የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የሥራ ማቆም አድማ | ኢትዮጵያ | DW | 08.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የሥራ ማቆም አድማ

በባሕር ዳር ከተማ ከአንድ አመት በፊት በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ተቃዋሚዎችን በመዘከር የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ። በዛሬው አድማ የመጓጓዣ አገልግሎት ከወትሮው በተለየ የተቀዛቀዘ ሲሆን መደብሮችም ተዘግተዋል። የሥራ ማቆም አድማው የተደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ባነሳ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:45

ነዋሪዎች ከዓመት በፊት በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰልፈኞችን ለመዘከር ያለመ ነው ብለዋል

ባሕር ዳር ጸጥ ብላ ውላለች። የህዝብ መጓጓዣዎች እንደ ወትሮው ግልጋሎት አልሰጡም። ሱቆች እና መደብሮችም ተዘግተዋል። ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ እንደሚናገሩት የተደረገው አድሞ ቀድሞ የታቀደ ነበር።

"ዛሬ ባሕር ዳር ላይ አድማ ነገር አለ። ሱቆች ተዘግተዋል። መጓጓዣ የለም። ባጃጆች ሁሉ አቁመዋል። ጸጥ ብላለች፤ታስፈራለች፤ቀዝቅዛለች። እኔ ትናንትና ጀምሮ እንደዚህ አይነት ነገር እንደሚኖር ጽሁፍ እያነበብኩ ነበር። ጥሪ ነበረ።"

ያነጋገርናቸው የባሕር ዳር ነዋሪዎች የዛሬውን የስራ ማቆም አድማ "ማን እንዳቀናጀው አይታወቅም" ይበሉ እንጂ ከአንድ አመት በፊት በጸጥታ አስከባሪዎች የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ለመዘከር መታቀዱ ግን አልጠፋቸውም።"በትክክል ማን እንደ ሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። ከትናንት ጀምሮ ከተማ ውስጥ ይወራ ነበረ። የዛሬ ዓመት ነው ሰልፍ የነበረው እዚህ ከተማ ላይ። በዚያን ጊዜ በጣም ብዙ ሰዎች በጥይት ሞተዋል። ቤታችን ቁጭ በማለት እነሱን እናስባለን የሚል ነገር ይወራል።" ይላሉ አንድ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ።

 ከአንድ አመት በፊት ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ባሕር ዳር ከተማ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የጸጥታ አስከባሪዎች በተኮሱት ጥይት በርካቶች መገደላቸው አይዘነጋም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በማግስቱ ባወጣው ዘገባ ቢያንስ 30 ተቃዋሚዎች መገደላቸውን አትቶ ነበር።

ባሕር ዳር ያዘነችበትን ቀን የሚያስታውሱት የከተማዋ ነዋሪ የዛሬው ተቃውሞ ዓላማ የሞቱትን መዘከር ብቻ አይደለም ባይ ናቸው። "በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ጠይቀው የወጡ ሰልፈኞች በታጠቁ የኢህአዴግ ወታደሮች ተጨፍጭፈዋል ያለ አግባብ። ያን በማሰብ እና ዕለቱን በማክበር እንዲሁም ደግሞ ቀጣይ እንደሆነ ለማረጋገጥ የተደረገ ነው።"

"ባሕር ዳር ገበያ አካባቢ ሱቆች ተዘግተዋል። ምንም አይነት ነገር የለም። አንዳንድ ታክሲዎች እና ባጃጆች ይሰራሉ። መደብሮች፤የግል ሱቆች የመዋቢያ እቃዎች መሸጫዎች ተዘግተዋል።ገበያ እና ልኳንዳ ቤት የለም።" ትላለች የከተማዋን መቀዛቀዝ የታዘበች ወጣት።

በከተማዋ የሚኖሩ የአይን ምስክር የዛሬውን የባሕር ዳር ውሎ ''ጤናማ አይደለም" ይሉታል። የሥራ ማቆም አድማው ከቀጠለ "ወደሌላ ነገር ያመራል" የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል። "የንግድ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ቆመዋል። ጥቂት ባጃጆች ብቻ ይንቀሳቀሳሉ። ሌላው ነገር ሁሉ ጭር ያለ ነገር ነው። ባጃጆች የተወሰኑ አሉ። ግን ከተማው ውስጥ ከሚሰራው ባጃጅ አንፃር ስታየው አለ ብለህ መናገር የምትችለውም አይደለም። ጤናማ አይደለም። ከተማው ላይ ድባቡ ጥሩ ነገር አይሰማም። ዛሬ ብቻ ከሆነ በዚሁ ይጠናቀቃል። ነገም ከነገ ወዲያም የሚቀጥል ከሆነ ወደ ሌላ ነገር ያመራል ብለን እናስባለን።"

ወትሮ ከተማዋን የሚያደምቋት እና በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩት ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ከባሕር ዳር ጎዳናዎች መቀነሳቸውን ያስተዋለው ወጣት የስራ ማቆም አድማው የፈጠረውን ጭርታ ታዝቧል። "ጠዋት ላይ ምንም አይነት መጓጓዣ አልነበረም። የአንዳንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ካልሆነ በስተቀር። ሰርቪስ የሚጠቀሙ የመንግሥት ሰራተኞች ናቸው ወደ ሥራም ሲሔዱ የነበሩት። ባጃጆችም ታክሲዎችም ሥራ አልጀመሩም ነበር። አሁን ረፋዱ ላይ እያስገደዷቸው ይመስለኛል አምስት ሰዓት ከሆነ በኋላ አንዳንድ ባጃጆች መንቀሳቀስ ጀምረዋል።"

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ የሆነችው ባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ ፔዳ መስመር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የቦምብ ፍንዳታ ገጥሟታል። የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ለአማራ መገናኛ ብዙኃን አምስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል። የፖሊስ አዛዡ በፍንዳታው የተጎዳ ሰው አለመኖሩንም ተናግረዋል።

"አዲስ አበባ ስብሰባ ላይ ነኝ።" ያሉት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም ብለዋል። የክልሉ ፕሬዝዳንት ቢሮ እና የፖሊስ ኮሚሽን ስልኮችም ጥሪ አይቀበሉም። የከተማዋ ነዋሪዎች ጸጥታ ኃይሎች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ታዝበዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች