የባራክ ኦባማ ንግግርና የደቡብ ሱዳን ምላሽ | አፍሪቃ | DW | 30.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የባራክ ኦባማ ንግግርና የደቡብ ሱዳን ምላሽ

የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 17 ቀን ቋሚ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ አሊያም ጥብቅ ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል በመናገራቸው ተቆጥተዋል። ባራክ ኦባማ ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፉት የኬንያና ኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ማገባደጃ ላይ በአፍሪቃ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረጉት ንግግር ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:34
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
02:34 ደቂቃ

የባራክ ኦባማ ንግግርና የደቡብ ሱዳን ምላሽ

ፕሬዝዳንቱ የደቡብ ሱዳን መንግስትና አማጽያን ልዩነታቸውን ለመፍታት ያሳዩትን ቸልተኝነት ተችተው ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውንና የአንድነት መንግስት ለመመስረት ያስችላል ያሉትን ስምምነት በፍጥነት እንዲፈርሙ አሳስበዋል።

የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የአፍሪቃ ህብረት አዳራሽ ንግግር በርካታ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናትን አስቆጥቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባርናባ ማርያል ቤንጃሚን በጦርነት የተመሰቃቀለችውና 10 ሚሊዮን ህዝብ ስላላት ደቡብ ሱዳን ውስብስብ የሰላም ሂደት ባራክ ኦባማ ያደረጉት ንግግር ተገቢ አይደለም ሲሉ ከጁባ ተናግረዋል።

«የሰላም ሂደት ንግግር ነው። የሰላም ሂደት በጊዜ ሊወሰን አይችልም። ውይይቱ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ላይጠናቀቅ ይችላል። የሰላም ስምምነት በጊዜ ሊገደብ አይችልም። ይህ መሸነፍና ማሸነፍ እንዳለበት ጦርነት አይደለም። በመጨረሻ ተገቢ የሆነውን፤ በሰላም፤ በአንድነትና ይቅር ባይነት አገራቸውን ወደፊት የሚያራምዳትን የሚወስኑት የደቡብ ሱዳን ዜጎች ናቸው።»

በቻይና ሰራሹ የአፍሪቃ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ አስራ ዘጠኝ ወራት በዘለቀውና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ መሠረት ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተውበታል የተባለውን ግጭት እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። በንግግራቸው የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና የአማጽያኑ መሪ ሪየክ ማቻር ከቋሚ የሰላም ስምምነት መድረስ አለመቻላቸውን ተችተዋል።

«ኪርም ይሁኑ ማቻር ህዝቡን ከመከራ ለመታደግ ወይም ከፖለቲካዊ መፍትሄ ለመድረስ ፍላጎት አላሳዩም። ኪርና ማቻር በነሐሴ 17 ከስምምነት ሊደርሱ ይገባል። ካልሆነ ግን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከስምምነት ባለመድረሳቸው ቅጣታቸውን ከፍ ሊያደርግ ይገባል።»

የፕሬዝዳንቱን ይህን ሃሳብ በቀጥታ እንደ ማዕቀብ የተረጎሙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባርናባ ማርያል ቤንጃሚን ሶስት ተከታታይ ጥያቄዎች ያነሳሉ።

«ለምን ማዕቀብ ይጣልብናል? ለማዕቀብ የሚያበቃ አንዳች ወንጀል አልፈጸምንም። ማዕቀብ የት ሰርቶ ያውቃል?ሰላም በምትፈልግ አገር ላይ ማዕቀብ ይጣላል?»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ የአውሮጳ ህብረትና አሜሪካ ስድስት የጦር መሪዎች ላይ የጉዞና የሃብት ማዕቀብ መጣላቸው አይዘነጋም። የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ ለሚከታተሉት ኬንያዊ አጊና ኦጅዋንግ ግን አሁን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል።

Der Außenminister von Süsudan Barnaba Marial Benjamin

የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባርናባ ማርያል ቤንጃሚን

«የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች በሚቀጥለው ወር 17 ኛው ቀን ከስምምነት እንዲደርሱ የተቀመጠው አስገዳጅ ቀነ ገደብ ጊዜውን ያገናዘበ ውሳኔ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ድምጽና ዩናይትድ ስቴትስ ባላት ተደማጭነት ምክንያት የሚፈረም ስምምነት ተግባራዊነት የተረጋገጠ ይሆናል። ዋናው ጉዳይ ይህ ነው።»

ጄምስ ሺማንዩላ/እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic