የባህር ስደተኞችን የመታደጉ ጥረትና ፈተናው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 11.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የባህር ስደተኞችን የመታደጉ ጥረትና ፈተናው

በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አውሮፓ የሚጎርፈው ስደተኛ ቁጥር ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ እያሻቀበ ነው ። ማዕበሉ ጋብ በሚልበት ለጉዞ አመቺ በሆነው በዚህ ወቅት ላይ በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱ የተለመደ ነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:01
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:01 ደቂቃ

የባህር ስደተኞች

በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አውሮፓ የሚጎርፈው ስደተኛ ቁጥር ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ እያሻቀበ ነው ። ማዕበሉ ጋብ በሚልበት ለጉዞ አመቺ በሆነው በዚህ ወቅት ላይ በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱ የተለመደ ነው ። ሆኖም ባለፉት 7 ና 8 ወራት በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አውሮፓ የመጡት ስደተኞች ቁጥር ግን ከቀደሙት ጊዜያት ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፈተኛ ሆኖ ተገኝቷል ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCRእንዳስታወቀው ባለፉት 7 ወራት በዚህ መንገድ ወደ አውሮፓ የደረሱት ስደተኞች ቁጥር 224 ሺህ ገደማ ይሆናል ። እነዚህ እድል ቀንቷቸው በህይወት አውሮፓ የገቡት ሲሆኑ በዚሁ ጊዜ አውሮጳ ለመድረስ አልመው የውሐ ሲሳይ ሆነው የቀሩት ደግሞ ከ2100 ይበልጣሉ ። ይህም ባለፈው ረቡዕ በሜዴትራንያን ባህር ላይ ስትጓዝ ከሰጠመችው ጀልባ ውስጥ የነበሩና ሳይሞቱ እንዳልቀረ የተገመተ 200 ሰዎችን ሳይጨምር ነው ።ይህችው ጀልባዋ ካሳፈረቻቸው 700 እንደሆኑ ከተገመቱ ሰዎች መካከል የ373ቱን ህይወት ማትረፍ ተችሏል ። 25 ሰዎችመሞታቸዉሲረጋገጥ የተቀሩትን በህይወት የማግኘቱ ተስፋ ተሟጧል ። በወቅቱ ስደተኞቹን ከታደጉት መካከል የድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን መርከብ አንዱ ነው ። የድርጅቱ የጀርመን ቅርንጫፍ ሃላፊ ፍሎርያን ቬስትፋል ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ከመስጠም ለሚታደጋቸው ስደተኞች «ዲግኒቲ አንድ» በተባለችው በዚህች መርከብ ላይ የህክምና እርዳታዎች ይሰጣል ።

«መርከቧ ቢያንስ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ የሚሰጡ ሰዎችና ለዚሁ አስፈላጊ የሆኑ የህክምና መሣሪያዎች አሏት ።ለምሳሌ አብዛኛዎቹ ስደተኞች ሰውነታቸው በከፍተኛ የውሐ እጥረት ተጠቅቷል ።ለበርካታ ጊዜያት ውሐ ሳይጠጡ መርከብ ላይ እንደመቆየታቸው የውሐ ጥም አንድዷቸዋል ። ቆስለው የሚመጡትን ልናክማቸው እንችላለን ። አደገኛው ጉዞ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ የጣላቸውን ስደተኞችም ለመርዳት እንሞክራለን ። መሠረታዊ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ደግሞ መሪት ላይ ሲደርሱ ነው መታከም ያለባቸው ። ሆኖም በተቻለን መጠን ማድረግ የምንችለውን የህክምና እርዳታመርከባችን ላይ እንሰጣለን ። »

አነዚህን ተግባራት የሚያከናውኑ ሁለት ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን መርከቦች በሜዲቴራንያን ባህር ላይ ይገኛሉ ። ቡድኑ በሌላ ሶስተኛ መርከብ መንግስታዊ ካልሆነ ተመሳሳይ እርዳታ ከሚሰጥ አንድ የማልታ ድርጅት ጋርም ይሰራል ። ቬስትፋል እንደሚሉት በዚህ ግብረ ሰናይ ሥራ የብዙዎችን ህይወት ማትረፍ ተችሏል ።

«ከግንቦት መጀመሪያ ወዲህ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን በሜዴቴራንያን ባህር ከመስጠም አድነናል።ወይም ደግሞ ከተሳፈሩባቸው ጀልባዎች ወስደን ኢጣልያ በህይወት እንዲደርሱ አድርገናል።»

በዚሁ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ግሪክም በርካታ የባህር ስደተኞችን ታድጋለች ። የግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች በምሥራቃዊ የግሪክ ደሴቶች ውስጥ ካለፈው አርብ እስከ ትናንት ማለዳ ድረስ ባካሄዷቸው 60 የፍለጋና የነፍስ አድን ዘመቻዎች ከ 1400 በላይ ስደተኞችን መታደግ ችለዋል ። የስደተኞቹን ህይወት ማትረፍ የተቻለው አሰሳዎቹ የተካሄደባቸው፤ ሌስቦስ ክዮስ ሳሞስ አጋቶኒሲ እና ኮስ ከተባሉት የግሪክ ደሴቶች ነው ።በባህር ወደ ግሪክ ከሚመጡት በ10 ሺህዎች ከሚቆጠሩት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ከሶሪያና ከአፍጋኒስታኑ ጦርነት ና ግጭት ሸሽተው በቱርክ በኩል ወደ አቃራቢዎቹ የግሪክ ደሴቶች በአነስተኛ ጀልባ የሚሰደዱ ናቸው ። ከነዚህ ስደተኞችም አብዛኛዎቹ ከሰሜን ግሪክ በእግር ወደ ባልካን አገራት ይጓዛሉ ወይም ደግሞ በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ ኢጣልያ ያቀናሉ ።በሶስቱ ቀናት ግሪክ ከገቡት ሰደተኞች መካከል ሙክታር የተባለው ሶማሊያዊ ስደተኛ ይገኝበታል ።የሙክታር ዓላማ ኖርዌይ የሚኖሩት ቤተሰቦቹ ጋ መሄድ ነው ። ከተለያዩ 20 ዓመታት

ተቆጥረዋል ። ባለፉት 7 ወራት በጀልባ ግሪክ ከገቡት 124 ሺህ ስደተኞች ሙክታር አንዱ ነው ። የግሪክ ባለሥልጣናት እንዳሰሉት በጎርጎሮሳዊው 2015 ግሪክ የገባው ስደተኛ ቁጥር አምና በዚሁ ጊዜ ወደ ሃገሪቱ ከመጣው ስደተኛ በበ750 ፐርሰንት ጨምሯል ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR እንዳስታወቀው ባለፈው ሐምሌ ብቻ 50 ሺህ ስደተኞች ግሪክ ገብተዋል ። ከመካከላቸው 70 ከመቶው ከሶሪያ ነው የመጡት ። ስደተኞች በብዛት የሚጎርፉት ሊስቦስ ክዮስ ኮስ ሳሞስና ሌሮስ ወደተባሉት የግሪክ ደሴቶች ነው ። በአሁኑ ጊዜ በከፋ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው ግሪክ ስደተኞችን የማስተናገድ አቅሟ ተዳክሟል ። መንግሥት ባለፈው የካቲት ፣ዋና ከተማዋ አቴንስ የሚገኝ አንድ ትልቅ የስደተኞች መቀበያ ከዘጋ በኋላ ስደተኞች በህዝብ መናፈሻ ስፍራዎች ውስጥ በድንኳኖች ለመጠለል ተገደዋል ።አሁን ደግሞ ማዕከላዊ አቴንስ ውስጥ አዲስ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል እየተገነባ ነው ። ወደ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ስደተኞችን የመታደግ እንቅስቃሴ ስንመለስ ድርጅቱ ከሜዲቴራንያን ባህር ላይ የሚታደጋቸውን ስደተኖች ኢጣልያ ካደረሰ በኋላም እርዳታ መስጠቱን እንደማያቆም ቬስትፋል ተንግረዋል ።

«በርግጥ ስደተኞቹን የመንከባከብ ዋነኛው ሃላፊነት የኢጣልያ ባለሥልጣናት ነው ። ሆኖም እኛ እዚያ ስለ ምንንቀሳቀስ በተለይ በሲሲሊው የፖሳሎ የስደተኞች የመጀመሪያ ማረፊያ የህክምና እርዳታ እንሰጣቸዋለን ።ሲሲሊ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ለሚቆዩት ደግሞ የስነ ልቡና ሕክምና እንሰጣለን ።»

ቬስትፋል እንደሚሉት እነዚህ ሰዎች በሃገራቸው ያሳለፉት መከራ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ከሸሹ በኋላ በጉዞ ላይ የገጠሟቸው

አስቸጋሪ ሁኔታዎች መዘንጋት የለባቸውም ።»

በብዛት ከሶርያ፤ከኤርትራ፤ከሱዳን፤ከሶማልያእናከባንግላዴሽከሚመጡት ከነዚሁ ስደተኞች መካከል በሃገራቸው ከደረሰባቸው እንግልት በተጨማሪ በአደገኛው ጉዞ ሰበብ በጭንቀት ና ተያያዥ የጤና ችግሮች የሚሰቃዩም አሉ።ስደተኞች እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች ውስጥ እንዳይወድቁ በመስኩ የተሰማሩ የእርዳታ ድርጅቶች ከሚያቀርቧቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ውስጥ ስደተኞች በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮጳ የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት የሚለው አንዱ ነው ። ይህን ሃሳብ ከሚሰነዝሩት ውስጥ የድንበር የለሽ የሐኪሞች ድርጅት የጀርመን ቅርንጫፍ ሃላፊ ፍሎርያን ቬስትፋል አንዱ ናቸው

«የአውሮፓ ህብረትና ጀርመንን ጨምሮ አባል ሃገራቱ ስደተኞችን የሚመለከተውን መርሃቸውን መቀየር እንዳለባቸው ግልፅ ሊሆን ይገባል ።ከሃገር የሚሸሹ ሰዎች በህጋዊ ና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ወደ አውሮፓ ገብተው ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው።ይህ ተግባራዊ ከሆነ ህገወጥ አሻጋሪዎች ከሥራ ውጭ ያደርጋል ። በአውሮፓ ፖሊስ ምክንያት ሰዎች ለዚህን መሰሉ የእብደት ጉዞ በመዳረግ ለአደጋ ይጋለጣሉ ። ምክንያቱም ስደተኞቹ በአስተማማኝና በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮፓ እንዳይሰደዱ መንገዱ ተዘግቶባቸዋል ። ብዙዎቹ ወደ አውሮፓ የሚገቡበትበት ሌላ አማራጭ መንገድ በማጣታቸው ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ለማጋለጥ ይገደዳሉ ። »

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCRም የአውሮጳ መንግሥታት የስደተኞችን ሞት ለማስረቀትአማራጭ መፍትሄዎችን እንዲፈልጉ ጠይቋል።የድርጅቱ ቃልአቀባይ ባርባራ ሞሊናርዮ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት መንግሥታት ስደተኞች በህጋዊ መንገድ የሚመጡበትን መንገድ እንዲያስተካክሉ ነው ሃሳብ ያቀረቡት

«በሜዲቴራንያን ባህር የሚደርስው የስደተኞች ቀውስ ነው ። ትልቁ የሚታየው ቀውስ ሰዎች እየሞቱ በዚህ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመምጣት መገደዳቸው ነው።አስፈላጊ የሆነውና UNHCR ም የሚጠይቀው የአውሮጳ መንግሥትት ወደ አውሮፓ ለሚሸሹ ስደተኞች አማራጭ መፍትሄዎችን እንዲያቀርቡ ነው ። እነዚህም በዚህ ዓይነት መንገድ እንዳይመጡ የሚያደርጋቸውን ሰብዓዊ ቪዛን መስጠት ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚሄዱበትን መንገድ ማመቻቸት የመሳሰሉ አማራጮች ናቸው ።ወደዚህ ከሚመጡት ስደተኞች አብዛኛዎቹ አውሮጳ ህብረት ውስጥ በህጋዊ መንገድ የሚኖሩ ዘመዶች አሏቸው ።»

ለአውሮፓ መንግሥታት ይህን መሰሉ ጥሪ ተደጋግሞ በሚቀርብበት በዚህ ወቅት ላይ የአውሮፓ ህብረት በስደተኞች ለተጨናነቁ የህብረቱ አባል ሃገራት 2.4 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥ አስታውቋል ። ከዚሁ ገንዘብ ኢጣልያ 558 ሚሊዮን ዩሮ ፣ግሪክ 478 ዩሮ ስፓኝ 521.8 ሚሊዮን ዩሮ ስዊድን 154 ሚሊዮን ዩሮ በእርዳታ ይሰጣቸዋል ። በተጨማሪም ሃንጋሪ ቡልጋርያ ቆጵሮስ ኦስትርያ ኤስቶንያ ፊንላንድ አይርላንድ ሊትዌንያ ሉክስምቡርግ ማልታፖላንድ ፖርቱጋል ሮማንያ ስሎቫክያና ስሎቬንያም ወደ ሃገራቸው የሚጎርፉ ስደተኞችን መቋቋም የሚያስችላቸው ገንዘብ ተመድቦላቸዋል ። የገንዘብ እርዳታው በዋነኝነት ኢጣልያንና ግሪክን በመሳሰሉ ሃገራት ለስደተኖች መቀበያ ማዕከላት ግንባታ ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርበው እንዲኖሩ ለሚረዱዋቸው መርሃ ግብሮች ነው የሚውሉት ።ከዚህ ሌላ ገንዘቡ ሃገራቱ ድንበሮቻቸውን በተሻለ መንገድ እንዲጠብቁ ና ጥገኝነት የነፈጓቸውን ስደተኞች ለሚያባርርሩባቸው መርሃ ግብር ማጠናከሪያ የሚውል ነው ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic