የባህር ላይ ውንብድና እና ወጣት ሶማሊያውያን | ባህል | DW | 17.08.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የባህር ላይ ውንብድና እና ወጣት ሶማሊያውያን

ባለፉት ዓመታት በሶማሊያ የባህር ላይ ውንብድና ምን ያህል እንደተስፋፋ እና ገንዘብ ማግኛ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። በዚህ ተግባር የተሰማሩት አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው።

ቤንያሚን ተድላ ሄከር ሶማሊያ ውስጥ ወጣቶችን ስለሳበው የባህር ላይ ውንብድና ጥናት አካሂዷል። የእንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ያጠናው ቤንያሚን በጀርመን ቦን ዮንቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ 2ኛ ዲግሪውን አግንቷል። ስለሶማሊያ ወጣቶች እና የባህር ላይ ውንብድና የሚያውቀውን አካፍሎናል።

በትናንሽ ፈጣን ጀልባዎች ላይ ሆነው ትላልቅ መርከቦችን በቁጥጥር ስር ስለሚያውሉት የባህር ላይ ወንበዴዎች ሲወራ፤ በሀሳብ ወደ ሶማሊያ እንሄዳለን። በርግጥም ቢያንስ ያለፉት አመታትን ብንመለከት የባህር ላይ ውንብድና በመፈፀም ደጋግሞ ስማቸው የተጠራው ሶማሊያውያን ናቸው። ይህን ተግባር ከሚፈጽሙት ውስጥ ደግሞ ወጣቶች ይበዙበታል። ለምን እነዚህ ሶማሊያውያን ወጣቶች በባህር ላይ ውንብድና ተግባር ተሳቡ?

In this photo taken Sunday, April 3, 2011 and released by Dutch defense ministry Monday April 4, 2011, armed Dutch marines on board of two Dutch navy motorboats capture suspected pirates in a small skiff off the coast of Somalia in an operation to free it from pirates. The Dutch defense ministry says its marines have killed two pirates and captured 16. (Foto: Dutch Defense Ministry/HO/AP/dapd)

የባህር ላይ ወንበዴዎች

« የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ የባህር ላይ ውንብድና የሚታየው፤ ካለፍቃድ አሳ ከሚያጠምዱ ሰዎች ባህረ ሰላጤውን ለማዳን ከሚደረግ ጥበቃ ጋ በተያያዘ ነበር። ይህንንም አስተያየት አልፎ አልፎ አሁንም ይጠቀሙታል። ይሁንና በርካታ ወጣት የባህር ላይ ወንበዴዎች ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ ስራን ሲያስቡ ከውንብድናው ጋ እንደሚያያይዙ መናገር ይቻላል። ምክንያቱም በባህር ላይ ውንብድና ከምንም ተነስቶ ባንድ ጊዜ 70 እና 80 ሺ ዶላር ማግኘት ይቻላል። ይህ ብዙ ገንዘብ ነው። ብዙዎቹ ወንበዴዎች ደግሞ ስራ የላቸው። ስለዚህ ይህ በአጭር ጊዜ ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችል ዘዴ ነው።»

የባህር ላይ ወንበዴዎቹ የተለያየ ስልት እየተጠቀሙ በትናንሽ ጀልባ ትልቅ መርከብን በቁጥጥር ስር አውለው የካሳ ክፍያ እንደሚጠየቁ ይሰማል። በዚህ ተግባር የተሰማሩ ወጣቶች ተይዘው በህግ በሚጠየቁበት አጋጣሚ የእድሜያቸው ነገር አነጋጋሪ መሆኑን ነው ቤንያሚን የሚገልፀው።

« አዎ ይህ አንዱ አነጋጋሪ ርዕስ ነበር ። በአውሮፓ ፍ/ቤቶች የባህር ላይ ወንበደዎችን በወጣቶች የወንጀል መቅጫ ህግ መቅጣቱን በተመለከተ አስቸጋሪ አድርጎታል። እንዳገኘኋቸው መረጃዎች ከሆነ ወንበዴዎቹ በ 15 እና 25 እድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ።

Pro-Palästina Demonstration der Al-Shabaab Miliz in Somalia

የአሸባብ ታጣቂዎች በሶማሊያ

ለባህር ውንብድና የተጋለጡ በአመት እስከ 20 000 የሚደርሱ የንግድ መርከኖች በአፍሪቃ ቀንድ ባህረ ሰላጤዎች ይጓጓዛሉ። ይህንን መንገድ መቀየር ተጨማሪ 3 ሳምንት ያህል እና ብዙ ገንዘብ እንደሚያስወጣ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። የአለም አቀፉ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት መስሪያ ቤት የመረጃ ማዕከል እንዳስታወቀው ባለፈው አመት ብቻ 125 የባህር ላይ ውንድናን በአፍሪቃ ቀንድ ተፈጽሟል።

ባልተረጋጋችው ሶማሊያ የሚኖሩት ወጣቶች እንደ ትርፋማ ስራ ሆን ብለው የያዙት የባህር ላይ ውንብድና ብቻ አይደለም። የሙስልሙ አማፂ ቡድን አሸባብ ሌላኛው አማራጭ ነው። «እድሉ አለ። እዚጋ መለየት ይገባል። በወደብ አካባቢ የባህር ላይ ወንበዴዎች ናቸው። በከተማ አካባቢ ደግሞ አሸባቦች ናቸው። አንድ ዘገባ ላይ ያገኘሁት ነበር። አንድ የአሸባብ ተዋጊ እስከ 350 ዶላር በወር የሚያገኝበት ሁኔታ አለ። ይህ ለአንድ ሱማሊያዊ ብዙ ገንዘብ ነው። በባህር ላይ ውንብድና በርግጥ ብዙ ገንዘብ ማግኘት ይቻላል። ለአደጋ መጋለጡም የዛን ያህል ነው።»

በሶማሊያ የተረጋጋ መንግስት ስለሌለ አንዳንድ ወንበዴዎች ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ እየሄዱ መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈሱ ይነገራል። ይሁንና በአገራቸው ውስጥም ገንዘቡን በስራ ላይ የሚያውሉ አልጠፉም።

«በቅርብ ጊዜ የአፍሪቃ ህብረት ያወጣውን ዘገባ አንብቤ ነበር። አንዳንድ ከተሞች ለምሳሌ ጋሮቬ ፑትላንድ ውስጥ ከዚህ የባህር ላይ ውንብድና ምን ያህል አትራፊ እንደሆኑ ይታያል። ቤቶች ተሰርተዋል። መንገዶች ተገንብተዋል። እና ህብረተሰቡ በከፊል ከዚህ የተጠቀመ ይመስላል። ይሁንና ሌሎች ዘገባዎችም አሉ ህብረተሰቡ ከባህር ላይ ውንብድናው ምንም ትርፍ እንደማያገኙ የሚናገሩበት። ርግጥ የሆነ ትንሽም አስቂኝ እውነታዎች አሉ። ለምሳሌ ሰዎች ሲታገቱ ለነዚህ ሰዎች ምግብ የሚያበስሉ የምግብ አቅራቢዎች አሉ። ይህ በጎ ተግባር ሆኖ አይደለም። ይሁንና ሌሎች የተለያዩ ስራዎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ። »

የወጣት ሶማሊያውያን እጣ ፈንታ የሆነው የባህር ላይ ውንብድና በከፊል ህብረተሰቡን ጠቀመ ቢባልም የባህር ላይ ወንበዴዎቹ በደህንነት አስከባሪዎች ብቻ ሳይሆን ተፈላጊነታቸው፤ ትዳር ለመመስረት በተዘጋጁ ልዳገረዶችም ጭምር ነው። በዚህ ተግባር የተሰማራ ካልሆነ ሌላ ሰው ማግባት አልፈልግም የሚሉም አልጠፉም። ብዙውን ጊዜ ስለ የባህር ላይ ውንብድና ሲነገር ተሳታፊዎቹ ወንዶች መሆናቸው ነው የሚሰማው። ሴቶቹስ የሉበትም ይሆን? ቤንያሚን

« ስለ ሴት የባህር ላይ ወንበዴዎች እስካሁን አልሰማሁም። ሴቶቹ ቀደም ሲል እንዳልኩት ምግብ በማቅረብ በመሳሰሉ መንገዶች ባሎቻቸውን የሚተባበሩ ይመስለኛል። ወንበዴዎቹን የሚያስስ አካል ከመጣ ሴቶቹ እነሱን በመደበቅ የሚተባበሩ ይመስለኛል። በተረፈ ግን ስለ ሴቶቹ ሚና ከዚህ የበለጠ አልሰማሁም።»

የአሸባብ ቡድንን የተቀላቀሉትም ይሁን በባህር ውንብድና የተሰማሩት ፤ ጠመንጃ ከእጃቸው አይለይም። ለመሆኑ ስልጠና ያገኛሉ? ከሆነስ ከማን?

Karte versuchter und erfolgter Piratenübergriffe im Golf von Aden im Jahr 2008 --- DW-Grafik: Peter Steinmetz 2009_06_04-horn_afrika-v2.jpg

በአደን ባህረ ሰላጤ በባህር ላይ የሚጠቁ መርከቦች እኢአ በ2008

«2008 የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ያወጣው አንድ ዘገባ ነበር። የባህር ላይ ውንብድና ወጣቶች የሚሰለጥኑበት አንድ ጣቢያ እንዳለ ነበር የጠቆመው። በዚህ ጣቢያ ውስጥ የሚገርመው ነገር የአሸባብ ታጣቂዎችም ይሰለጥኑ ነበር። ይህ አንዳንድ ምሁሮች እንደሚሉት አሸባብ እና የባህር ላይ ወንበዴዎቹ አብረው እንደሚሰሩ የሚያመላክት ነው። በርግጥ ይህ በአንዳንድ አካባቢዎች ታይቷል። ይህ የሚያመላክተው አንዳንድ የባህር ላይ ወንበዴዎች ስልጠና እንደሚያገኙ ነው። ሆኖም አንዳንድዎች መሳሪያ ይዘው ወደ ባህር በመሄድ የዕድላቸውን ይሞክራሉ ብዬ እገምታለሁ። ስለዚህ የሰለጠኑ እና ያልሰጠኑ የባህር ላይ ወንበዴዎች ናቸው። »

በነዚህ ሁለት በተደራጁ ወንጀሎች የተሰማሩት ወጣቶች በአጭር ጊዜ ብዙ ገንዘብ የሚያገኙበት አጋጣሚ ስላለ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ለወጣቱ ስራ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ሙከራ አዳጋች እንዳደረገው ቤንያሚን ያስረዳል። በአንድ በኩል ለሶማሊያውያኑ ከወንጀል የራቀ ስራ መፈለጉ ችግር ሆኖ ሳለ፤ ሌላው ደግሞ በአካባቢው የሚገኙትን ባህረ ሰላጤዎች ከወንበዴዎች ነፃ ማድረግ ነው።

« አዎ ችግሮቹ እነሱ ናቸው። በመጀመሪያ የአደን ባህረ ሰላጤ ውሃ ነፃ እንዲሆን መጣር ነው ያለው ፍላጎት ሌሎች ርምጃዎች በርግጥ ቀጣይ እና ብዙ ትግል የሚጠይቁ ናቸው። ያልተረጋጋ ብቻ ሳይሆን አደገኛም በሆነ አገር ላይ የሚካሄድ ርምጃ ነው። የበለጠ የስራ እድል መፍጠር ዋና አላማው መሆን አለበት። እንዴት መስራት እንደሚቻል ስራ ላይ የዋሉ እና በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያሉ ብዙ መንገዶች አሉ። በመጀመሪያ ግን መሳሪያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱትን መታገል ያስፈልጋል። ያም ማለት ትጥቅ ማስፈታት ያስፈልጋል።»

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic