የቤተ-ሙከራ እጥረት ለሳይንስ ትምህርት እንቅፋት ሆኗል | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 12.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የቤተ-ሙከራ እጥረት ለሳይንስ ትምህርት እንቅፋት ሆኗል

የኢትዮጵያ መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ከወሰነ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ “70/30” ተብሎ የሚታወቀው ፖሊሲ እንደታሰበው ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ተማሪዎች በሁለተኛ ደረጃ ቆይታቸው የሳይንስ ትምህርቶችን በበቂ ሁኔታ በተግባር አለመማራቸው እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:16

“አብዛኞቹ ቤተ-ሙከራዎች በወጉ የተደራጁ አይደሉም”  

በአሜሪካ ኒውዮርክ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆነችው ሃና ዛሞራ የዛሬ ዓመት ተኩል ገደማ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ብላ ነበር፡፡ የበጋ እረፍቷን ተጠቅማ ኮንሰርን የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት በወላይታ የሚያከናውናቸውን ፕሮጀክቶች ስትጎበኝ ቆይታለች፡፡ በመስክ ጉብኝቷ ማጠናቀቂያ ላይ ከዕድሜና ትምህርት አቻዎቿ ጋር የመጨዋወት ዕድል አግኝታለች፡፡ በሶዶ ከተማ ባለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበራትን ቆይታ እንዲህ ገልጻዋለች፡፡  

“ተማሪዎች እና የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች የትምህርት ቤቱን ዙሪያ ገባ አሳዩን፡፡ ተማሪዎች ስለህይወታቸው አጫወቱን፡፡ ዶክተር፣ ሳይንስቲስት፣ አርቲስት፣ መምህር መሆን የሚመኙ አሉባቸው፡፡ የሳይንስ ቤተሙከራቸውን ሲያሳዩን ግን በጣም ተገርመናል፡፡ በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚጠቀሙበት ውሃ መልክ ጆግ ጭጋግ የለበሰ ይመስላል፡፡ ያሉት ኬሚካሎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ የተለጠፉት ፖስተሮች በእጅ የተሳሉ ናቸው፡፡ ይህን ቤተሙከራ ስድስት ሺህ ተማሪዎች በጋራ ይጠቀሙበታል፡፡ [ሆኖም] በአግባቡ የሚሰራ ዕቃም ሆነ ኬሚካል የለውም” ስትል ጉብኝቱ የጫረባትን መደነቅ በድረ-ገጽ ባወጣችው ጽሁፍ አካፍላለች፡

አሜሪካዊቷ ሃና የተመለከተችውን ቤተ-ሙከራ እና የአሮጌ አጋዥ መጽሀፍት ስብስብ ከራሷ እና በሀገሯ ካሉ ትምህርት ቤቶች ጋር አነጻጽራ ብትደመምም ትምህርቱ ቤቱ በኢትዮጵያ ሻል ያሉ ከሚባሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚመደብ መሆኑን አላወቀችም፡፡ ትምህርት ቤቱ የኢትዮጵያ ቁንጮ ባለስልጣናት እና አንቱታ ያተረፉ ሰዎችን ያፈራ መሆኑን ብትሰማ ኖሮ ደግሞ ጉዳዩ እንቆቆልሽ ይሆንባት ነበር፡፡

 

“ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በ1975 ዓ.ም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት አምጥተው ወደ ዩኒቨርስቲ የገቡት ከሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እና አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከዚህ ትምህርት ቤት ናቸው፡፡ ሌሎችም ዶክተሮች፣ ፕሮፌሰሮች፣ ናሳ ውስጥ ያሉ ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ሰዎች ያፈራ ትምህርት ቤት ነው” ይላሉ የሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተሾመ አየለ፡፡

እርሳቸው እየመሩት ያለው ትምህርት ቤት በሀገሪቱ ግማሽ ክፍለ ዘመንን ከተሻገሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡ በአጼ ኃይለስላሴ ተመርቆ የተከፈተው ይህ ትምህርት ቤት አንድ የመማሪያ ተቋም ሊያሟላቸው ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ የሆነውን የቤተ-ሙከራን ነገር በቅጡ ለማደራጀት የተሞከረበት ነበር- ሊያውም ለባዮሎጂ፣ ኬሜስትሪ እና ፊዚክስ የሳይንስ የትምህርት ዘርፎች ራሳቸውን የቻሉ ሶስት ቤተ-ሙከራዎችን በመገንባት፡፡ 

በ1970ዎቹ ዝነኛ የነበረው ይህ ትምህርት ቤት ዛሬ በቀድሞ ቁመናው ላይ አይደለም፡፡ ቤተ-ሙከራዎቹ እንኳ ባረጁ ዕቃዎች እና ከጥቅም ውጭ በሆኑ ኬሚካሎች መጨናነቁን ምክትል ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡ ሰባ መማሪያ ክፍሎች ያሉት አዲስ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ከዓመታት በፊት ከአጠገቡ ቢገነባም ቤተ-ሙከራዎች በውስጡ አላካተተም፡፡ ነባሩ ትምህርት ቤት በ44 ክፍሎች ውስጥ ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች በተጨማሪ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በቤተ-ሙከራዎቹ ያስተናግድ ዘንድ ተፈርዶበታል፡፡ ይህ ደግሞ የሳይንስ ትምህርትን በአግባቡ ለመረዳት አጥብቆ የሚመከረውን የቤተ-ሙከራ የተግባር መማሪያ ጊዜን አጣብቧል፡፡ 

ለተግባር ትምህርት የሚሰጠው አነስተኛ ጊዜ ቤተ-ሙከራ ባለባቸው በርካታ የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የሚንጸባረቅ ነው፡፡ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ችግሩን በሻሸመኔ ባለ ሁለተኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤት መታዘብ ይቻላል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ የሆነው አሉላ ኃይሉ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን የተማረው በሻሸመኔ ጮራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዚያ የነበረውን የትምህርት አሰጣጥ እንዲህ ያስታውሳል፡፡ 

Deutschland Radsport Doping Probe

“ጮራ በሳምንት አንድ የቤተ-ሙከራ ክፍለ ጊዜ አለን፡፡ አሪፍ ነበረ ባይባልም፣ እንደልብህ መስራት ባትችልም ባለው ክፍለጊዜ የፈለግኸውን መስራት ትችላለህ፡፡ ከዚያ ውጭ ግን አትችልም፡፡ በተለምዶ ኬምስትሪን ብቻ ነበር [በቤተ-ሙከራ] የምናየው፡፡ ሌላው ያው በወሬ ብቻ  ነበር፡፡ አንድ ክፍል ውስጥ 75 ተማሪ ገደማ ነበር የምንማረው፡፡ ቤተሙከራ በዙር ነበር፡፡  ግማሽ ግማሽ ሆነን፣ በሳምንት አንደኛው፣ በሳምንት ደግሞ ሌላኛው ማለት ነው” ሲል በመንግስት ትምህርት ቤት ቆይታው የታዘበውን ያጋራል፡፡ 

ቤተ-ሙከራዎችን ለአንድ የሳይንስ ትምህርት ብቻ ማዋል አሊያም ሶስቱን የትምህርት ዓይነቶች በአንድ ቦታ በተግባር ለማስተማር መሞከር በብዙ ትምህርት ቤቶች የተለመደ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች በእንደዚህ ዓይነት “የጋራ” ቤተ-ሙከራዎች በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ይጠቁማሉ፡፡ በሰመራ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ መሐመድ ሰኢድ በአፋር ክልል ባሉ በተመረጡ ሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች በሳይንስ ዘርፍ የተግባር ትምህርት ለመስጠት ስላሉ ተግዳሮቶች ከሌላ መምህር ጋር ተቀናጅተው ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናታቸው ያተኮረባቸውን ጭብጦች በማስረዳት ይጀምራሉ፡፡

“በእያንዳንዱ የጥናት ቦታችን (በየትምህርት ቤቱ ላይ) የተግባር ተኮር የሚሰሩበት ቤተ-ሙከራ መኖር አለመኖሩን አይተናል፡፡ ካለም ደግሞ በአግባቡ የተደራጀ ነው ወይ? የሚለውን ነገር በራሳችን መስፈርት በየትምህርት ቤቱ ገምግመናል፡፡ ሌላው በተግባር ተኮር የሰለጠነ የሳይንስ ባለሙያ ወይም ላብ ቴክኒሽያን የምንላቸው አሉ ወይ? የሚለውን ነገር አይተናል፡፡ እኛ ጥናት ባካሄድንባቸው በእያንዳንዳቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሳይንስ ቤተ-ሙከራ ተግባር አልተሰራም ወደሚለው ድምዳሜ ላይ የደረስነው፡፡ ለየት ያለው ትምህርት ቤት አዋሽ የሚባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ እዚያ የተሻለ የሰሩበት ሁኔታ ነው ያየነው፡፡ ከዚያ ውጭ ባሉ ትምህርት ቤቶች ግን የሳይንስ ትምህርት በተግባር ተደግፎ አላገኝንም፡፡ ሁለተኛ እንደውም ቤተ-ሙከራዎች ጭራሽ የሌሉበትም አይተናል” ሲሉ በጥናታቸው የደረሱበትን ግኝት አብራርተዋል፡፡ 

ባለፈው ዓመት በሳይንስ ጆርናሎች ላይ የታተመው የእነ አቶ መሐመድ ጥናት በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ያሉ ቤተ-ሙከራዎች በሚገባ አለመደራጀታቸውን አመላክቷል፡፡ የ“ጋራ” የሚባሉ ቤተ-ሙከራዎች ጠባብ፣ በዛ ያሉ ተማሪዎችን ማስተናገድ የማይችሉ፣ ንጽህናቸው ያልተጠበቀ እና ለስራ ያልተመቹ እንደሆነ ዘረዝሯል፡፡ በአንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች በቤተ-ሙከራነት የሚያገለግሉት ክፍሎች ለዚያ ዓላማ ተብለው ያልተገነቡ መሆናቸውን እና በራቸው፣ መስኮታቸው አሊያም ጣራቸው የተሰበረ እንደሆነ ገልጿል፡፡  

አገልግሎት በሚሰጡት ቤተ-ሙከራዎች በጥቂት መጠንም ቢሆን እንኳ ከቤተ-ሙከራ ሊጠፉ አይገባም የሚባሉ ኬሚካሎች አለመኖራቸውንም ይፋ አድርጓል፡፡ ተገዝተው የመጡ ኬሚካሎችም ቢሆን በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ በየትምህርት ቤቶቹ ባለመኖሩ በዘፈቀደ እንደሚቀመጡ አሳይቷል፡፡ በማቀዝቀዣ መቀመጥ የሚ

ኖርባቸው ኬሚካሎች እንዲሁ እንደሚተዉ እና በቂ አየር በማይዘዋወርበት ቦታ እንደሚከማቹም ጠቁሟል፡፡ በአግባቡ የማይከማቹ እና የማይወገዱ ኬሚካሎች የሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ችግር ነው፡፡

“ሳይንስ ላይ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች እና ዕቃዎች አስወጋጅ ቡድን ማጣቱ ቤተ-ሙከራውን እንዲጨናነቅ አድርጓል፡፡ መምህራንም ለመስራት ፍቃደኛ ሆነው ወደ ቤተ-ሙከራ ቢገቡም የበለጠ የተግባር ስራ ለመስራት ኪሚካሎች ላይ ስጋት አለባቸው፡፡ እነዚህ የድሮ ኪሚካሎች እነ ሃይደሮክሎሪክ አሲድ፣ ናይትሪክ አሲድ በጠርሙስ ውስጥ እንደተቀመጡ ነው ያሉት፡፡ ሊፈነዳ ሁሉ ይችላል የሚል ስጋት አለባቸው” ይላሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተሾመ፡፡

ለቤተ-ሙከራ የተገዙ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ ሳይውሉ ባክነው መቅረታቸው በኦሮሚያ ክልል ባሉ ትምህርት ቤቶች ላይም ይስተዋላል፡፡ በመቱ ዩኒቨርስቲ የማይክሮ ባይሎጂ አስተማሪ የሆኑት አቶ ተካልኝ ቀጀላ በኦሮሚያ ክልል በኢሉባቡር ዞን በቤተ ሙከራ ግብዓት ይዘትና አጠቃቀም ላይ የሚያጠነጥን ጥናት አካሄደው ነበር፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት በ12 ትምህርት ቤቶች ላይ የካሄዱትን ጥናት ባለፈው መስከረም በሳይንስ ጆርናል ላይ አሳትመዋል፡፡

“አንዳንድ ቦታ ላይ ግብዓትም እያላቸው በተግባር አይውሉትም፡፡ ቤተ-ሙከራ ተዘግቶ ነው የሚቀመጠው፡፡ ያለውን ግብዓት ምንም ሳይጠቀሙ፣ ከእሽጉ እንኳ ሳያወጡት ተበላሽቶ አለ” ሲሉ ጥናታቸውን በሚካሄዱበት ወቅት የታዘቡትን ያጋራሉ፡፡ 

በሌሎቹ ትምህርት ቤቶች ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ደግሞ ጥናታቸውን ተመርኩዘው ያብራራሉ፡፡ “ትምህርት ቤቶቹን በሶስት ቦታ ከፍዬ ነው ያየሁት፡፡ በጣም ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ትምህርት  ቤቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ራሱ ትልቅ ቦታ ያላቸው እንደ ጎሬ፣ መቱ እና አልጌ ያሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ከተመሰረቱ ብዙ ዕድሜ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ አዲስ የተቋቋሙ ትምህርት ቤቶችም አሉ፡፡ ሰላሳ ሶስት በመቶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ምንም የቤተ-ሙከራ ግብዓት የለም፡፡ ቤተ-ሙከራ የሚባል ነገር እንኳ የላቸውም፡፡ በኬምስትሪ፣ በፊዚክስም እንደዚሁ ነው፡፡ እና በጣም ችግር ውስጥ እንዳሉ ነው ያየሁት፡፡” 

Symbolbild Labor, Reagenzglas

የዶክትሬት ትምህርታቸውን በባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ በህንድ እየተከታተሉ ያሉት አቶ ተካልኝ የቤተ-ሙከራ የተግባር ስራ ለሳይንስ ተማሪዎች ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡ በጥናታቸውም ቤተ-ሙከራን በአግባቡ መጠቀም ከተማሪዎች የውጤት ስኬት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ እንዳለው አረጋግጠዋል፡፡ ግብዓቶች የተማሉሏቸው ጥሩ ቤተ-ሙከራዎች ያሏቸው ትምህርት ቤቶች እና የተግባር ትምህርትን በመምህራኖቻቸው በሚገባ የሚወስዱ ተማሪዎች በሳይንስ ውጤታቸው ልቀው መገኘታቸውንም በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

በተግባር የመማር ጥቅሞቹን “አንደኛ በደንብ ያስታውሱታል፡፡ ሁለተኛ ይህ ለምን ሆነ? የሚለውን ማንሳት ይችላሉ፡፡ ሶስተኛ ነገር ደግሞ የፈጠራ ችሎታቸው እንዲነሳሳ የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ- ሙከራ በሳይንስ መማር ማስተማር ትልቅ ቦታ ይኖረዋል ማለት ነው” ሲሉ ይዘረዝሯቸዋል፡፡     

የቤተ-ሙከራ የተግባር ትምህርት ወሳኝነት የገባት የምትመስለው አሜሪካዊቷ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሃና በሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁኔታ ተደንቃ ብቻ ዝም አላለችም፡፡ ከኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር ስትሰነባበት “ምን ቃል ትገቢልናለሽ?” ሲሉ ለጠየቋት “የሳይንስ ቤተሙከራችሁን ለማሻሻል በጎ ፍቃደኛ እሆናለሁ” ብላቸው ነበር፡፡ ለትምህርት ቤቱ የቤተ-ሙከራ ዕቃዎችን መግዛት የሚያስችላትን ገንዘብ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ “ጎፈንድሚ” በተሰኘው ድረ-ገጽ የጀመረችው ወደ ሀገሯ በተመለሰችበት ወር ነው፡፡

ሃና አንዳንድ የቤተ-ሙከራ ዕቃዎች ከ5 እስከ 15 ዶላር ባሉ ዋጋዎች በገበያ ላይ መገኘታቸውን አውቃለች፡፡ ለዚህም ይመስላል አጠቃላይ ለማሳባሰብ የወሰነችውን የገንዘብ ጣሪያ አንድ ሺህ ዶላር የገታችው፡፡ በ18 ወር ውስጥ ካሰበችው በላይ 1‚245 ዶላር ሰብሰባለች፡፡ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ገጿ አሁንም ክፍት ነው፡፡ አዳጊዋ ሃና ውጥኗን እስክታሳካ እና የሚታደገው አካል እስኪመጣ ድረስ ከጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ተመራማሪ ያፈራው ትምህርት ቤት በዕድሜ ጠገብ ቤተ-ሙከራዎቹ መንገታገቱን ይቀጥላል፡፡  

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ
     
 

Audios and videos on the topic