የባራክ ኦባማ ጉብኝት በጀርመን | ዓለም | DW | 24.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የባራክ ኦባማ ጉብኝት በጀርመን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አምስተኛውን እና ምን አልባትም በሥልጣን እያሉ የመጨረሻቸው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን የጀርመን ጉብኝት ዛሬ በመጀመር ሰሜናዊቷ የሐኖቨር ከተማ ውስጥ ከመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር ንግግር አሰሙ።

ፕሬዝዳንቱ ከጀርመን መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር በመሆን ከሚሳተፉበት የኢንዱስትሪ ንግድ ትርዒት በተጨማሪ የትራንስ አትላንቲክ የንግድና መዋዕለ ነዋይ ትብብር ውል ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የጀርመን ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል በአውሮጳ ያሳዩትን የአመራር ክህሎት አወድሰዋል።

ቅዳሜ፤ ሚያዝያ 15 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. ለኅትመት ከበቃው «ቢልድ» ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አንጌላ ሜርክል፦ «እውነተኛ የፖለቲካ እና የሞራል አመራር» ማሳየታቸውን ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በርካታ መሰናክሎች አሉበት ባሉት የትራንስ አትላንቲክ የንግድና መዋዕለ ነዋይ ትብብር ውል ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲኖር ግፊት እንደሚያደርጉ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ጠቁመዋል።

የትራንስ አትላንቲክ የንግድና መዋዕለ ነዋይ ትብብር ውልን በተመለከተ በነገው እለት ወሳኝ ንግግር ካሰሙ በኋላም የጀርመን ጉብኝታቸው ይጠናቀቃል።

ፕሬዚዳንቱ በዛሬው ንግግራቸው ወቅት ዓለማችን ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድንን መዋጋትን የመሰለ ተግዳሮት ገጥሟታል ብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመንም ከምን ጊዜውም በበለጠ ሽብርተንነትን በጋራ ለመዋጋት ብሎም የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተንግረዋል። መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል አውሮጳ የገጠማትን የስደተኞች ቀውስ በተመለከተ አያያዛቸውን ፕሬዚዳንቱ አወድሰው አድናቆታቸውን ገልጠዋል። መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን፦ «በታሪክ ትክክለኛው መንገድ ላይ ናቸው» ሲሉ አሞግሠዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ