የሚገኙ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ እና በፓርቲው ላይ እየደረሱ ያሉ ጫናዎች በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲፈቱለት ጠየቀ። የድርጅቱ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መርቀኒ አዙበር ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መቅረቡን ጠቅሰው ከ3 ሺሕ በላይ ደጋፊዎችና አባላት ፒቲሽን ተፈራርመው ለቦርዱ ማስገባታቸውን ጠቁመዋል።
በአመራሮች መካከል ሐምሌ 2015 ዓ.ም በተፈጠረ አለመግባባት ፓርቲው ለሁለት መሰጠንቁን አቶ መርቀኒ አዙበር ተናግረዋል። ችግሩ የተፈጠረው በወቅቱ የድርጅቱ ሊቀ-መንበር አቶ አብዱልሰላም ሸንግል ከመንግስት ጋር የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያላመነበትን ስምምነት በመፈራረማቸው እንደሆነም ገልጸዋል። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ አብዱልሰላም ሸንግል በበኩላቸው የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለዋል።
የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ አመራሮች ውዝግብ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ አምስት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከነሐሴ 2015 አንስቶ በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መርቀኒ አዙበር ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አዲስ ሊቀ-መንበር ለመምረጥ እንዲያስችለው በክልሉ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የታሰሩ የፓርቲው አመራሮች እንዲፈቱ የሚል ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።
በድርጅቱ ሊቀ-መንበር “የፓርቲውን ገንዘብ በመመዝበራቸው በምርጫ ቦርድ ጉዳዩ ተጣርቶ መፍትሄ እንዲበጅ” የሚል ጥያቄ መቅረቡን አክልዋል። አሁንም ባለው ሁኔታ ፓርቲው በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በክልሉ ይካሄዳል በተባለው ምርጫ ላይ መሳተፍ እንደማይችል ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም እና ኢንቨስትመንት
የድርጅቱ ሊቀ-መንበር የሆኑት አቶ አብዱልሰላም ሸንግል በሰጡን አስተያየት በድርጅታቸው አመራሮች የቀረበባቸውን ክስ “የውሸት ውንጀላ” ሲሉ አጣጥለዋል። አቶ አብዱልሰላም እንደሚሉት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በአመራሮች መካከል የነበሩ ቅሬታዎች ተፈተዋል። “የፓርቲውን ገንዘብ መዝብረዋል” ተብለው ለቀረበው ቅሬታም “ፓርቲውን ለማፍረስ አልሞ የሚንቃሰቀሱ ጥቂት” ያሏቸው ቡድኖች “የፓርቲውን አባላት ለማሳሳት ያሰራጩት የውሸት መረጃ” መሆኑን ጠቅሶ በቅርቡ የኦዲት መስሪያ ቤት ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የፓርቲውን ቅሬታ መቀበሉን ገልጾ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችል አስታውቋል። ታሰሩ የተባሉ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ አመራሮችን ጉዳይ አስመልክቶ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ከዚህ ቀደም በሰጡን ማብራሪያ ግለሰቦቹ የታሰሩት በወንጅል ድርጊት ተጠርጥረው መሆኑን ተናግረው ነበር። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ እንደሚካሄድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በምርጫው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ነጋሳ ደሳለኝ
እሸቴ በቀለ