የቤተሰብ ሸክሙ የጠናባቸው ጋናውያን ወጣቶች | ወጣቶች | DW | 18.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

የቤተሰብ ሸክሙ የጠናባቸው ጋናውያን ወጣቶች

ከጋና ህዝብ አብዛኛውን የሚይዙት ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች የሆኑት ናቸው፡፡ በሀገሪቱ በዚህ የዕድሜ ክልል ባሉ ዜጎች ላይ “የጥገኝነት ንፅፅር” (dependency ratio) ጎልቶ እንደሚታይ ጥናቶች ያመለክታሉ። በዚያ ያለው “የጥገኝነት ንፅፅር” በበርካታ አፍሪካ ሀገራት ካለው ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ መሆኑ በጥናቱ ተደርሶበታል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:10

የቤተሰብ ሸክሙ የጠናባቸው ጋናውያን ወጣቶች

በሰሜን ጋናዋ ታማሌ ከተማ ያለው የአቦአቡ ገበያ ደርቷል፡፡ ፋታው ያኩቡ እና ባልደረቦቹም ጥድፊያ ላይ ናቸው፡፡ ዕቃዎችን ይሸከማሉ፡፡ ፋታው “ቤተሰቤን ለመርዳት ስል በየቀኑ ይህን ማድረግ አለብኝ” ይላል ስለስራው ሲናገር፡፡  

ፋታው 27ኛ ዓመቱን ቢደፍንም ሚስትም ሆነ ልጆች የሉትም፡፡ ስራ የሌላቸው ወላጆቹን እና አምስት ዘመዶቹን የመርዳት ኃላፊነቱን ለመወጣት በየቀኑ ይታትራል፡፡ እንደፋታው በገበያ ውስጥ የሚሰሩ ብቻ አይደሉም ቤተሰብ የመርዳት ከባድ ሸክም የወደቀባቸው፡፡ እንደ ክሌሜንት ቦቴንግ ያሉ በንጽጽር የተሻለ የሚባል ስራ የሚሰሩ ወጣቶችም በተመሳሳይ ምክንያት በርካታ ስራዎችን እንዲሰሩ ይገደዳሉ፡፡

ክሌሜንት በዚያው በታማሌ በሚገኝ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የህዝብ ግንኙነት መኮንን ሆኖ ይሰራል፡፡ ከመደበኛ ስራው ውጭ ሌሎች ስራዎች መደረብ ያስፈለገበትን ምክንያት እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ “በዙሪያዬ ላሉት ቤተሰቦቼ በቂ ገንዘብ መስጠት እንዲያስችልኝ በተጨማሪ ጠንክሬ መስራት አለብኝ፡፡ የተመቻቸው ቤተሰቦቼ ለሌሎች የቤተሰብ አባላትም ተመሳሳዩን ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ለእኔ ሸክም ነው ነገር ግን እንደ አፍሪካዊ እነዚህን ኃላፊነቶች መሸከም አለብኝ” ይላል።   

እንደ ክሌሜንት ገለጻ በወር ከሚያገኘው ገቢ ጠቀም ያለ መጠን ለቤተሰቦቹ ይሰጣል። “በየወሩ ከማገኘው  20 በመቶ ገደማውን ለእነዚያ ነገሮች አውላለለሁ፡፡ ያንን ገንዘብ ቆጥቤ፣ ለንግድ እና መሰል ተግባራት ባውል ሌሎች ሰዎችን መቅጠር እችል ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ማድረግ አልቻልኩም፡፡ በቤተሰቤ ውስጥ ሳይበላ የሚያድር  ሰው እያለ ገንዘብ ልቆጥብ አልችልም፡፡ አይደረግም!” ይላል ጫን ባለ ድምጽ። 

ሁለቱ ወጣቶች በሚኖሩበት ታማሌ ከተማ ያለዉ አዳራሽ ገጉት በሚታይባቸው  ወጣቶች ተሞልቷል፡፡ ወጣቶቹ በዚያ የተሰበሰቡት ለወደፊት ህይወታቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሀሳቦች የሚያካፍላቸውን ተናጋሪ ለማድመጥ ነው፡፡ ሀገራቸውን ታላቅ ለማድረግ እያንዳንዳቸው ሚና እንዳላቸው ያስታውሱ ዘንድ የጋናን ብሔራዊ መዝሙር ዘምረዋል፡፡  

ከጋና ህዝብ አብዛኛውን የሚይዙት ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች የሆኑት ናቸው፡፡ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በዚህ የዕድሜ ክልል ባሉ ዜጎች ላይ ጎልቶ የሚታየውን “የጥገኝነት ንፅፅር” (dependency ratio) ለማቅለል በብርቱ እያጣሩ ነው፡፡ በኢኮኖሚክስ፣ ጆኦግራፊ፣ የህዝብ ጥናት እና ሶሺዮሎጂ ዘርፎች ጥቅም ላይ የሚውለው “የጥገኝነት ንፅፅር” ጽንሰ ሀሳብ ስራ ሳይኖራቸው በሌላው ላይ ጥገኛ የሚሆኑቱ በሚሰራው የሰው ኃይል የሚያሳርፉትን የኢኮኖሚ ሸክም የሚገልጽ ነው፡፡ በጎርጎሮሳዊው 2016 በጋና የተደረገ ጥናት በሀገሪቱ ያለው “የጥገኝነት ንፅፅር 66.7 በመቶ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ይህ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ካለው ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ነው፡፡

በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ከአምራች ኃይሉ ይልቅ ጥገኞቹ በዙ ማለት በአንድ ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ባሉ ጥቂት ስራ ማግኘት በቻሉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ግፊት መኖሩን አመላካች ነው፡፡ በጋና ለምሳሌ አንድ ሰው ሰባት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን እንዲደግፍ ይጠበቅበታል፡፡ “የጥገኝነት ምጥጥኑ” ከፍ ማለት በተለይ በወጣቶች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ወጣቶች የሚመኙትን ከመስራት ይልቅ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለመሟላት በርካታ ስራዎችን እንዲሰሩ ይገደዳሉ፡፡ ስለወደፊት ህይወታቸው ተረጋግተው ለማቀድ እና ለዚያ የሚሆናቸው ተጨማሪ ዕውቀትም ሆነ ክህሎት ለመገብየት በቂ ጊዜ ያጣሉ፡፡ 

ማህማ ቴኒ በታማሌ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ (UNFPA) ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ውስጥ  ይሰራሉ፡፡ በወጣቶች ዘንድ የሚስተዋለውን ትልቅ ቤተሰብ የመመስረት አካሄድ መለወጥ ይሻሉ፡፡ የዚህን ጠቀሜታ በታማሌ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ወጣቶችም ነግረዋቸዋል፡፡ 

“የእህታችሁን፣ የወንድማችሁን ልጆች ወይም ሌሎችን ሳይሆን ለሚስታችሁ እና ለልጆቻችሁ ጥሩ እንክብካቤ አድርጉ፡፡ ይህ ማለት ትርፍ አካባታችሁ ማለት ነው፡፡ እናንተ እየሰራችሁ ገንዘቡን በሌላ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ ትችላላችሁ” ሲሉ ወጣቶችን መክረዋል።

በጋና ድህነት በአብዛኛው ጠንቶ የሚታየው ሰፊ ቤተሰብ ባላቸው ዘንድ ነው፡፡ በሰሜን ጋና የስነ-ህዝብ ካውንስል ኃላፊ የሆኑት አልሃጂ ኢሱፉ ኢዲ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ 

“ትሰራለህ፡፡ በወሩ መጨረሻ ግን ስራ ያለህም አትመስልም፡፡ የምትገኘው ሁሉ ለቤተሰብህ ይሄዳል፡፡ ሰዎች መጥተው በርህን ይንኳኳሉ፡፡ ለልጆቻቸው የትምህርት ቤት ክፍያ ካንተ ይፈልጋሉ፡፡ የእህትህ ወይም የወንድምህ ልጅ በር ላይ መጥታ ወደ ሆስፒታል መሄድ እንደምትፈልግ ትነግርሃለች፡፡ እምቢ ማለት አትችልም፡፡ በስተመጨረሻ ግማሾቻችን ለብድር ስንዞር እንገኛለን” ይላሉ፡፡ 

የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አልሃጂ ኢሱፉ ኢዲ ይህ ችግር በራሳቸው ላይም እንደሚስተዋል ይናገራሉ፡፡ ከሩቅ ዘመዶቻቸው በሚመጡ የገንዝብ ጥያቄዎች ምክንያት በወሩ መጨረሻ ባዶቸውን እንደሚቀሩ ያስረዳሉ፡፡ ይህን አዙሪት በማህበረሰቡ ተደጋግሞ መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ 

ሙሳ አሚና በሙያቸው ነርስ ናቸው፡፡ ይኖሩበት ከነበረው ከተማ ለቅቀው ወደ ትውልድ መንደራቸው ተመልሰዋል፡፡ ከወለዷቸው ሶስት ልጆች ባሻገር ሁለት ተጨማሪ ልጆች አስጠግተዋል፡፡ ከሰፊው ቤተሰባቸው ደግሞ በአጠቃላይ 10 ሰዎችን የመርዳት ኃላፊነት አለባቸው፡፡

“አሁን የተጋፈጥኩትን ለማንም ቢሆን አልመኝም፡፡ ለጠላቴም ቢሆን፡፡ የምረዳው አነስተኛ የቤተሰብ መጠንን ነው፡፡ በድህነት ውስጥ እንዳለሁ አውቃለሁ፡፡ ይህን ጭነት ባልሸከም ኖሮ ልቆጥበው የምችለው ገንዘብ አሁን በጣም ደስተኛ ሴት ሊያደርገኝ ይችል ነበር“ ይላሉ አሚና፡፡ 

ገንዘብ መቆጠብ መቻል ሰዎች በህይወታቸው የተሻለ ነገር ለማምጣት አቅም ይሆናቸዋል፡፡ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አሊያም በህይወታቸው የሚመኙትን ስራ እንዲሰሩ ያስችላቸዋል፡፡ እንደ አላሃጂ ኢሱፉ ኢዲ አባባል በጋና ለቁጠባ ያለው ጊዜም ሆነ አቅም አነስተኛ ነው፡፡  

“በምታገኘው አነስተኛ ደመወዝ ላይ ጥገኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በወሩ መጨረሻ ምንም አግኝ ምን እነዚህን ሰዎች ለመርዳት እንደሚውል እና የሚተርፍ ካለ ለራስህ ዕድገት ያለህ አነስተኛ እንደሆነ ትረዳለህ፡፡ ስለቁጠባ ለማውራት እና ወደፊት ለሚያጋጥሙህ ያልተጠበቁ ወጪዎች ለመዘጋጀት እንኳ አስቸጋሪ ይሆንብሃል” ሲሉ በራሳቸው ኑሮ ጭምር የታዘቡትን እውነታ ያጋራሉ።

ሞሃመድ ጃባሩ የተባሉ የታማሌ ነዋሪ ግን በአፍሪካ ያለው ሰፊ የቤተሰብ ትስስር ጠቀሜታም አለው ባይ ናቸው፡፡ “በህይወቴ እናቴ እና አባቴ ብቻ አይደሉም የረዱኝ፡፡ ሌሎችም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ትምህርቴን እስከጨርስ እና በዕድገቴ ሁሉ አግዘውኛል፡፡ እነርሱ የሩቅ የቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡ ስለዚህ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለን የምናምንባቸውን ሌሎች የቤተሰብ አባላትን መርዳት እንደ ኃላፊነት ነው የምንመለከተው፡፡”

በርካቶች ግን እንደ ሞሃመድ ጥቅሙ አይታያቸውም፡፡ የተወሰኑ ወጣቶች እንደውም ይህን ሽሽት ወደ ከተማ ይሰደዳሉ፡፡ በዚያም እያሉ ከሰፊ የቤተሰብ አባላት የሚቀርብላቸውን የገንዘብ ጥያቄ ለማምለጥ የስልክ ቁጥራቸውን በየጊዜው ይቀያይራሉ፡፡ መንግስት ይህን ችግር ለመቅረፍ በተቋም ደረጃ ያደራጀው ምንም ነገር ባይኖርም አዲስ ተጋቢዎች የሚወልዷቸውን ልጆች ቁጥር እንዲመጥኑ ሲመክር ይስተዋላል፡፡ ሆኖም የጋና ህዝብ ቁጥር ማሻቀቡ አሁንም አልተገታም፡፡

ማክስዌል ሱክ / ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች