የባህላዊ መዚቃዎች ተስፋና ተግዳሮት በደቡብ ኢትዮጵያ | ባህል | DW | 05.12.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የባህላዊ መዚቃዎች ተስፋና ተግዳሮት በደቡብ ኢትዮጵያ

በደቡብ ኢትዮጵያ ባህላዊ ዜማዎችና ውዝዋዜዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጭምር ተወዳጅነታቸው እየጨመረ ነዉ ።  ይሁንና በአሁኑወቅት በርካታ ወጣቶች በባህላዊ መዚቃ ድምጻዊነትና ተወዛዋዥነት እየተሳተፉ ቢገኙም አሁንም ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ወደ ሙዚቃ ገበያው ለመግባት በርካታ እንቅፋቶች እንዳሉበት ይነገራል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:55

የባህላዊ ሙዚቃ ባለሙያዎች ድጋፍ ያስፈልገና

በኢትዮጵያ ሰፊ ማኅበረሰባዊና ባህላዊ ሀብቶች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል የደቡብ ክልል በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በክልሉ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ያሏቸው ቱባ ባህላዊ ዜማዎችና ውዝዋዜዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከክልሉ አልፎ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጭምር ተወዳጅነታቸው እየጨመረ ይገኛል።  በአሁኑወቅት በርካታ ወጣቶች በባህላዊ መዚቃ ድምጻዊነትና ተወዛዋዥነት እየተሳተፉ ቢገኙም አሁንም ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ወደ ሙዚቃ ገበያው ለመግባት በርካታ እንቅፋቶች እንዳሉበት ይነገራል።   

በሀዋሳ ከተማ በምስራቅ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው መለስተኛ ክፍል የደቡብ አምባሳደር የባህል ኪነት ቡድን አባላት ዘውትር ለባህላዊ ሙዚቃ ልምምድ የሚገናኙበት ክፍል ነው። በዚህ ክፍል ከወላይታ እስከ ከንባታ ፣ ከዘይሴ እስከ ደራቬ ሁሉም የደቡብ ክልል ማህበረሰብ ባህላዊ ዜማዎች ይቀነቀኑበታል፤ ውዝዋዜና ዳንኪራዎች ይረገጡበታል።

በደቡብ አምባሳደር የባህል ኪነት ቡድን አማካኘነት በሚዘጋጀው የባህላዊ ሙዚቃ ልምምድ የሚሳተፉት አብዛኞቹ በአፍላ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው ። ከእነኝሁ ወጣቶች መካከል በኪነት ቡድኑ ውስጥ በቋሚ የደሞዝ ክፍያ በማገልገል ላይ የሚገኙት ነፃነት ረጋሳ እና አማኑኤል ኪሮስ ይጠቀሳሉ ። ነፃነት እና አማኑኤል በትምህርት  ቤት ሳሉ ይሳተፉባቸው የነበሩ የባህል እና የኪነ ጥበብ ክበባት ዛሬ ላይ የኑሮ መተዳደሪያቸው ለሆነው  ባህላዊ የሙዚቃ ተወዛዋዥነት ስራቸው መሰረት እንደሆኗቸው ይናገራሉ። በተለይም ወጣት ነፃነት ረጋሳ << በትምህርት ቤት በሚገኙ የኪነ ጥበብ ክበባት ውስጥ ፍላጎቱ ከነበራቸው ሌሎች ተማሪዎች ጋር የተለያዩ ባህላዊ ትርኢቶችን በማቅረብ እሳተፍ ነበር ። ይህም የደቡብ አምባሳደር የባህል ኪነት ቡድንን በመቀላቀል ከተለማማጅነት ወደ ሙሉ ሙያተኝነት ላደረኩት ሽግግር መነሻ ሆኖኛል >> ትላለች ። 

ሌላኛው የቡድኑ ተወዛዋዥ አማኑኤል ኪሮስ በበኩሉ ባህላዊ የኪነት ቡድኑን በአባልነት መቀላቀሉ በቀጣይ በባህላዊ ኪነ ጥበብ ዘርፈ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ እንደሆነለት ይናገራል ። በማያያዝም << በቡድኑ ውስጥ መስራቴ በዘርፉ ያለኝን ልምድና ክህሎት እንዳሳድግ አስችሎኛል። ይህም ወደፊት በቀላሉ የሙዚቃው ገበያውን ለመቀላቀል ዕድል ይፈጥርልኛል የሚል እምነት አለኝ>> ብሏል።

በዚሁ የኪነት ቡድን ውስጥ የባህላዊ ዜማዎች ድምጻዊ የሆነው ፀጋዬ ጢሞጢዎስ እና የተወዛዋዥ ባለሙያዋ ነፃነት ረጋሳ ቱባና ባህላዊ የኪነ ጥበብ ስራዎቻቸውን ወደ ገበያ በማውጣት አካባቢያቸውን ለማስተዋወቅ የበረታ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ ። ይሁንእንጂ በደቡብ ክልል ባህል ፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ በኩል የሚፈለገውን ድጋፍ አለማግኘታቸው ውጥናቸውን ከግብ ለማድረስ እንቅፋት እንደሆነባቸው አልሸሸጉም።

ባለሙያዎቹ << እስከአሁን በጣም ጥቂት የባህላዊ ሙዚቃ ባለሙያዎች በራሳቸው ጥረት ወደ ሙዚቃው ገበያ በመግባት አካባቢያቸውንና ራሳቸውን እየጠቀሙ ይገኛሉ። በአንፃሩ የተሻለ አቅም ያለን የቡድኑ አባላት ግን በቢሮው የድጋፍ እጦት ምክንያት ወደአሰብነው ደረጃ ለመሸጋገር አልቻልንም >> ብለዋል። በእርግጥ ባህላዊ ሙዚቃዎችን ጨምሮ የማህበረሰቦችን ትውፊቶችን የማጎልበትና የማሳደግ ስራ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ይታመናል።

በይበልጥ ግን ስራዎችን የማስተባበሩና የማስፈጸሙ ሃላፊነት የወደቀው በክልሉ ባህል ፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ትከሻ ላይ እንደሆነ ይታወቃል። የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አብቶ አኒቶ በክልሉ ባህላዊ ሙዚቃዎችን ለማጎልበት ባህላዊ የኪነት ቡድኖች ማደራጀትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል ።

በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ክልሉ በባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ ያለውን እምቅ ሀብት  በጥናት እንዲለይ መደረጉንም አቶ አብቶ ተናግረዋል። በባህላዊ መዚቃ ለተደራጁ የኪነት ቡድኖች የተሟላ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም በሚል የቀረበው የባለሙያዎች ቅሬታ << ትክክለኛ >> በማለት የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አብቶ ይስማሙበታል። አቶ አብቶ በማያያዝም << ክልሉ ካለው ሰፊ የብሄረሰብ ስብጥር አንፃር ሁሉንም ባህላዊ አልባሳትና የሙዚቃ መሳሪያዎች ባለው ውስን የበጀት ሀብት ምክንያት በአንድ ጊዜ ሟሟላት  ያስቸግራል ። ይሁንእንጂ ቢሮው ምንም አንኳን በቂ ነው ባይባልም ጉድለቶቹን በሂደት ለሟሟላት ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ ይገኛል >> ብለዋል።

በደቡብ ክልል ሰፊ ባህላዊ ሀብቶች ቢኖሩትም እስከአሁን ሀብቱን ከማስተዋወቅ ባለፈ ጥበቡን ለገበያ በመሸጥ ሙያተኞችንና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለተቻል የሚናገሩት የቢሮው ምክትል ሃላፊ በቀጣይ መንግስት እና ፍላጎቱ ያላቸው ባለሀብቶች በዘርፉ ሊሰማሩ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ሊመቻቹ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

 

ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች