የቤተእስራኤላውያን እሮሮ በእስራኤል | ዓለም | DW | 08.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የቤተእስራኤላውያን እሮሮ በእስራኤል

በእስራኤል ኣገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ቤተእስራኤላውያን የኑሮ ውድነትን በመቃወም ኣደባባይ እየወጡ ነው። ከመንግስት የሚደረገው ድጎማ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ በተለይም ቤት መግዛት እንዳልቻሉም ይናገራሉ። በዚያች ኣገር የሚኖሩ የኣፍሪካ ስደተኞችም የእስራኤል መንግስት የውጪ ስደተኞችን ከኣገሩ

ለማስወጣት የያዘውን እቅድ በመቃወም ባለፈው ሳምንት ኣደባባይ ወተው ነበር።

በኣፍሪካ ስደተኞች የልማት ማዕከል መረጃዎች መሰረት በኣሁኑ ጊዜ በእስራኤል ኣገር 60 ሺህ ያህል የውጪ ስደተኞች ይገኛሉ።

ባለፈው ሐሙስ በእየሩሳሌም እና በናታኒያ ከተሞች አደባባይ የወጡት በመቶዎች የሚቆጠሪሩ ቤተእስራኤላዊያን ዋናው ጥያቄያቸው የኑሮ ውድነትን መጋፈጥ ኣለመቻለቸው ሲሆን ከዚሁ የተነሳ የፍጆታ ሸቀጦችን መሸመት ከባድ እየሆነባቸው መምጣቱን ይናገራሉ። መንግስት የሚሰጣቸው ድጎማ ቢኖርም ከዋጋ ንረቱ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ በተለይም ቤት መግዛት ኣለመቻላቸውንም ያስረዳሉ። ከዚሁ የተነሳም ብዙዎቹ እጅግ በተጣበቡ የመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ለመኖር መገደዳቸውንም ይገልጻሉ። ከዚህም ሌላ በእስራኤል ኣገር መገለልና አድልዎ እንደሚደርስባቸውም ቤተእስራኤላውያኑ ያማርራሉ።

በተያያዘ ዜና በእስራኤል ኣገር የሚገኙ የውጪ ስደተኞችም መንግስት ከስደተኞች አንጻር የያዘውን የማስወጣት እቅድ በመቃወም ባለፈው ሳምንት በቴላቪቭ ከተማ ኣደባባይ መውጣታቸው ታውቐል። የሰልፉም ዓላማ ተገቢ ኣያያዝን ጨምሮ በስደተኝነት ተቀባይነት ኣግኝተው የመኖሪያና የስራ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ ሲሆን የARDC ስራ ኣስኪያጅ አቶ ዮኃንስ ባዩ እንደሚሉት የእስራኤል መንግስት ስደተኞች ወደኣገሪቱ እንዳይመጡ ከወዲሁ ለመከላከልና የገቡትም ቢሆኑ ተስፋ ቆርጠው ወደየመጡበት እንዲመለሱ የሚያስገድድ ህግ እያጸደቀ ነው።

የእስራኤል መንግስት የዚህ ዓይነቱን ህግ ሲያወጣ በእርግጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ኣይደለም የሚሉት አቶ ዮኃንስ ባዩ ከዙህ በፊት የወጣውን ተመሳሳይ ህግ ድርጅታቸው ARDC በፍ/ቤት ተሟግቶ ውድቅ ማድረጉን ኣስረድቷል። የበፊቱ ህግ ወደዚያች ኣገር የሚገቡ ስደተኞች ተይዘው ለሶስት ዓመታት ያህል ያለኣንዳች ፍርድ እንዲታሰሩ የሚደነግግ ሲሆን የኣሁኑ ደግሞ ለኣንድ ዓመት ያህል በማጎሪያ ካምፕ እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው። የእስራኤል መንግስት እንደ ሳውዲ አረቢያው ሁሉ ስደተኞችን ኣስገድዶ ወደየኣገራቸው መመለስ ስለመቻሉ በእርግጥ የብዙዎች ስጋት ነው። የሆነ ሆኖ የእስራኤል ሁኔታ ከሳውዲ አረቢያው እንደሚለይ የጠቀሱት አቶ ዮኃንስ ባዩ የኣፍሪካ ስደተኞች የልማት ማዕከል ARDC ይህንኑ ድንጋጌ ለማስቀልበስ መሟገቱን እንደሚቀጥል ኣስረድቷል።

ጃፈር ዓሊ

ነጋሽ መሃመድ