የባህል መድረክ በአዉሮጻዉያኑ 2009 አ.ም | ባህል | DW | 03.01.2010
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ባህል

የባህል መድረክ በአዉሮጻዉያኑ 2009 አ.ም

የአዉሮጻዉያኑ አዲስ አመት አንድ ብሎ በጣት የሚቆጠሩ ቀናትን አስቆጥሮአል። ዛሪ በመጀመርያዉ ሳምንት በመጀመርያዉ አሁድ ደግሞ ባለፈዉ የአዉሮጻዉያኑ 2009 አ.ም በጀርመን የባህል መድረክ ምን አበይት ጉዳዮች ተፈጽመዉ አልፈዋል።

default

ብራንድቡርገር በር የአዲስ አመት ቅበላ

በዛሪዉ ጥንቅራችን የጀርመን ባህል መድረክ በአዉሮጻዉያኑ 2009 አ.ም በሚል በጥቂቱ ልንዳስስ ተዘጋጅታናል ለጥንቅሩ አዜብ ታደሰ ነኝ መልካም ቆይታ
ከባተ ሶስተኛ ቀኑን የያዘዉ የአዉሮጻዉያኑ 2010 አ.ም የጀርመን ህዝብ በደማቅ ሁኔታ ተቀብሎታል። በመጨረሻዎቹ ቀናት ህዝቡ የገናን እንዲሁም የአዲስ አመት ክብረ በአልን በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል። ምንም እንኻ ያለፈዉ አዉሮጻዉያኑ 2009 አ.ም ሲብት ጀምሮ አለምን የመታዉ የፊናንስ ቀዉስ እድግሱ ፊስታ ላይ ጫና ቢጥልም ጀርመናዉያን ተወዳጅ የገና በአላቸዉን ለገና ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ ብለዉ እንደ ደንቡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቁጠባ ባህላቸዉ በመሆኑ ቆጥበዉ አሳልፈዉታ። ባለፈዉ የአዉሮጻዉያኑ 2009 አ.ም በባተ በአምስተኛ ቀኑ፣ በጀርመን አገር በሃብት ንብረታቸዉ ብዛት አምስተኛ የሆነት ጀርመናዊ የመድሃኒት አስመጪና ላኪ ቢሌዮኔር፣ የ 74 አመቱ Adolf Merckle የፊናንስ ቀዉሱ በሚያስተዳድሩት በርካታ ድርጅቶቻቸዉ ላይ ከፍተኛ ተጽኖ በማምጣቱ እና ቀዉስ በመከተሉ የራሳቸዉን ህይወት አጠፉ። በጀርመን የባህል ድረ-ገጾችን ጨምሮ በአለም ዙርያ ስለ ጀርመናዊዉ ባለ ሃብት እና የህግ ሰዉ ከዚህ አለም በአሰቃቂ ሁኔታ በሞት መለየት አበይት ዜና ሆኖ የአመቱ መጀመርያ ወር ጀመረ። የፊናንስ ቀዉሱ በጀርመን ያሉ ታላላቅ የሸቀጥ መደብሮችንን፣ ሸቀጥ አቅራቢዎችን መጎነጡ ሳያንስ ባሳለፍነዉ የአዉሮጻዉያኑ አመት በገባ በሶስተኛዉ ወር እዚህ በጀርመን በትልቅቱ ሶስተኛ የሆነዉ እና የ2000 ታሪክ ባለዉ በኮለኝ ከተማ በጀርመን ከፍተኛ የታሪክ ማህደራትን አቅፎ የያዘ የነበረዉ የኮለኙ ሙዚየም ተፈረካክሶ ወደቀ። ይህ በመሃል ኮለኝ ከተማ ይገኝ የነበረዉ የታሪክ ሙዚየም ተፈረካክሶ የወደቀዉ በከርሰ ምድር ዉስጥ በመገንባት ላይ ያለዉ የባቡር ሃዲድ ግንባታ መሰሩቱን ነክቶት በመጎዳቱ ነበር። በጉዳቱ በርካታ የማይገኙ የሁለት ሽህ አመታት ታሪክ በመዉደሙ እና በመበላሸቱ በርካታ የታሪክ ምሁራን በተለይም የከተማይቱን ነዋሪ አሳዝኖአል በጉዳቱ የሁለት ወጣቶች ህይወትም ጠፍቶአል። በተፈረካከሰዉ የቤት ፍርስራሽ የተቀበረዉ እና ሁኔታዉን የለወጠዉን የታሪክ መዝገብ እና ቁሳቁስ እንደገና አድሶ ለትዉልድ ለማኖር አሁንም የፍለጋ ስራዉ አልተጠናቀቀም።

ሌላዉ በዚሁ በተጠናቀቀዉ የአዉሮያዉያኑ አመት 2009 የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪ ዳን ድርጅት ናቶ የተመሰረትበትን ስድሳኛ አመት በማስመልከት እዚህ በጀርመን በመዝናኛነት እና ለፈዉስ የሚሆን ንጥረ ነገ ያዘለ ፍል ዉሃ እንደሚፈልቅባት በአለም አቀፍ ደረጃ በሚነገርላት በባድን ቫድን ከተማ የናቶ አባል አገራት ተወካዮች እና መንግስታት ታዋቂ ፒያኖ ተጫዋች በታጀበ የደመቀ የራት ግብዣ ማድረጋቸዉ በባህሉ መድረክ አካያ በስዕል በተደገፈ መረጃ የአመቱ የአብይ ርእስ ሆኖ ቀርቦአል።

Sara Nuru Gewinnerin Germany's next Top Model

ዉቢት ሳራ ኑሩ


በጀርመን ባሳለፍነዉ የአዉሮጻዉያኑ 2009 አመት ለአራተኛ ግዜ በተካሄደዉ የሴቶች የቁንጅና ዉድድር የሃያ አመትዋ ኢትዮጽያዊትዋ ዉቢት፣ የዉቦች ዉብ በመሆን የጀርመን ቆንጆ ተብላ በአለም አቀፍ መድረክ መቅረብ ጀምራለች። እዚህ በባየር ግዛት በምትገኝ ኢርዲንግ በምትባል አነስ ያለች የገጠር ከተማ የተወለደችዉ ዉቢት ሳራ ኑሩ፣ በጀርመን በተካሄደዉ የቆነጃጅት ዉድድር 21 ሺህ ተወዳዳሪ ዉቢቶችን በቁንጅናዋ፣ ጣጥላ ከጀርመን ኒዮርክ ከሃዋይ ሲንጋፖር እንዲሁም ፓሪስ በሚገኘዉ እዉቅ የዘመናዊ ልብስ በሞዲልነት መድረክ ቀርባ፣ በዉበትዋ አለምን ማስገረሟ የጀርመንን የባህል መድረክም ሆነ ሌላዉን አለም አገራት የመገናኛ ብዙሃን ትኩረቱን እንዲጥል ያደረገዉ። ኢትዮጽያዉያን በተለይ፣ በተለይ፣ ጀርመን የምንኖር ደግሞ አኩርተሽናል ብለናታል። ሳራ በኢትዮጽያ በመንቀሳቀስ ላይ ያለዉ ሜንሽን ፎር ሜንሽን እርዳታ ድርጅት ዉስጥ እርዳታዋን በማቀበል ወገኖችዋን እንደምትረዳም መግለጽዋ ተጠቅሶአል። ሳራ በቅርቡ ኢትዮጽያን ጎብኝታ መምጣትዋ እንዳስደሰታትም በባህል ድረ-ገጽ ላይ ኢትዮጽያዊትዋ ዉቢት ሳራ ኑሩ ተብሎ ተጽፎላታል።

ሌላዉ የጀርመንን የባህል ድረ-ገጽ እና የብዙሃን መገናኛ የሳበዉ ርእስ እ.አ 1912 አ.ም ሰሜን አትላንቲክ ዉቅያኖስ ላይ የሰመጠዉ የታይታኒክ ግዙፍ መርከብ 1517 ያህል ተሳፋሪዎች ሰምጠዉ ሲሞቱ ከተሳፋሪዎች መካከል 706 ያህሉ ተርፈዉ እንደ ነበር እና የመጨረሻዋ ተሳፋሪ ባሳለፍነዉ የአዉሮጻዉያኑ 2009 አ.ም በ 97 አመታቸዉ ከዚህ አለም መለየታቸዉን የሚያሳየዉ ዜና ነበር። ከተረፉት 706 ተሳፋሪዎች መካከል በፖስታ ክምችት ባለበት ሳጥን ዉስጥ ሆና የተረፈችዉ የሁለት ወር ህጻን፣ የዛሪ ሶስት ቀን ባሳለፍነዉ የፈረንጆቹ 2009 አ.ም የዘጠና ሰባት አመት አዛዉንት ሆነዉ የመጨረሻዋ የታይታኒክ መርከብ ተራፊ በመሆን ቤተሰቦቻቸዉ በስደት አሜሪካ ለመኖር ወደ አሰቡበት ሳይሆን በትዉልድ አገራቸዉ በእንግሊዝ ነበር የኖሩት። እንግሊዛዊቷ ወ/ሮ Millvina Dean ወላጆቻቸዉን እና ታላቅ ወንድማቸዉን በአደጋዉ አጥተዉ ፣በዚሁ አዳጋ ብቻ እዉቅናቸዉ ጠንክሮ በተለይ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ወደ ተለያዩ አገሮች በመጋበዝ እና ቃለ መጥይቅን በመመለስ ብቻ አለምን መዞራቸዉ ተገልጾአል።

የአፍሪቃዉ የሙዚቃ ንጉስ ከዚህ አለም በሞት ተለየ በሚል። የጀርመኑ ሽፒግል የተሰኘዉ መጽሄት በመገናኛ መረብ በባህል ድረ-ገጹ የዝነኛዉ ኢትዮጽያዊ ሙዚቀኛ የዶክተር ጥላሁን ገሰሰን ህይወት ታሪክ እና የቀብር ስነ-ስርአቱን በተመለከተ በስዕል በተደገፈ በዚሁ ባለፈዉ የአዉሮጻዉያኑ አመት ሰፋ ያለዉን ዘገባ አዉጥቶ ነበር። ስለ እዉቁ ኢትዮጽያዊ ሙዚቀኛ ጥላሁን ገሰሰ፣ መጽሄቱ በተለይ በርዕሰ አንቀሱ በኢትዮጽያ ታሪክ በቀብር ስነ-ስርአቱ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር በህዝብ የተሸኘ ሲል አስቀምጦታል።

የአለም የፖፕ የሙዚቃ ንጉስ የማይክል ጃክሰን መምት ባጠናቀቅነዉ የአዉሮጹያኑ አመት የአለምን ህዝብ አሳዝኖአል አስደንግጦአል። የ51 አመቱ የፖፕ የሙዚቃ ንጉስ This is it በተሰኘ ያዜመዉ ሙዚቃ የመጨረሻ እትሙ እንደሆነም ተገልጾአል። ሃይል ያለዉ መድሃኒት መመርፊ ተሰጥቶት ልቡ ስራዉን መስራት አቁሞ በድንገት ከዚህ አለም በድንገት መለየቱ በዜና ማሰራጫዎች በተሰማ ወቅት በአለም ያሉ አፍቃሪዎቹ የሃዘን መግለጫቸዉን በተለያየ ሁኔታ አስተጋብተዋል። ህጻናትን አባልጓል በመባል ለብዙ አመታት ከመድረክ ተገልሎ የቆየዉ ማይክል ጃክሰን በየሙዚቃ አልበሙ መደብሩ ለሽያጭ የቀረበዉ የሙዚቃ አልበሙ በግፍ ገበያ ቀርቦ በሽምያ ተሸጦአል። ሙዚቃዉ በመገናኛ ብዙሃን እንብዛም አይሰማ የነበረዉ በተለያዩ አገራት የመገናኛ ብዙሃን ዳግም በሰፉዉ መሰማት ጀምረዋል። የባህል መድረግ ድረ-ገጾች በአለም ዙርያ እያለዉ ያጣ ኖሮ ያልኖረ የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን በማለት ጽፈዉለታል።

Leichtathletik-Weltmeisterschaft 2009, Gewinner der 200m Sprint, Usain Bolt

ጃማይካዊዉ ፈጣን ሯጭ እና በርሊኖ

ባለፈዉ አመት ሌላዉ በባህል መድረክ አነጋጋሪ የነበረዉ ርዕስ እዚህ በበርሊን የተካሄደዉ 12ኛዉ የቀላል አትሌቲክስ ዉድድር ነበር። በተለይ የወቅቱ የዉድድሩ ገድ ሆኖ የቀረበዉ በርሊኖ የተሰኘዉ የድብ ቅርጽ አይነቱ አሻንጉሊት የስፖርት ዉድድሩን ለየት ያለመልክ እንዲኖረዉ ሲያደርግ፣ የአለምን ህዝብ ትኩረት የሳበዉ ደግሞ ጃማይካዊዉ የአጭር ርቀት ሮዋጭ Usain Bolt በአለም ፈጣኑ ሯጭ መሆኑን ያረጋገጠበት እና ከበርሊኑ ድብ ጋር በመሆን ለየት ያለ እንቅስቃሴን በማሳየት ስፖርት የአለምን ህዝብ የሚያገናኝ ታላቁ መሳርያ መሆኑን የገለጸበት ሁኔታ በጀርመን በአመቱ የባህል ክንዉኖች ዉስጥ ቦታ ተሰጥቶት ያለፈ ርእስም ነበር።

ባሳለፍነዉ የአዉሮጻዉያኑ 2009 አ.ም ጀርመናዉያን የነጻነት ኃይል ብለዉ በኩራት የሚጠቅሱት 20 ዓመት የሆነው የበርሊኑን ግንብ አጥር የገረሠሠበት ዳግም ሀገራዊ ውኅደት የተከበረበት ፣ 60 ዓመት ጸንቶ የቆየው መሠረታዊው ህገ-መንግሥት የተወሳበት፣ የባህል መድረክም ሳይጠቀሰዉ አላለፈም። ሌላዉ በዝያዉ 2009 የአዉሮጻዉያኑ አመት ጀርመናዉያን እጅግ የኮሩበት በስቶኮልም የሚገኘዉ የኖቤል ሽልማት ቢሮ የአመቱ የስነ-ጽሁፍ ኖቤል ሽልማቱን ትዉልደ ሮማንያዊት ለሆነችዉ ጀርመናዊት ደራሲ ሄርታ ሙለር ማበርከቱ ነበር። የ 56 አመትዋ ጀርመናት ጸሃፊ ሄርታ ሙለር በግጥም ስራዎቿ ተደናቂ መሆንዋ ተገልጾላታል፣ በተለይ ለስደት ያበቃት ኒደሩንገን በተሰኘዉ በጀርመንኛ ያወጣችዉ የአጭር ልቦለድ ስብስብ ስለሰዉ ልጆች መብት ማመላከቱም ተጽፎላታል። የመብት እጦት የነበረባት የቀድሞዋ ሶሻሊስት ሮማንያን የማህበራዊ ህይወት በግልጽ በማስቀመጥዋ ስራዎችዋ በሮማንያ ለህትመት እንዳይበቃ ተደርጎአል። ባለፉት ጥቂት አመታት ዉስጥ በተለይ በምዕራብ አዉሮጻ የጀርመናዊቷ የስነ-ጽሁፍ ስራዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለአንባብያን ቀርበዋል። በተለያዩ የድርሰት ስራዎችዋ በጀርመንኛ ቋንቋ ለአንባብያን ያቀረበችዉ ጀርመናዊት ደራሲ በተለይ ከሁለተኛ አለም ጦርነት በኻላ በተለያዩ አገሮች ይኖሩ የነበሩ ጀርመናዉያን ይደርስባቸዉ የነበረዉን በደል በጽሁፎችዋ አስቀምጣለች።

በአዉሮጻ በሙዚቃዉ መድረክ ደግሞ ተደናቂ የሆነዉ እንጊሊዛዊ ጎልማሳ ሮቢ ዊሊያምስ በአመቱ መጠናቀቅያ ላይ ከሶስት አመት ከመድረክ መጥፋት በኻላ ብቅ ማለቱ በሙዚቃ አፍቃሪ አዉሮጻዉያንን ደስ በማሰኘቱ ሌላዉ የጀርመን የባህል መድረክ የዳሰሰዉ ርእሱ ነበር። ሮቢ ዊሊያምስ የዛሪ ሶስት አመት በተለይ በአገሩ ጭኖት የነበረዉን የሙዚቃ ዝና ዳግም ለመመለስ እንደሚፈልግ መግለጹ ሲታወቅ አመቱ ሊጠናቀቅ ባወጣዉ Bodies በተሰኘዉ አልበሙ ለሟቹ የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ለማይክል ጃክሰን መታሰብያ ማቀንቀኑም ተገልጾአል።

Herta Mueller verleihung Literaturnobelpreis

ጀርመናዊትዋ ደራሲ ሄርታ ሙለር

ታድያ አመቱ ሳይቋጭ ማለት ባለፈዉ 2009አመት በአዉሮጻዉያኑ 2010 በተለይ የባህል መድረክ የሚዳስሰዉን አበይት መረሃ ግብር አስቀምጦአል። በያዝነዉ አዲስ ዓመት በጉጉት ከሚጠብቁት ድርጊቶች በደቡብ አፍሪቃ የሚካሄደዉ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር፣ እዚህ በጀርመን የሩር ግዛት የአመቱ የአውሮፓ የባህል ከተማ ተብሎ መገለጹ እና የተለያዩ የባህል ክንዉኖች እንደሚካሄዱ፣ እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያን ጉባዔ እንደሚገኙበት ሳይጠቅስ አላለፉም።

ለአዲስ አመት መቀበያ በመባቻዉ ምሽት ላይ በተለይ በበርሊን ከተማ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በለቱ የነበረዉ ቅዝቃዜ ሳይበግረዉ ለድግሱ በተዘጋጀዉ ሙዚቃ ዳንስ ዉዝዋዜ እና ለበአሉ ድምቀት የተዘጋጀዉን የርችት ተኩስ እያየ እና እሱም እራሱ እየተኮሰ አዲስ አመትን ተቀብሎአል። በማቹ የአለም የሙዚቃ ንጉስ በማይክል ጃክሰን ዜማም ተወዛዉዞአል። የአዉሮጻዉያኑ አመት የጀርመን የባህል ገጾች ከብዙ በጥቂቱ ከላይ ያነሳናቸዉን ርእሶች አዉስተዉ አልፈዋል። አመት አመት ያድርሰን!

አዜብ ታደሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 03.01.2010
 • አዘጋጅ Azeb Tadesse
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/LJBp
 • ቀን 03.01.2010
 • አዘጋጅ Azeb Tadesse
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/LJBp