የባዮ ጋዝ አብዮት በደቡብ ክልል | ጤና እና አካባቢ | DW | 07.01.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የባዮ ጋዝ አብዮት በደቡብ ክልል

የዓለማችን የህዝብ ቁጥር ዕድገት ማሻቀብ እና የተፈጥሮ ሐብት መመናመን ለኃይል አቅርቦት መቀነስ የየራሳቸውን አሉታዊ ተፅኖ እያሳደሩ እንደሚገኙ በየጊዜው የሚካሄዱ የዓለም አቀፍ ጥናት ውጤቶች ይጠቁማሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:21

ከዘጠና በመቶ በላይ ነዋሪዎቿ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ናቸው

ይህ የምድራችን ነባራዊ ሁኔታ ታዲያ መንግስታት እና የአካባቢ ተቆርቋሪ ድርጅቶች ትኩረታቸውን በታዳሽ የኃይል ምንጭ አማራጮች ላይ እንዲያደርጉ እያስገደዳቸው ይገኛል። ከእነኝሁ ታዳሽ የኃይል ምንጭ አማራጮች መካከል በቤተሰብ ደረጃ በመተግበር ላይ የሚገኘው የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ዘርፍ አንዱ ነው። በዚህ ረገድ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ነዋሪዎቿ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆነችውና በደቡብ ክልል የምትገኘው የወሻና ሶያማ መንደር በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።  

ወሻና ሶያማ በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በወንዶ ገነት ወረዳ የምትገኝ አነስተኛ መንደር ናት። በዚህች መንደር ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ነዋሪዎች የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆናቸው ይነገራል። የወሻና ሶያማ መንደር አባላት መልካም ተሞክሮ የተነሳ ዛሬ ላይ በተለያዩ ክልላዊና አገራዊ መድረኮች ላይ ስሟ ተደጋግሞ እየተነሳ እንደሚገኝ ከክልሉ ውኃ ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 
 ወይዘሮ ሸጊቱ አያኖ የዚሁ መንደር ነዋሪና የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ። ወይዘሮ ሸጊቱ «በወቅቱ የባዮ ጋዝ ፕሮግራም ሊጀመር ነው የሚለውን እንደሰማሁ ነገሩ ብዙም ካልተዋጠላቸው የመንደሩ ነዋሪዎች መካከል እኔም አንዷ ነበርኩ» ሲሉ ያስታውሳሉ ። «ይሁንእንጂ በማቅማማት የጀመርኩት የባዮ ጋዝ ፕሮጀክት በጭስ ሲያነባ ለከረመው አይኔ እረፍት የሚሰጥ መሆኑ የገባኝ ግን ዘግይቶ ነው።» ይላሉ። 

 የወሻና ሶያማ መንደር ነዋሪና የወይዘሮ ሸጊቱ ጎረቤት የሆኑት ወይዘሮ ሸዋዬ ሰብስቤ ደግሞ ከጤናቸው ይልቅ የወጪው ጉዳይ ያሳሰባቸው ይመስላል። ወይዘሮ ሸዋዬ በመንደራቸው የማገዶ እንጨት እንደልብ የማይገኝና ዋጋውም ከዕለት ዕለት የማይቀመስ እየሆነ ይገኛል ይላሉ። በማገዶ ፍጆታ ዙሪያ የነበረባቸው ችግር ታዲያ የባዮ ጋዝ ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆን ሲጀመሩ መለ በሙሉ መቀረፉን ይናገራሉ። 
 አቶ ዘርይሁን ደሳለኝ በደቡብ ክልል ውኃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ የባዮ ጋዝ አስተባባሪ ናቸው ። በአሁኑወቅት በኢትዮጵያ መንግስት እና በአውሮጳ ኅብረት ድጋፍ በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘውን የባዮ ጋዝ ፕሮጀክት ዓላማን እንዲህ ይገልጻሉ። 

 የባዮ ጋዝ ፐሮግራም አስተባባሪው አቶ ዘርይሁን ደሳለኝ እንደሚሉት የባዮ ጋዝ ልማት ከኃይል ምንጭነቱ በተጨማሪ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ። በተለይም ከባዮ ጋዙ ተብላልቶ የሚወጣው ተረፈ ምርት የፋብሪካን ማዳበሪያ በመተካት ለእርሻ አገልግሎት እየዋለ እንደሚገኝ ነው አስተባባሪው የሚናገሩት። 

 ወይዘሮ ሸጊቱና ወይዘሮ ሸዋዬ ጨምሮ የወሻና ሶያማ መንደር ነዋሪዎች የባዮ ጋዝ ልማት ጠቀሜታ የኃይል ፍላጎታቸውን በማርካት ብቻ የተገደበ አለመሆኑን ይናገራሉ። በተለይም ከባዮ ጋዝ የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለእርሻ ማዳበሪያነት መጠቀማቸው ቀደም ሲል ለፋብሪካ ማዳበሪያ ግዢ ያውሉት የነበረውን ወጪ አንዳስቀረላቸው ይናገራሉ። በአሁኑወቅት የሚያለሟቸው የሸንኮራ እና የአቮካዶ ምርቶች በፋብሪካ ማዳበሪያ ሲጠቀሙ ከነበረው የተሻለ ምርት እያገኙበት እንደሚገኙ ነው ተጠቃሚዎቹ የሚገልጹት። 

 በአርግጥ የባዮ ጋዝ ልማት የወሻና ሶያማ መንደር ነዋሪዎችን ሕይወት በእጅጉ ያቀለለ ቢሆንም ቴክኖሎጂውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት ግን ማነቆዎች ማጋጠማቸው አልቀረም። በተለይም ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚያስፈልገው የገንዘብ ወጪና ይህንኑ ከሚደገፉ የፋይናንስ ተቋማት በቂ የብድር አቅርቦት አለመኖር አሁንም ዋነኛ የፕሮግራሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ነው የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ዘርይሁን ደሳለኝ የጠቀሱት። 


ሙሉዉን ቅንብር የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ። 

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ 

አዜብ ታደሰ 
 

Audios and videos on the topic