የባለሥልጣናቱ እስርና የአትሌቶቹ ምርጫ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 28.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የባለሥልጣናቱ እስርና የአትሌቶቹ ምርጫ

ኢትዮጵያ በሙስና የተጠረጠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና የመረጣቸውን አትሌቶች ይፋ አድርጓል። ቅሬታዎችን፣ ድብደባም አስከትሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:19

የባለሥልጣናቱ እስርና ድብደባ ያስከተለው የአትሌቶቹ ምርጫ

ከሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ርእስ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ከሰላሳ በላይ የሚኾኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ከሙስና ጋር በተያያዘ እንደታሰሩ መነገሩ አንዱ ነው። የሀገሪቱን ሐብት የሚበዘብዙ ዋነኞቹ ሙሰኞችን እንዳላየ አልፎ እነዚህ ላይ ማተኮሩ ትርጉም የለውም ከሚሉ አንስቶ፦ «መንግስት የጀመረው ሁሉ በሕዝቡ ተቀባይነት አግኝቷል» እስከሚሉ የተለያዩ አስተያየቶች ድረስ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰንዝረዋል። የግብር ተቃውሞው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ የባለሥልጣናቱ መታሰር የብዙዎች መነጋገሪያ እንደመሆኑ መጠን አትሌቲክሱም ትኩረት ስቧል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በለንደን 16ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሳታፊ አትሌቶችን ይፋ ማድረጉ ከቅሬታ እስከ ድብደባም አዳርሷል። 

በኢትዮጵያ የግብር ተመን ያስከተለው ተቃውሞ አዲስ አበባ ውስጥ ዳር ዳር ማለት በጀመረበት ወቅት ነበር ሌሎች ሁለት ጎላ ያሉ ጉዳዮች የተደመጡት። የአምባሳደሮች ሹመትና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ነጋዴዎች የመታሰራቸው ዜና። ሁለቱ ጉዳዮች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ በፍጥነት ነበር አስተያየት የተሰጠባቸው። አንዳንዶች ሹመቱና እስሩ ተቃውሞውን ለማስቀየስ ጊዜ ጠብቀው የወጡ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል። ሌሎች ደግሞ መንግሥት በጀመረው ርምጃ እንዲገፋበት አበረታትተዋል። 

በተለይ ሪፖርተር ጋዜጣ ከሰላሳ በላይ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና የነጋዴዎችን ስም ዝርዝር ይዞ የመውጣቱን ዜና በርካቶች ተቀባብለውታል። አማር ቢን ያስር በፌስቡክ ገጹ፥ «ሰበር ዜና» ሲል የተጠርጣሪ እስረኞቹን ስም ከሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በመውሰድ አያይዟል።  ተጠርጣሪዎቹ የሥልጣን ደረጃቸው ከፍተኛ አለመሆኑን ለማመላከት ይመስላል፦ «የደረጃ "ሐ"ተጠርጣሪ ሙሰኞች ዝርዝር እንደሚከተለው ነው» ሲል አማር ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ የተጠርጣሪዎችን ስም ዝርዝር ጽፏል።  ብስራት ተሾመም እንደ አማር ደረጃ«ሐ» ሙሰኞች ሲል ጽፏል። 

«እነዚህ ሚጢጢዎቹ 1.2 ቢሊዮን ጉዳት አደረሱ ካሉ ራሳቸው ምን ያክል እንዳካበቱ መገመት ቀላል ነው። ሌባ ሁላ!!» በማለት ትዊተር ላይ ጽሑፉን ያሰፈረው ደግሞ አውራሪስ ነው። ደረጄ ጂ እዛው ትዊተር ላይ፥ «እነዚህ ሰላሳ አራቱ መጀመሪያ ላይ የ40/60 ዕድለኞች ነበር የመሰሉኝ» ሲል ተሳልቋል።

ተሰማ በላይ ደግሞ «ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ስም ዝርዝር» በሚል ኢንተርኔት ላይ የወጣውን የሪፖርተር ዜና በማያያዝ እንዲህ ሲል በእንግሊዝኛ ጽፏል።  «በተግባር ላይ ያሉ ሻርኮች ትንንሽ ዓሦችን እየሰለቀጡ ነው።» ጽሑፉ ከትዊተር ገጹ የተገኘ ነው።
ቀጣዮቹ አስተያየቶች ደግሞ መንግስት የወሰዳቸውን ርምጃዎች የሚደግፉ ናቸው። ከጠዓመ ሐጎስ እንጀምር፦ «መንግስት በራሳችን ስልጣን ስለሰጠነው የፈለገውን ማድረግ ይችላል አያገባችሁም» ብሏል ጠዓመ። ዐወቀ ለጥአርጌ ደግሞ፦ «ምንም አትጠራጠሩ የሚጨንቀው ቁጭ ብሎ የሚያወራ ካልሆነ በቀር መንግስት የጀመረው ሁሉ በህዝቡ ተቀባይነት አግኝቷል» የሚል አስተያየት ሰጥቷል። 

«የአሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ ፣የስርዓቱ ብልሹነት ከላይ ከመሰረቱ ስለሆነ አሁን በቁጥጥር ስር ዋሉ የሚባለው ሁሉ የወያኔ ጨዋታ መሆኑ ነው» የዓለማየሁ መንግስቴ የፌስቡክ አስተያየት ነው። «ዲሞከራሲ በለቤት ሀገር ለሞን አሥር ጊዜ አይቀያይርም ይችላል» የሚል አስተያየት ደግሞ ኃይሉ ንጉሥ አስፍሯል። በለጠ አበበ በፌስቡክ አስተያየቱ፦ «ኧረ [አሳፋሪ] ነው! የበላው ሳይጠይቅ የላሰው ሲታሰር» ብሏል።

ከዚሁ ከእስር ጉዳይ ሳንወጣ ሰሞኑን የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ ባሕርዳር ችሎት ለመታደም ባቀኑበት ወቅት ለአጭር ጊዜ መታገታቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ተናግረዋል። አቶ የሺዋስ ገና በአውሮፕላን ወደ ባሕር ዳር ጉዞ ማድረግ ከጀመሩበት ቅጽበት አንስቶ ታግቼ ተለቀቅኹ እስካሉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ኹኔታ በተከታታይ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴ አስነብበዋል። 

«የእነ መልካሙ ታደለ ቀጠሮ ወደነገ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ተዛወረ» ሲሉ የጻፉት አቶ የሺዋስ «እኔና የመኢአዱ አንሙት የኔዋስ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ካመቻቸን በኃላ ባህርዳር ተገኝተን ችሎቱን ተከታትለናል» ሲሉ አስነብበዋል። ጥቂት ቆየት ብለው ደግሞ፦ «ማንነታቸውን ለመግለፅ ፈቃደኛ ባልሆኑ ሰዎች አሁን ለጥያቄ ትፈለጋልህ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየተባልኩነው» የሚል ጽሑፍ ፌስቡካቸው ላይ አስፍረዋል። እነማን ናቸው እና የፍርድ ቤት ማዘዣ ካላሳዩህ የትም እንዳትሄድ የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችም ለአቶ የሺዋስ ተሰጥተዋል። አቶ የሺዋስ ትንሽ ዘግየት ብለው ግን መፈታታቸውን ገልጠዋል። እንዲህ በሚል አጭር ዐረፍተ ነገር። «ከጥቂት ጊዜ እገታና ማስፈራሪያ በኋላ ነፃ ሆኘ ተመልሻልሁ።»

የሹም ሽር እና እስሩ ዜና የብዙዎች መነጋገሪያ በሆነበት ቅጽበት በአeትሌቲክሱ ዘርፍም ከቃላት ንትርክ እስከ ድብደባ ያዳረሰ ውዝግብም ተሰምቷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከጥቂት ቀናት በኋላ በለንደን ለሚደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ውድድር በብሔራዊ ቡድኑ የሚያሳትፋቸውን አትሌቶች ይፋ ማድረጉ በርካታ ነገሮችን አስከትሏል። ከቅሬታ እስከ አሰልጣኝ ድብደባ።

በምርጫው ለጊዜው 40 አትሌቶች ተካተዋል። አቶ ስለሺ ብሥራት፦ «የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በለንደን 16ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን አስመልክቶ ትናንት አመሻሽ ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ በ40 አትሌቶችና በ13 የውድድር ዓይነቶች ትሳተፋለች» ሲሉ የአትሌቶችን ስም ዝርዝር ረቡዕ ዕለት በፌስቡክ ገጻቸው ይፋ አድርገዋል። 

የስፖርት አማካሪው ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ ነጋሽ ምርጫውን አስመልክቶ በትዊተር ገጹ ትኩረት ሳቢ ሲል ጽፎበታል። «ለለንደኑ ውድድር የኢትዮጵያ ቡድን ምርጫ አጓጊ ነው» ሲል ጽሑፉን ያንደረደረው ኤልሻዳይ፦ ገንዘቤ ዲባባና አልማዝ አያና በሁለት ዘርፍ እንደተመረጡ፤ ቀነኒሳ በቀለ በምርጫው አለመካተቱ እንዲሁም ሞሐመድ ዓማን መመረጡን አስነብቧል። 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የለንደን ማራቶን ተሳታፊ አትሌቶችን ለመመረጥ የሚጠቀምበትን መስፈርት ቀደም ሲል አለማስታወቁ በብዙዎች ዘንድ ግርታን ፈጥሮ ነበር። አንዳንዶች የምርጫ መስፈርቱ ቀድሞ ይፋ አለመሆኑ ለተበላሸ አሠራር ያጋልጣል ሲሉም ስጋታቸውን አሰምተው ነበር።

አትሌ ጫላ ባዩ  አራራት ሆቴል አሰልጣኙን በድንጋይ ደብድቦ ተሰወረ መባሉን አስመልክቶ ሠናይትጥበቡ በፌስቡክ ገጿ እንዲህ ብላለች። «እኔ ያልገባኝ በአራራት ጫካ በኩል ሎንደን ቅርብ ነው እንዴ?»

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች