የባህል መድረክ-ጀርመን | ባህል | DW | 16.07.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የባህል መድረክ-ጀርመን

የለቱ የባህል መድረክ ጥንቅራችን የጀርመን የባህል ደረ-ገጾች ያነስዋቸዉን ርዕሶች ያስቃኛል።

default

Goethe-Institut የጀርመኑ የባህል ማዕከል ከተመሰረተ ዘንድሮ ስድሳኛ አመት መሙላቱ ሌላዉ የጀርመን የተለያዩ ባህል ድረ-ገጾች ካተኮሮባቸዉ ርዕሶች መካከል አንዱ ነዉ። ከሁለተኛ አለም ጦርነት በኋላ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 1951 አ.ም የጎተ ማህበር በሚል የተቋቋመዉ ድርጅት የጀርመንኛ ቋንቋን በዉጭ አገሮች ለማስፋፋት ታቅዶ ነበር ስራዉን የጀመረዉ። የጀርመንኛ ቋንቋ ለማስፋፋት የተቋቋመዉ ማህበር በአሁኑ ግዜ የጀርመን የባህል ማዕከል በሚል መጠርያዉ በአለም ዙርያ በሚገኙ አገሮች በሰፊ መድረክ የተለያዩ ባህሎች ልዉዉጥ የሚደረግበት መድረክ ሆንዋል። በአስራ ስምንተኛዉ ክፍለ ዘመን ታዋቂ በነበረዉ ጀርመናዊ ገጣሚ በዮሃን ዎልፍ ጋንንግ ፎን ጎተ የተሰየመዉ የጀርመኑ የባህል ማዕከል በሙኒክ ከተማ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 1951 አ.ም የመጀመርያዉን ቢሮዉ ከከፈተ በኋላ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 1952 አ.ም የመጀመርያዉ የጀርመን ባህል ማዕከል በአቴንስ ከተማ ነበር የተከፈተዉ። አስር አመት ሳይቆይ በዝያን ግዜዋ ምዕራብ ጀርመን ዉስጥ አስራ ሰባት ቅርንጫፍ መስራ ቤቶች እና በተለያዩ አገሮች ሃምሳ አራት የጀርመን የባህል ልዉዉጥ ማዕከል ተከፍቶአል። በጎርጎረሳዉያኑ 1980 እና 90 ዎች ላይ የጀርመን የባህል ማዕከል በዉጭ አገሮች የጀርመንን ገጽታ በማንጸባረቅ የያዘዉን ራዕዩን በማስፋት የምስራቅ ጀርመን እና የምዕራብ ጀርመን አንድነት በማስመልከት አዲሲትዋን ጀርመን ማስተዋወቁን ቀጠለ። ይህም በምስራቅ እና በምዕራብ ተከፍሎ ለነበረዉ አለም አንድ የባህል የፖለቲካ መወያያ ሃሳብ መቀያየርያ ማዕከላዊ ቦታን ከፍቶለታል። በዚህም ነዉ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጠጠር እስከ 1994 አ.ም ድረስ በሃንጋሪ በሩስያ በቼክ ሪፐብሊክ፣ በፖላንድ፣ በቤላሩስያ፣ ሌትላንድ በስሎቫኪያ በዩክሪን በጆርጂያ እና በካዛኪስታን የጀርመን የባህል ማእከል ጎተ ኢኒንቲቲዉት ተከፍቶ የጀርመን ገጽታን በማንጸባረቅ ጀርመን ከምስራቅ አዉሮጻ አገሮችም ጋር የባህል ልዉዉጥ ግንኙነት በተጥናከረ መልኩ የተጀመረዉ።
ዉጥረት በሰፈነበት በቱርክ እና በግሪክ መካከል በምትገኘዉ በቆጵሮስ ኒኮስያ ከተማ ላይ አንድ ወር ግድም አካባቢ የተከፈተዉ የጀርመን የባህል ማዕከል ጥሩ የባህል የፖለቲካ መወያያ ቦታ ሊሆን ይችላል ይላሉ ከሶስት አመት ጀምሮ የጎተ ተቋም ሃላፊ የሆኑት ክላዉስ ዲተር ሌማን ይገልጻሉ።
«ለዚህም ነዉ በመካከለኛዉ አዉሮጻ ለሁለት በተከፈለችዉ ከተማ መካከል የጎተ የባህል ማዕከል መከፈቱ አንድ ምልክት ነዉ። ምናልባትም የአዉሮጻ ኤንባሲ ይሆናል»

60 Jahre Goethe-Institut Flash-Galerieበኒኮስያ ያለዉ የባህል ማዕከል የቋንቋ መማርያ ቦታ ብቻ ሳይሆን ባህልን መተዋወቅያ መግባባት ያልተደረሰባቸዉን የፖለቲካ ጉዳዮች መወያያ ቦታም ይሆናል። በኢትዮጽያም አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚገኘዉ የጀርመን የባህል ማዕከል ከተቋቋመ ሃምሳኛ አመቱን የሚይዝ ሲሆን የምስረታዉን ሃምሳኛ አመት በማስመልከት የዛሪ ዘጠኝ ወር ግድም የተለያዩ ዝግጅቶችን ያቀፈ መድረክ እንደሚዘጋጅም ማዕከሉ አስታዉቆአል። በአሁኑ ወቅት በአለም ዙርያ የጀርመን ገጽታ የሚያንጸባርቁ የተለያዩ አገር ህዝቦች የባህል ልዉዉጥ እና ዉይይት የሚያደርጉበት 150 የባህል ማዕከል ይገኛል።

ሰሞኑን በጀርመን መገናኛ ብዙሃን እና የባህል አምደ መረብ ካሰፈሩዋቸዉ ባህል ነክ ዜናዎች መካከል ባለፈዉ ሳምንት አርብ እዚህ የዶቸ ቬለ የራድዮ ጣብያ በአመት አንድ ግዜ በጋ ወር መጀመርያ ላይ የሚያዘጋጀዉን ግብዣ በማስመልከት የቀረበዉ ነዉ። Sommerfest በሚል በዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ በአመት አንድ ግዜ የሚዘጋጀዉ ድግስ መስራ ቤቱ ሰራተኞቹን በማሰባሰብ የተለያዩዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች ይካሄዱበታል። የዘንድሮዉ ዝግጅት እዚሁ ራድዮ ጣብያዉ ቅጽር ግቢ ባለዉ ሰፊ አረንጓዴ ሳር በለበሰ ሜዳ ላይ፣ መድረክ በመዘርጋት የዶቼ ቬለ ጣብያ ዋና አስተዳሪ ሪክ ቤተርማን እንኳን ለአመት አደረሰን፣ በማለት ንግግራቸዉን አስምተዉ የዶቼ-ቬለ ሰራተኞች በመቀጠል ሚዛናዊ ዘገባቸዉን ከአዉሮጻ እንብርት ከጀርመን ከዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ ወደ ተለያዩ የአለም ክፍሎች ማሰራጨታቸዉን እንዲቀጥሉ በመንገር የምስጋና ንግግር በማድረግ የግብዣዉን መጀመር አብስረዋል። በዚሁ ዶቼ ቬለ ባለፈዉ አርብ በጠራዉ ድግስ ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች የተካሄዱ ሲሆን አንድ የጃዝ ሙዚቃ ቡድን እድምተኞቹን ሲያዝናና አምሽቶአል። ከተጋባዦች መካከል በቦን ከተማ የሚገኙ የተለያዩ አገር ኤንባሲ ሰራተኞች የዶቼ ቬለ ሰራተኛ ቤተሰቦች በተለይም ህጻናቶች ይገኙበታል። ለህጻናቱ በተዘጋጀዉ ልዩ የመጫወቻ መድረክ፣ የስዕል መሳል ዉድድር ተካሂዶአል። በዚህ አይነት የዶቸ ቬለ ሰራተኞች ታጋባዥ እንግዶች መዝናናት ላይ ሳሉ ነበር በድንገት ሳይታሰብ የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጊዶ ቬስተር ቬለ በመዝናናት ባለዉ ህዝብ መካከል አልፈዉ መድረክ ላይ በመዉጣት ንግግር የጀመሩት

Guido Westerwelle Pressekonferenz Ägypten

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ«መልካም ምኞቴን መግለጽ እወዳለሁ! ሌላዉ ምስጋናዪ ለዶቸ ቬለ ተጠሪ ለኤሪክ ቤተር ማን ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ እየሰራችሁ ላላችሁት የዶቸ-ቬለ ሰራተኞች ለምታበረክቱት ግሩም ስራችሁ ላመሰግን እወዳለሁ። እየተገበራችሁት ያለዉ ስራ እዉቅና የሚሰጠዉ፣ በጣም አስፈላጊ ግንኙነት ያለበትና ለፊደራል ጀርመን እጅግ ጥሩ መታወቅያ በመሆኑ ሁላችሁንም ማለት በዶቼ ቬለ ጣብያ ስር በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወራችሁ ለምትሰሩት ጀርመኖችም ሆነ ከተለያዩ አለም ክፍሎች መጣችሁ እዚህ ለምትገኙት ጋዜጠኞች በሙሉ ከልብ ምስጋናዪን ማቅረብ እወዳለሁ»

በሌላ በኩል የዶቼ ቬለ ምርጥ የእግር ኳስ ቡድኖች ግጥምያ ያካሄዱ ሲሆን የቦሊንግ የቲኒስ ጨዋታ ዉድድር ሌላዉ የመዝናኛ የድግሱን አድማቂ ጨዋታ ነበር። በስርጭት ጣብያዉ ባለዉ ትልቅ አዳራሽ ዉስጥ ከተለያየ የቋንቋ ስርጭት ክፍል የተዉጣጡት የዶቼ ቬለ ጋዜጠኞች የቲያትር ቡድን ያዘጋጀዉን የሃምሳ ደቂቃ ትያትር በግብዣ መልክ አቅርቦአል። በዚህ የግብዣ ስነ-ስርአት ላይ ሰሞኑን በጀርመን በተከሰተዉ ሙቀት ሰበብ፣ ያለዉን ዉሃ ጥማት «ተሽ» ለማድረግም ከቢራ ሌላ ልዪ ልዪ ቀጥቃዛ መጠጦች ቀርበዉ ነበር። ዶቼ ቬለ

የቀድሞዉ የጀርመን መራሄ መንግስት ሄልሙት ኮል ባለቤት የህይወት ታሪክን የያዘዉ አዲስ መጽሃፍ ሰሞኑን በጀርመን የመጽሃፍ አለም ለሽያጭ ቀርቦ በሽያጭ ቀዳሚዉን ቦታ መያዙ የጀርመን የባህል ድረ- ግጽም ርእሱ አድርጎት ሰንብቶአል ።

Buchcover Die Frau an seiner Seite. Leben und Leiden der Hannelore Kohl


ጀርመንን ለአስራ ስድስት አመታት በመራሄ መንግስትነት የመሩት የሄልሞት ኮል ባለቤት የዛሪ አስር አመት ነዉ በመኖርያ ቤታቸዉ የራሳቸዉን ህይወት ያጠፉት። ዛሪ ከአስር አመት በኋላ የሳቸዉን የህይወት ታሪክ ያዘለዉ መጽሃፍ አንባቢያን እጅ ሲገባ ቤተሰቦቻቸዉ በመጸሃፉ ይዘት ባይደሰቱም ለምን እራሳቸዉን አጥፉ የሚለዉ ጥያቄ በህዝብ ጭንቅላት እንደ አዲስ መጉላሉቱ አልቀረም። በርካታ ጀርመናዉያን የቀድሞዋ የጀርመን መራሄ መንግስት ባለቤት ሃነሎረ ኮልን የሚያቋቸዉ ምንም እንኳ ጥሩ ቢለብሱም እንብዛም ዘመናዊ በማይባለዉ አለባበሳቸዉ፣ በጸጉር አበጣጠራቸዉ እና በፈገግታቸዉ ነዉ። ሁለቱ ጀርመን ጥምረት ተምሳሌት እና አስራ ስድስት አመት ጀርመንን በመራሄ መንግስትነት የመሩት የሄልሙት ኮል ባለቤት የህይወት ታሪክ ይላል ታዋቂዉ ጀርመናዊ ጋዜጠኛ እና የስነ-ጽሁፍ Heribert Schwan በቅርቡ ለአንባብያን ያቀረቡት መጽሃፍ። መጽሃፉ እዚህ ጀርመን ዉስጥ በገፍ ቢሸጥም የመጽሃፉ ዋና ገጸ-ባሃሪ የሃና ሎረ ሁለት ወንዶች ልጆች ግን ታሪኩ ብዙ እዉነታ አይታይበትም አልያም ጸሃፊዉ በአደባባይ መዉጣት የሌለበትን የቤተሰብ የግል ህይወት በይፋ ማዉጣታቸዉ አላስደሰታቸዉም።
እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር 1933 አ.ም ከሁለተኛዉ ጦርነት በፊት በጀርመን ዛክዘን ግዛት ዉስጥ ደህና ይዞታ ከነበረዉ ቤተሰብ የተወለዱት ሃና ሎረ፣ ኢንጂኔር አባታቸዉ ታታሪ ሰራተኛ በመሆናቸዉ እንደ አ.አ 1934 አ.ም በናዚ አገዛዝ ዘመን በላይ ፕዚግ ከተማ በሚገኝ አንድ የጦር መሳርያ አምራች ድርጅት አስተዳዳሪ ይሆናሉ። ይህንን ስልጣን ያገኙት የናዚ ፓርቲ አባል በመሆናቸዉም ነበር። ከሁለተኛ ጦርነት በኋላ የናዚን አባላት ሲያባርር የነበረዉ የሩስያ ጦር፣ ሃና ሎረ ቤትም በማንኳኳቱ የአስራ ሁለት አመትዋ ሃናሎረ ከእናታቸዉ ጋር የሩስያን ጦር በመሸሽ ወደ ምዕራብ ጀርመን ይሰደዳሉ። ጸሃፊ Heribert Schwan የሃና ሎረን የህይወት ታሪክ ባስቀመጡበት መጸሃፋቸዉ ሃነ ሎረ የአስራ ሁለት አመት ልጅ ሳሉ የሩስያ ወታደሮች አስገድደዉ ከደፈሯቸዉ በኋላ አንድ ሲሚንቶ እንደ ያዘ ከረጢት በመስኮት ዉጥተዉ ወርዉረዋቸዋል። በዚህም ይላሉ ደራሲዉ ሃነ ሎአ ኮል በህይወታቸዉ ዘመን ሁሉ የተከተላቸዉ ከጭንቅላት የማይፋቅ አሰቃቄ ሁኔታ በህይወታቸዉ ዘመን አምቀዉት ቆይተዋል። የሃነ ሎረን የህይወት ታሪክ አቅራቢዉ Heribert Schwan ሃና ሎረ ከዚህ አለም እስከተለዩ ድረስ በርካታ ዉይይቶችን አድርገዋል። ጋዜጠኛዉ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ዉይይት ሃነ ሎረ ይላሉ ጋዜጠኛ ጸሃፊ እንዲሁም ፊልም ቀራጭ መሆኔን ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ፤ የህይወት ታሪካቸዉን ያወሩልኝ በመጽሃፍ መልክ እንዳወጣዉ በመፈለጋቸዉ ነዉ። በሌላ በኩል የሃነ ሎረ ኮል ወንድ ልጅ እናቴ በሁለተኛ ጦርነት ወቅት የደረሰባትን ሁሉ ተርካልኛለች፣ ነገር ግን በግልጽ እንዲወጣ ፍላጎትዋ አልነበራትም፣ ይህ ታሪክ ይፋ ከሚሆን ሞትዋን እንደምትመርጥ አዉቃለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

Hannelore Kohl und Helmut Kohl NO FLASH

የቀድሞዉ የጀርመን መራሄ መንግስት ሄልሙት ኮል እና ባለቤታቸዉ ሃነሎረ ኮል


ጋዜጠኛ Heribert Schwan በ 1990 ዎቹ መጨረሻ የቀድሞዉን የጀርመን መራሄ መንግስት ሄልሙት ኮል የህይወት ታሪክ እና አንዳንድ ትዝታዎች ለመጻፍ ሄልሞት ኮል መኖርያ ቤት በእንግድነት ይመጡ እንደነበር እና በዝያም ሰበብ ከባለቤታቸዉ ከሃነ ሎረ ኮል ጋር ጥሩ ግንኙነት ተፈጥሮ ታሪካቸዉን እንዳወሩላቸዉ ይገልጻሉ። ሃነ ሎረ ኮል እንደ ጎርጎረሳዉያኑ 1993 አ.ም ጀምሮ የብርሃን ጨረር የማይቋቋም የቆዳ በሽታ ስለያዛቸዉ ቀን ከሚዉሉበት ከጨለማ ቤት ዉስጥ ወደ ዉጭ ለሽርሽር የሚወጡት ለሊት ድቅድቅ ባለ ጨለማ ዉስጥ ነበር። ለሊት ሽርሽር በሚወጡበት ግዜም ጋዜጠኛዉ አልተለዪዋቸዉም። የፈረንሳይና እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት ሃነሎረ የአስተርጓሚነት ትምህርትን ተምረዉ፣ በማስተርጎም ስራ ተሰማርተዉ ነበር። እንደ 1960 አ.ም ከሄልሞት ኮል ጋር በትዳር የተሳሰሩት ሃነ ሎረ ኮል የቀድሞዉን የጀርመን መራሄ መንግስት ሰላሳ አመት በትዳር አለም አብረዋቸዉ ቆይተዉ ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል። የዉጭ ቋንቋንም ጠንቅቀዉ በማወቃቸዉ የዝያን ግዜዉ መራሄ መንግስት ከዉጭ መንግስታት ጋር ሲገናኙ እሳቸዉም ሃሳብን ለመቀያየር እንብዛም እክል አልገጥማቸዉም። የጸሃይ ብርሃን ጨረር መቋቋን የማችል የቆዳ በሽታ በመያዛቸዉ በመጨረሻዎቹ አመታት እጅግ ስቃያቸዉ እንዳበዛ ደራሲዉ በመጽሃፉቸዉ አስቀምጠዉታል። እንደ ጎርጎረሳዉያኑ 1991አ.ም ሃነ ሎረ ኮል ለባለቤታቸዉ በጻፉት የስንብት ደብዳቤ ከህመማቸዉ የመዳን ተስፋቸዉ በመመንመኑ ራሳቸዉን ለማጥፋት ዉሳኔ ላይ መድረሳቸዉን በጽሁፍ አስቀምጠዉ አልፈዋል። ደራሲዉ የሃነ ሎረን የህይወት ታሪክ ያኖሩበትን ጽሁፋቸዉን ሲደመድሙ፣ በህጻንነታቸዉ የደረሰባቸዉ አስቃቂ በደል የጭንቅላት ቁስል ሆኖ ህይወታቸዉን በሙሉ እንደተከተላቸዉ እና ለበሽታቸዉ ሁሉ ሰበብ መሆኑን በመግለጽ መጸሃፉን ይደመድማል። መጽሃፉ ሰምወኑን የጀርመን የብዙሃን መገናኛን ለዉይይት የዳረገ፣ አንባብያንን በመጽሃፍ ግዢዉ እሽቅድምድም ያስገባ በመሆኑ የዶቼ ቬለዉ የባህል ድረ-ገጽ በሰፊዉ የዘገገበት ርእስ ነዉ

የሞናኮዉ መስፍን አልቤር ሁለተኛ እና የደቡብ አፍሪቃዊትዋ ታዋቂ የዋና እስፖርተኛ ቻርሌን ባለፈዉ ሰኔ 25 በአለም ዙርያ የሚገኙ ንጉሳዊ በተሰቦች ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ባለንዋዮች ተጋባዥ እንግዶች እና ጋዤጠኞች በተገኙበት የጋብቻ ስነ-ስርአታቸዉን ፈጽመዋል። ሜድተራንያን ዉቅያኖስን ተንተርሳ ፈረስሳይ እና ጣልያንን በማዋሰን መካከለኛዉ አዉሮጻ የምትገኘዉ ሞናኮ በትንሽነትዋ ከቫቲካን ግዛት ቀጥላ ከአለም ትንሽዋ አገር ነች። አገሪትዋ በአለም ሁለተኛዋ ትንሽ አገር ትሁን እንጂ፣ በአለም እጅግ ሃብታም የሆኑ የፊልም ሰራተኞች ፖለቲከኞች፣ እንደዉ ባለጸጎች የሚዝናኑባት የሚኖሩባት እንደሆነም ይነገራል። በሞናኮ ከተማ ለጸጥታ ጥበቃ በየሜትሩ ቪዲዮ ካሜራ ተተክሎ ጥበቃዉ በጣም የተጠናከረ በመሆኑም ሞናኮ ከአለም እጅግ አስተማማኝ እና ጸጥታዉ የተረጋገጠ ስፋራ መሆኑ ይነገርለታል። ሰርጉ ሁለት ቀን ሲቀረዉ በፊት ቻርሊን መሰረግዋን ትታ ጠፍታ ወደ አገርዋ ጠፍታ ልትሄድ ስትል አየር ጣብያ በፖሊስ መያዝዋን አንድ አንድ መገናኛ ብዙሃኖች ቢዘግቡም ዜናዉን ያረጋገጠ ወገን አልነበረም። እንዳ አንዳንድ ምንጮች የሞናኮን መስፍን አልቤር ከደቡብ አፍሪቃዊትዋ ፍቅረኛቸዉ ጋር ሳሉ ከሌላ ሁለት ሴቶች ጋር ሳይባልጉ አልቀሩም በዚህም ምክንያት ወር ያልሞላዉ ልጅም ሳይወለድላቸዉ አልቀረም የሚል ወሪ ተናፍሶአል። ምናልባትም ይህ ሙሽራዋን ሳያስቀይም እንዳልቀረ ተገምቶአል። ሁሉ ሚስጢር እስካሁን ይፋ ባይወጣም የሞናኮዉ መስፍን ልጆቹ የሳቸዉ መሆኑን ለማረጋገጥ የደም ምርመራ አድርገዉ ወላጅ አባት መሆናቸዉ አለመሆናቸዉ መረጋገጥ እንዳለበት እየተነገረ ነዉ።

Hochzeit Albert II. und Charlene in Monaco

የሞናኮዉ መስፍን አልቤር ሁለተኛ እና የደቡብ አፍሪቃዊትዋ ታዋቂ የዋና እስፖርተኛ ቻርሌን የጋብቻ ስነ-ስርአትከሰርጉ በኋላ የሞናኮዉ መስፍን አልቤር በክረምት ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል በመሆናቸዉ ደቡብ አፍሪቃ ላይ ባለፉት ሳምንታት ዉስጥ በ 2018 አመት ለሚደረገዉ የክረምት የኦሎምፒክ ዉድድር አዘጋጅ ማን እንደ ሆን ዉሳኔ ላይ ለመገኝት አዲስዋን ሙሽራ አስከትለዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ተጉዘዋል። በሌላ በኩል ከሳምንት በፊት ያገቧት ደቡብ አፍሪቃዊት የአሁንዋ የሞናኮ ንግስት ቤተሰቦችም ሆኑ የደቡብ አፍሪቃ ፕሪዝደንት የእንኳን ደስ ያላችሁ ብለዉ ቅልጥ ያለ ግብዣን አድርገዉላቸዋል። በዝያዉም ከሰርግ በኋላ የጫጉላ ግዜያቸዉን በደስታ እንዲያሳልፉ የተንጣለለ ሆቴል ተዘጋጅቶላቸዉም ነበር። ግን አዲሶቹ ሙሽሮች በፍቅር ላይ አይመስሉም ይላል የደቡብ አፍሪቃዉ City Press ጋዜጣ እንኳን በአንድ ጣርያ ስር አንድ አልጋ ላይ ሊሆኑ ይቅርና በሳላሳ ኪሎሜትር ርቀት ተነጣጥለዉ የተለያየ ሆቴል እንደሚኖሩ ዘግቦአል። አዲሷ ሙሽራ የሞናኮዋ ንግስት ቻርሌን ከደስታ ይልቅ ፊትዋ ላይ ሃዘን አጥልሎ እንደሚታይና ይህንኑ ለመሸፈን ትልቅ ጥቁር መነጽር እንደምታደርግም ተዘግቦአል። ሰምወኑን የጀርመን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች፣ የንጉሳዊ ቤተስብ ጉዳይ አዋቂዎችን እያቀረቡ ስለሞናኮዉ መስፍን እና ስለ ደቡብ አፍሪቃዊትዋ ሙሽራ በሰፊዉ የሚነጋገሩበት ርዕስ ሆንዋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ