የባህል መድረክ - ጀርመን | ባህል | DW | 07.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ባህል

የባህል መድረክ - ጀርመን

ዩክሬይን እና ፖላንድ የሚያስተናግዱት የዘንድሮዉ የአዉሮጳ አገራት የእግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ነገ ይጀመራል። የእግር ኳስ ጨዋታ ባህሉ ያደረገዉ የጀርመን ህዝብ የግጥሚያዉን መጀመር በጉጉት እየተጠባበቀ ነዉ።

ዩክሬይን እና ፖላንድ የሚያስተናግዱት የዘንድሮዉ የአዉሮጳ አገራት የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ነገ ይጀመራል። የእግር ኳስ ጨዋታ ባህሉ ያደረገዉ የጀርመን ህዝብ የግጥሚያዉን መጀመር በጉጉት እየተጠባበቀ ነዉ። ሌላዉ ባለፈዉ ሳምንት እዚህ በቩርዝቡርግ ከተማ ስለተካሄደዉ የአፍሪቃ ፊስቲቫል እንዲሁም ፣ የብሪታንያ ንግስት ኤልሳቤጥ የነገሱበት ስድሳኛ አመት ከእሁድ ጀምሮ ለአራት ቀናት የተከበረበት ሂደት በዕለቱ ዝግጅታችን የምንዳስሳቸዉ አርዕስት ናቸዉ።

የእግር ኳስ ጨዋታን ባህሉ ያደረገዉ የጀርመን ህዝብ የዘንድሮዉ የአዉሮጳ አገራት የእግር ኳስ ዋንጫ  ዉድድርን ለመከታተል የዉድድሩን መጀመር የመጀመርያ ፊሽካ ጥሪ ለመስማት በጉጉት ላይ ነዉ። የዘንድሮዉ ዉድድር አዘጋጆች ዩክሬይን እና ፖላንድ ሲሆኑ ነገ የመክፈቻዉ ስነስርአት ደማቅ እንደሚሆን ከወዲሁ እየተነገረ ነዉ። ዉድድሩ ሊጀመር ገና ወራቶች ሲቀሩት ጀምሮ ጓደኛሞች ዉድድሩን በጋራ የሚያዩበትን ቦታ እቅድ ሲያወጡ፣ ቡና ቤቶች እና የመዝናኛ ቦታዎች ደንበኞቻቸዉ የእግር ኳስ ዉድድሩን በቴሌቭዥን መስኮት በድሎት የሚከታተሉበትን ስፍራ ሲያመቻቹና ሲያበጃጁ ሰነባብተዋል። በርካታ መደብሮችም ለእግር ኳስ አፍቃሪዉ እና በተለይም ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች የሚሸጡትን፣ በተለያየ መልክ  የተሰራዉን የጀርመንን የሰንደቅ አላማ ህብረ ቀለም የያዙ የተለያየ ቁሳቁስ በገበያ መደባቸዉ ላይ አዉጥተዉ መሸጥ ከጀመሩ ወራትን አስቆጥረዋል።

በኩል የጀርመኑ የእግር ኳስ  ብሄራዊ ቡድን የአዉሮጳ አገራት የእግር ኳስ ዋንጫ  ዉድድር  ከመጀመሩ አንድ ሳምንት ቀደም ሲል አንዷ የዉድድሩ  አዘጋጅ በሆነችዉ በፖላንድ፣ አዉሽፊትዝ በመባል የሚታወቀዉን የናዚን የእልቂት ጣቢያ  ጎብኝቶ፣ ሻማ በማብራት እና  ጉንጉን አበባን በማስቀመጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ያለቀበትን ጥቁር የጀርመን የታሪክ  ጠባሳ በማሰብ ሃዘኑን ገልጾአል። በጉብኝቱ ከጀርመኑ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ከዮአሂም ሎቨ ጎን፣ የቡድኑ አምበል ፊሊፕ ላም፣ ትዉለደ ፖላንዳውያን ሚሮስላቭ ክሎዘ እና ሉካስ ፑዶልስኪ ተሳታፊ ነበሩ። ጀርመናዊው የብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዋና ስራ አስኪያጀ ኦሊቨር ቢርሆፍ አዉሽቪትስን የጎበኘነው  የጀርመን ጥቁሩ የታሪክ ምዕራፍ መቼም እንደማይረሳ እና ይህ ዓይነቱ ታሪክም እንደማይደገም ለማሳየት ነዉ ብለዋል። «ጉብኝታችን ትልቅ እና አስፈላጊ ትምህርት ሰጥቶናል። ማስተላለፍ የፈለግነዉንም ዋና መልዕክት አሳክተናል ብዪ እገምታለሁ። በተለይ የወጣቱ ትዉልድ ተጫዋቾቻችን፣ ይህ ዓይነቱን ያለፈ ጥቁር የታሪክ ጠባሳ መርሳት እንደሌለባቸዉ፤ ሁልግዜም ይህን ታሪክ በማስታወስ  እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ዳግም መፈጸም እንደሌለበት እንዲያስቡ ለማድረግ ሞክረናል።»   በደቡባዊ ፖላንድ  የሚገኘዉ አዉሽቪትስ በመባል የሚታወቀዉ የአዶልፍ ሂትለር የናዚ አገዛዝ  እጅግ ትልቅ የማጎርያ ጣብያን የጎበኘዉ የጀርመኑ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ፕሬዝደንት Wolfgang Niersbach በስፍራዉ በተቀመጠዉ  ማህደር ላይ በብሄራዊ ቡድኑ ስም የሃዘን መግለጫ ቃላቸዉን አኑረዋል። የብሄራዊ ቡድኑ ፕሬዝደንት Wolfgang Niersbach በተጨማሪ የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያዉ፤ የግል ጥቅምን የማያስቀድም፣ መቻቻል እና ሚዛናዊነት የሚታይበት የህብረት ጨዋታ መሆን እንደሚኖርበት አስረድተዋል። በርካታ የአዉሮጳ አገራት የእግር ኳስ ቡድኖች እንዲሁ ይህንን የመታሰብያ ቦታ ጎብኝተዋል።  በፖላንድ በአዉሽቪትስ የማጎርያ ጣብያ ከ1,3 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ በአዶልፍ ሂትለር በተመራዉ የናዚ ጦር በግፍ ሲገደል፣ ከሟቾች መካከል አብዛኞቹ አይሁዳውያን ነበሩ።

የምዕራብ አፍሪቃዊትዋ አገር ሴኔጋል እና በአትላንቲክ ዉቅያኖስ ላይ የምትገኘዉ ደሴቲቷ ካፕቬርዴ ዘንድሮ እዚህ ጀርመን ቩልስ ቡርግ ከተማ በተደረገዉ አመታዊ የአፍሪቃ ፊስቲቫል ላይ በክብር እንግድነት የተገኙ አገራት ነበሩ። በአዉሮጳ እጅግ ግዙፍና የተለያዩ የአፍሪቃ አገራት ባህል ነክ እንቅስቃሴዎች የሚታዩበት፣ ሙዚቃ እንዲሁም ባህል ነክ የመዝናኛ መድረኮች የሚታዩበት በቮልዝ ቡርግ ከተማ የሚደረገዉ የሶስት ቀናት የአፍሪቃ ፊስቲቫል ከተለያዩ የአዉሮጳ አገራት የሚመጡ  100 ሽ በላይ እንግዶችንም ያስተናግዳል። በዚህም የቮልስ ቩርጉ ፊስቲቫል በአዉሮጳ የሚታይ እጅግ ትልቁ የአፍሪቃ ፊስቲቫል ነው። ዘንድሮዉ በነበረዉ ዝግጅት  አፍሪቃዊ የሆነ የባህላዊ እና የዘመናዊ ልብስ ቅድ ትርኢት ለመጀመርያ ግዜ ቀርቦ ነበር።

ህዝብ በቮልስ ቡርግ የአፍሪካ ፊስቲቫል ላይ የቀረበዉን የልብስ ቅድ ትርዕኢት የተመለከተዉ በከፍተኛ አድናቆት ነዉ። አምስቱ የሴኔጋል ወጣቶች በልብስ ቅድ አዋቂዋ ሴኔጋላዊት የተሰፋዉን የተለያየ አልባሳትን እያጠለቁ ትርኢቱን በመድረክ ላይ መለስ ቀለስ እያሉ አሳይተዋል። ራማ ዲያዉ ትባላለች የ36 አመትዋ ሴኔጋላዊት የልብስ ቅድ አዋቂ፣ በቮልስ ቡርጉ ግዙፍ የአፍሪቃ መድረክ ላይ ስራዎችዋ ለዓለም ህዝብ በመታየቱ ህልሟ እዉን መሆኑን ትገልጻለች

« በቮልስቡርጉ አፍሪቃ ፊስቲቫል ላይ ስገኝ የመጀመርያ ግዜዪ ነዉ። በዚህ መድረክ ለመገኘት ብዜ ግዜ ተወዳድሪም ነበር።  በዚህ አመት ግን አንድ አስደሳች እና ድንገተኛ የሆነ መልክት መጣልኝ። ይኸዉም የፊስቲቫሉ ዳይሪክተር ስልክ ደዉለዉ፣ እንደተቀበሉኝ ብቻ ሳይሆን በፊስቲቫሉ እንደተጋበዝኩ እንዲሁም ለሶስት ቀናት የልብስ ቅድ ትርኢት ማሳየት እንደምችል ገለጹልኝ»  ራማ ዲያዉ ከህጻንነትዋ ግዜ ጀምሮ አሮጌ ልብሶችዋን እየቀደደች በሌላ አይነት መልክ በመስፋት አዲስ ፈጠራን ታደርግ እንደነበር ትናገራለች። እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 1995 ዓ,ም ለመጀመርያ ግዜ በአዲስ ፈጠራ የልብስ ቅድ፣ የዋና ልብስ ለገበያ አቅርባ እንብዛም አድናቂን እንዳላገኘች ተገልጾአል። በመቀጠል ራማ እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር 2009 ዓ,ም ለስራዎችዋ «ሜቲስ» ማለት ድብልቅ የሚል ስያሜን በመስጠት በአገርዋ በሴኔጋል በሚገኘዉ የልብስ ቅድ መድረክ  ገባች።

« የራሴ የሆነ የልብስ ቅድ ፈጠራ አለኝ። ማለት ዘመናዊዉን ከአፍሪቃ ባህላዊ የልብስ ቅድ ጋር በማጣመር የምሰራዉ ነዉ። ለምሳሌ ከቲሸርት ቁራጭ ጋር የአፍሪቃ ባህላዊ ጨርቅን በመቀጠል የምሰፋዉ ስራ አንዱ ነዉ። አንድ አፍሪቃዊት ከባህላዊዉ ጨርቅ ራቅ ብላ የአዉሮጳዊዉን መልበስ ስትፈልግ፣ ከአፍሪቃዊዉ ባህላዊ ጨርቅ ጋር የተሰፋዉን ዘመናዊዉን ልብስ  ማድረግ ትችላለች» 

የራማ ዲያዉ አዲስ አይነት የልብስ ቅድ ለአፍሪቃዉያኑ ሴቶች ብቻ ሳይሆን አዉሮጳዉያኑም እንዲለብሱት በማሰብ የተሰራ ነዉ። ማለትም እስካሁን ብዙም አይን ዉስጥ የማይገባዉ ባህላዊዉ የአፍሪቃ ሴቶች ልብስ አዎ ብዙዎች «የአፍሪቃዉያን የባህል ልብስ አፍሪቃዉያኑ ላይ በጣም ያምራል፣ እኛ ስንለብሰዉ ግን እንብዛም ደምቆ አይታይም ይሉኛል። ስለዚህ  ነዉ የልብስ ቅድ ስራዪን ሳሳይ አዉሮጳዉያኑንም የማሳትፈዉ። በልብስ ቅዱ ትርኢት ሁልግዜም ቢሆን የተለያዩ አገራት ባህሎችን አንጸባርቅበታለሁ። በዚህም፤ የዚህንም ሆነ የዚያን የባህል ልብስ ማድረግ እና ማሳየት እንደሚቻል እጠቁማለሁ»

በጀርመን ብቮልስ ቡርግ ከተማ በነበረዉ የአፍሪቃ ፊስቲቫል ላይ የሴኔጋልዋ ልብስ ቅድባለሙያ የራማ ዲያዉ ስራዎች አድናቆትን አግኝቶአል። ራማ በዚህ በጀርመን ቮልቡርግ ከተማ በተካሄደዉ የአፍሪቃ መድረክ ላይ ያሳያችዉ ስራዋ ለአለም መድረክ ለመድረስ እንደ መገናኛ መንገድ እንደሚሆናት ታምናለች። በአመታዊዉ በዚህ አፍሪቃ ፊስቲቫል ላይ በርካታ አፍሪቃዉያን ሙዚቀኞች ከምዕራባዊዉ የሙዚቃ መድረክ የሚተዋወቁበት መድረክ መሆኑ ይታወቃል። ባለፉት አመታት በዚሁ በቮልስ ቡርግ የአፍሪቃ ፊስቲቫል ላይ እዉቁ የበገና ደርዳሪ አለሙ አጋ፣ ብቸኛዉ ማንዶሊን ተጫዋች አየለ ማሞ፣ እንዲሁም በቀደምቶቹ አመታት እዉቋ የክራር ተጫዋች አስናቀች ወርቁ በዚሁ የቮልስ ቡርግ አፍሪቃ ፊስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን በመወከል መገኘታቸዉ የሚታወስ ነዉ።

ወደ ሶስተኛዉ እና የመጨረሻ ርዕሳችን ስንሻገር ደግሞ የብሪታንያዋ ንግስት ኤልሳቤጥ የነገሱበትን ስድሳኛ አመት የአልማዝ እዮቤልዩ በአል በደማቅ መከበሩ ነዉ። ብሪታንያ ባለፈዉ እሁድ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ንግስት ኤልሳቤትን ስድሳኛ አመት የንግስ ቀን በደማቅ አክብራለች። በክብረ በአሉ ላይ ለንደንን በሚያቋርጠዉ ቴምስ ወንዝ ላይ ከ 1000 የሚበልጡ መርከቦች እና ጀልባዎች ልዪ ትርኢቶችን አሳይተዋል። ዝናባማ የአየር ጸባይ እንዳላት በምትታወቀዉ ብሪታንያ በክብረ በአሉ ቀናትም ዝናብ አላጣትም፣ እንድያም ሆኖ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ የበአሉ ታዳሚዎች የዝናብ መከላከያ ዣንጥላ ይዘዉ የዝናብ ልብስ አጥልቀዉ በወንዙ ዳርቻ በመቆም ትርኢቱን ሲመለከቱ ታይቷል፤ ቦታ ለመያዝና ጥሩ ቦታን ለማግኘት ሲሉ ከበአሉ አንድ ቀን ቀደም ብለዉ በዝያዉ በወንዙ ዳርቻ አነስ ያለች ድንኳን ተክለዉ ያደሩም እንዳልጠፉ ዘገባዎች ያስረዳሉ።

ብራማ ነጣ ያለ አይነት ቀለም ልብስ የለበሱት የ 86 አመትዋ ንግስት ኤልሳቤጥ ቀይ ቀለም እና በወርቅ በተንቆጠቆጠ መርከብ ላይ ሆነዉ ትርኢቱን ሲከታተሉ ታይቶአል። በበአሉ ሁለተኛ ቀን 12 ሽ ተጋባዝ እንግዶች በንግስቲቱ መቀመጫ በሚገኘዉ የመዝናና ፓርክ መጋበዛቸዉ ተዘግቦአል።

በክብረ አሉ የመጀመርያ እለት በለንደን ቴምስ ወንዝ ዳርቻ ላይ በመሆን ክብር በአሉን የተከታተለዉ ህዝብ ቁጥር 1,2 ሚሊዞን ህዝብ እንደነበር ተነግሮአል።  ንግስት ኤልሳቤት አባታቸዉ ንጉስ ጆርጅ 6ኛ ከዚህ አለም በመለየታቸዉ እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር የካቲት 6 1954 ዓ,ም የአባታቸዉን ቦታ ተክተዉ መንገሳቸዉ ይታወቃል። ሙሉዉን ጥንቅር ያድምጡ!  

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 07.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/158V2

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 07.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/158V2