የቡድን 20 ጉባዔ በሀምበርግ | ዓለም | DW | 06.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የቡድን 20 ጉባዔ በሀምበርግ

የኤኮኖሚ ይዞታቸው ጠንካራ የሚባሉት የቡድን 20 አባል ሀገራት ር/ብሔር እና መራህያነ መንግሥት ነገ በጀርመን በሀምበርግ ከተማ የሁለት ቀናት ጉባዔ ይጀምራሉ።የአስተናጋጇ ሀገር ጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንዲህ እንዳሁኑ ብዙ ልዩነቶች ታይተውበት የማይታወቀውን የቡድን 20ን ጉባዔ በማስተናገዱ ላይ ብዙ ስራ እንደሚጠብቃቸው ተገምቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:48

«የቡድን20 ጉባዔ ትልቅ ተግዳሮት ተደቅኖበታል።»፣ ሜርክል

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በ12 ዓመቱ የአመራር ዘመናቸው በተለያዩ ጉባዔዎች መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም ጉባዔዎችን አዘጋጅተው አስተናግደዋል። በጎርጎሪዮሳዊው በ2007 ዓም በሀይሊገንዳም ከተማ  የቡድን ስምንት ጉባዔ፣ በ2015 በባቫሪያ የኤልማው ከተማ  የቡድን ሰባት ጉባዔ ይጠቀሳሉ፣ አሁን ደግሞ በሀምበርግ ከተማ ትልቅ ጉባዔ ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል። በኤኮኖሚ ይዞታቸው ጠንካራ ከሚባሉት የቡድን 20 አባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራህያነ መንግሥት በተጨማሪ ከመላ ዓለም ከማንኛውም ጊዜ በተለየ በርካታ እንግዶችም ለሁለት ቀናት ጉባዔ ወደ ከተማይቱ ይመጣሉ።ከ65 ሀገራት የተውጣጡ 4,800 ጋዜጠኞች ተመዝግበዋል።
አንጌላ ሜርክል እንደሚሉት፣ የሀምበርግ ጉባዔ በጉባዔው ተሳታፊዎች መካከል በብዙ ጉዳዮች ላይ በተፈጠረው ልዩነት የተነሳ  ትልቅ ተግዳሮት ተደቅኖበትል፣ ይህም ጉባዔውን ካሁን ቀደሞቹ ሁሉ የተለየ አድርጎታል። 
«ትልቅ(ዋነኛ) የሚባሉትን ሶስቱን ጉዳዮች እጠቅሳለሁ፤ ሽብርተኝነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የንግድ ማከላከል አሰራር እና ሌሎች ነጥቦች በጉባዔው አጀንዳ  ተካተዋል። ዓለም አልተረጋጋችም። ከሌላው ጊዜ በተለየም  ልዩነት ይታይባታል። »

ይኸው ልዩነት በመጀመሪያ ደረጃ  በዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት፣ በሩስያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን እና በቱርክ ፕሬዚደንት ረቼፕ ጠይብ ኤርዶኻን ርምጃዎች ጎልቶ ይታያል። በሀምበርግ ጉባዔ የሚካፈሉት ሶስቱም መሪዎች የራሳቸውን ጥቅም ማስቀደማቸው እንደማይቀር ይገመታል።  ኤርዶኻን፣ ምንም እንኳን ጀርመን መንግሥት ባይፈቅድላቸውም፣ ጉባዔውን በሀምበርግ ለሚኖሩት ቱርካውያን ንግግር ለማድረግ ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ። ትራምፕም ከፑቲን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ሊገናኙበት አስበዋል። ትራምፕ እና ፑቲንም  ከዩክሬይን ቀውስ እስከ ሶርያ ጦርነት እና በሩስያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ፣ እንዲሁም፣ ሩስያ በዩኤስ አሜሪካ ምርጫ ላይ አሳረፈችው የሚባለው ተፅዕኖን የመሳሰሉ በርካታ የሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች አሉ። ከዩኤስ አሜሪካ ብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ ኤችአር ማክማስተር እንደተሰማው፣ ትራምፕ  በሀምበርግ ጉባዔ ወቅት ምዕራቡ ከሩስያ ጋር «ገንቢ ግንኙነት» እንዲፈጥር ጥረት ያደርጋሉ። ትራምፕ በጉባዔው መነሳት አለባቸው ከሚሏቸው ጉዳዮች መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው ግዙፉ የብረት ምርት አንዱ ሲሆን፣ በምርቱ ላይ ገደብ እንዲያርፍ ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ግን፣ ሀገራቸውን ከፓሪሱ የአየር ንብረት ውል ያስወጡበትን ውሳኔአቸውን ለመቀየር አይፈልጉም። ያም ቢሆን ግን፣ ሜርክል ከሁሉም የስብሰባው ተካፋዮች ጋር ባንድነት በመስራት በወቅቱ በዓለም ለሚታዩት ችግሮች በጋራ መፍትሄ ለማፈላለግ እንደሚጥሩ ገልጸዋል። 
« ዓላማዬ ጉባዔው የቡድን 20 ሀገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራህያነ መንግሥት ለዓለም ያለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት በሚገባ እንደተረዱት እና ይህንኑ ኃላፊነታቸውንም እንደሚወጡ ቁርጠነታቸውን የሚያሳዩበት ምልክት እንዲያስተላልፍ ነው። »
ጀርመን በቡድን ሀያ ፕሬዚደንትነቷ ወቅት ያስቀመጠችው አንዱ ዋነኛ መወያያ ነጥብ  ከአፍሪቃ ጋር የሚኖረውን ትብብር የሚመለከት ሲሆን፣ ከልማቱ ርዳታ ጎን ተጨማሪ   ባለሀብቶችን ወደ አፍሪቃ ለመሳብ የሚያስችል «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ » የተሰኘ አንድ ንድፈ ሀሳብን አዘጋጅታለች። 


 ዛቢነ ኪንክል/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic