የቡድን 20 ጉባኤ ዉጤትና ዉድቀት | ዓለም | DW | 10.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የቡድን 20 ጉባኤ ዉጤትና ዉድቀት

ዶናልድ ትራምፕ ሐገራቸዉን ለማስቀደም ከነባር ወዳጅ፤ታማኝ፤ተባባሪዎችዋ እየነጥሉ ጋዜጠኛዉ እንዳለዉ ከትልቅ መሪነት ቁል ቁል እየጋለቧት ነዉ።የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬሳ ሜይ እና ተከታዮቻቸዉ ደግሞ ትልቅ ሐገራቸዉን ከትልቁ ማሕበር እንድትነጠል አስወስነዉ ብቻዋን ለመንዳት ደፋ ቀና እያሉ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:52

የቡድን 20 ጉባዔ ውጤት እና ውድቀት

የካፒታሊስቱን ሥርዓት ባጠቃላይ፤ የቡድን 20 ጉባኤን በተለይ በመቃወም የጀርመንዋን ታሪካዊ፤ ሐብታም፤ ትልቅ የወደብ ከተማ ሐምቡርግን ያመሰቃቀሉት ሰልፈኞች «ከቡድን 20፤የጅምላ ዳንስ ይሻላል» እያሉ ጥላቻቸዉን ከምግባራቸዉ በፊት በቃል ገልፀዉት ነበር።መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በመሩት ትልቅ ጉባኤ ሰበብ፤ ትልቂቱ የትዉልድ ከተማቸዉ በአመፅ-ግጭት በመተራመስዋ ማዘናቸዉን መግለፃቸዉም የብልሕ መሪነታቸዉን ልክ አመልካች ነዉ።የጉባኤዉን ዉጤት «አርኪ» ማለታቸዉን ግን ብዙ ታዛቢዎች ካንገት እንጂ ካጀት መሆኑን ተጠራጥረዉታል።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ብዙ ብለዉ፤ምንም ሳይሉ፤ ልጃቸዉን ተክተዉ ግን ከ19ኙ አቻዎቻቸዉ ተነጥለዉ የመመለሳቸዉን ያክል ብዙዎችን በትችት፤ በፌዝ-ምፀት አንድ ያደረገ የለም።

በ2008 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር) ዩናይይትድ ስቴትስን ያሽመደመደዉ የምጣኔ ሐብት ድቀት የመላዉን ሐብታም ዓለም ሐብት ሲያቀልጠዉ ወላፈኑ ሳይገላምጣቸዉ ያለፉ ሁለት ሐገራት ነበሩ።እስያቱ ቻይና እና አዉሮጳይቱ ጀርመን።የአንጌላ ሜርክሏ ጀርመን ከምጣኔ ሐብቱ ተምች ማምለጥ ብቻ ሳይሆን የአየርላንድ፤የፖርቱጋል፤የስጳኝ እና የግሪክ የተንኮታኮተ ምጣኔ ሐብት ትቢያዉን እያራገፈ እንዲያንሰራራ ከማንም ቀድማ ደርሳለች።የኢጣሊያ እና የፈረንሳይ ጠንካራ ምጣኔ ሐብት ሐዲዱን ስቶ እንዳይሾር በማድረጉ ጥረትም ቀዳሚዋ የሜርክሏ ጀርመን ናት።

ብዙ ስደተኞች በመቀበል ከወቀሳዉ በላይ ምሥጋና፤ ስደተኞች አዉሮጳ እንዳይገቡ በማገዱ ሥልት ከምስጋናዉ እኩል ወቀሳን ያተረፈችዉም የአዉሮጳ የምጣኔ ሐብት «እሪቋ» ሐገር ናት። ጀርመን።ጀርመን የአፍሪቃን የድሕነት አዙሪት ለመስበር ይረዳል የተባለዉን አዲስ ዕቅድ ይዛ ብቅ ብላለችም።ትላልቅ የአረብ ቱጃር መንግስታት ትንሽ

ወገናቸዉን ለመቅጣት እራሳቸዉን «ድዉይ» ሲያደርጉ የትራምፕዋ አሜሪካ ለሁለቱም የቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር ጦር መሳሪያ ለመላክ ስትዘጋጅ፤ የሜርክሏ ጀርመን አስታሪቂ ዲፕሎማትዋን ነዉ የላከችዉ።

ጀርመኖች «ሙቲ» እማማ እንደማለት የሚያንቆለጳጵሷቸዉ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፖለቲከኛ እንጂ ነብይ ወይም እናት አይደሉም። መስከረም ላይ ምርጫ አለባቸዉ።ከጀርመን አልፎ አዉሮጳን አዳርሶ አፍሪቃ እና መካከለኛዉ ምሥራቅ የናኘዉ በጎ ስም ዝናቸዉ እንደደመቀ ሐምሌና ነሐሴን ተዘናግሮ ለመስከረሙ ምርጫ ዳግም ባለድል እንዲያደርጋቸዉ ለቡድን 20 ጉባኤ ስኬት ጠብ-ርግፍ ቢሎ በርግጥ አያስወቅሳቸዉም።የጉባኤዉ ተቃዋሚዎች ላዛዥ-ለገራዥ አልበገር ብለዉ ሐሙቡርግን የዱላ-ድንጋይ መከሳከሻ፤ የእሳት-ዉሐ መራጪያ አዉድ ማድረጋቸዉ ግን የሜርክልን ሥልት እና ፍላጎን የሚያኮሰምን ነዉ።

«ይሕ የቡድን 20 ጉባኤ በሚደረግበት ወቅት የታየዉን ለከት ያጣ አመፅ እና በፖሊሶች ላይ በተደጋጋሚ የደረሰዉን ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት አጥብቄ አወግዛለሁ።የተፈፀመዉ ዘረፋ፤ቃጠሎ፤ በፖሊሶች ሕይወት ላይ ያነጣጠረዉ ጥቃት በምንም መንገድ ትክክል ሊባል አይችልም።በቀላሉ ልናገር።እንዲሕ አይነቱ ድርጊት ፖለቲካዊ ትችት ሊባል ወይም የሰዎች ኑሮ ለመለወጥ የሚደረግ ትግል አካል ነዉ ሊባል አይችልም።»

በአመፅ ግጭቱ የደረሰዉ ጥፋት መጠን  ገና አልታወቀም።የቡድን ሃያ የመሪዎች ጉባኤ ከተጀመረ ጀምሮ የዘንድሮዉን ያክል ጠንካራ ተቃዉሞ ገጥሞት ግን አያዉቅም።ወይዘሮ ሜርክል ጉባኤተኞችን ከሸኙ በኋላ «የጥፋት-ጥገና» ለማድረግ እየጣሩ ነዉ።የጉባኤዉን ዉጤት ሜርክል አስደሳች ብለዉታል።ለመደሰታቸዉ የጠቀሱት አብነት ግን ከብዙዎቹ የጉባኤዉ ርዕሶች አንዱን ነዉ።                             

«ጀርመን ያቀረበችዉ ሐሳብ ጠንካራ ድጋፍ ማግኘቱ እና ጥልቅ ዉይይት በመደረጉ  በጣም ተደስተናል።ይሕም ከአፍሪቃ ጋር በሚመሠረት ወዳጅነት ቡድን 20 ለአፍሪቃ (ልማት) ኃላፊነቱን መዉሰዱ ነዉ

።አዲስ ሐሳብም ተካትቶበታል።አዲስ የተጨመረዉን ሐሳብ የያዘ ተጨማሪ ሰነድ አፅድቀናልም።Compact with África በተባለዉ ሰነድ መሠረት ከያንዳዱ የአፍሪቃ ሐገራት ጋር ስምምነት ይደረጋል።የተለመደዉን የልማት ርዳታ  ብቻ ሳይሆን የግል መዋዕለ ነዋይም አፍሪቃ ዉስጥ ሥራ ላይ እንዲዉል የሚበረታታ ነዉ»

አፍሪቃን ወክለዉ በእንግድነት የገኙት የጊ እና የሴኔጋል መሪዎችም እንደ ሜርክል ሁሉ ጉባኤዉ ሥለ አፍሪቃ ባሳለፈዉ ዉሳኔ ረክተዋል።የማሕበሩ ቋሚ አባል የሆነችዉ ብቸኛይቱ አፍሪቃዊት ሐገር ግን ደቡብ አፍሪቃ ናት።አንዴ በሙስና ሌላ ጊዜ በዋልጌነት፤ደግሞ ሌላ ጊዜ የሱዳኑን መሪ አላሰሩም በሚል ዉንጀላና ሴራ የሰለለችዉ የሥልጣን  ገመዳቸዉ ጨርሳ እንዳትበጠስ የሚቀጣጥሉበትን ብልሐት እያዉጠነጠኑ ሐሙቡርግ ደርሰዉ የተመለሱት ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ ሥለ አፍሪቃ ልማትና ዕድገት የሚያስቡበት ጊዜ ያገኙ ይሆን?

ሜርክልን ያስደሰተዉ የአፍሪቃ ጉዳይ ዉሳኔ ከተላለፈበት ባንዱ ጉባኤ ላይ የዓለማችንን ብቸኛ ልዕለ ሐይል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስን የወከሉት ፕሬዝደንቷ አልነበሩም።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ፤ የፀጥታ ኃላፊዋ፤ ወይም ሌላ ባለሥልጣን አልነበሩም።የነበሩት የፕሬዝደንቱ ልጅ ናቸዉ።ወይዘሮ ኢቫንካ ትራምፕ።

ወይዘሮ ኢቫንካ ትራምፕ እንደ አሜሪካኖቹ ፖለቲካዊ ይትበሐል በሕዝብ የተመረጡ ፖለቲከኛ አይደሉም።በፕሬዝደንቱ ተሾመዉ በሕዝብ በተመረጡ የምክር ቤት እንደራሴዎች ሹመታቸዉ የፀደቀላቸዉ ሚንስትር ወይም አምባሳደር አይደሉም።በሕግ የሚታወቁ አማካሪ አይደሉም።ግን የፕሬዝደንት ልጅ ናቸዉ።

የሕዝብ መብት ተጣሰ፤ ሕግ ፈረሰ እያሉ ሐገር የሚያፈርሱት አሜሪካኖች መሪያቸዉ እና ልጃቸዉ ሐምቡርግ ላይ ያደረጉትን ወዲያዉ አዉቀዋል።

መብታቸዉን ማስከበር ሥለመቻላቸዉ ወይም አስከባሪ ኃይል ሥለመፈለግ-አለመፈለጋቸዉ እስካሁን ያሉት የለም።ጉባኤዉን የተከታተለዉ አዉስትሬሊያዊ ጋዘጠኛ ቻሪስ ቻሕማን እንደሚለዉ ግን ፓሬዝደንት ትራምፕ ዓለምን ንቀዉ ትልቅ ሐገራቸዉን እያስናቁ ነዉ።

«የተገነዘብነዉ ነገር ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ዓለም መሪ ያላትን ሥፍራ በፍጥነት እያዳከሙት መሆናቸዉን ነዉ።ሐገራቸዉን ከተቀረዉ ዓለም መነጠሉ፤ ወዳጆችዋን ማደናገር፤ አሜሪካን ማኮስመኑ ይዞላቸዋል።አንዳዶች በአሜሪካ መኮስመን የተደሰቱ ይመስላሉ።ሁሉም ካለቀ በኋላ ግን የሚቆጨን ይመስለኛል።ይሕ ትራምፕ በጣም እንደሚወዱት ለሚናገሩት ለምዕራቡ እሴት ትልቅ ሥጋት ነዉ።»

«አሜሪካ ትቅደም» ነዉ የትራምፕ መፈክር።ድፍን ዓለም የተስማማበትን የዓየር ንብረት ለዉጥን ሥምምነትን ዉድቅ በማድረጋቸዉ ከአስራ-ዘጠኙ መሪዎች የተነጠሉትም አሜሪካን ለማስቀደም ነዉ።ከዋናዉ ጉባኤ ይልቅ ልዩ ትኩረት የሰጡትም ከሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ላደረጉት ዉይይት ነዉ።ሥለ ዉይይቱ ዉጤት ግን ፑቲን እንጂ ትራምፕ ያሉት የለም።

«እንዴት እንደሚተረጎም አላዉቅም ግን  በቴሌቪዥን የማየዉ ትራምፕ ከእዉነተኛዉ ሥብዕናቸዉ የተለየ ነዉ።በግልፅ የሚናገሩ ናቸዉ።ቃለ መጠይቆችን በቅጡ ይገነዘባሉ፤ጥያቄዎችን ተንትነዉ በፍጥነት ይመልሳሉ።ትናንት በጀመርነዉ ሁኔታ እንቀጥላለን ብዩ አስባለሁ።የሚያስፈልገንን ትብብር ማሻሻል እንችላለን የሚል እምነት አለኝ።»

ዶናልድ ትራምፕ ሐገራቸዉን ለማስቀደም ከነባር ወዳጅ፤ታማኝ፤ተባባሪዎችዋ እየነጥሉ ጋዜጠኛዉ እንዳለዉ ከትልቅ መሪነት ቁል ቁል እየጋለቧት ነዉ።የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬሳ ሜይ እና ተከታዮቻቸዉ ደግሞ ትልቅ ሐገራቸዉን ከትልቁ ማሕበር እንድትነጠል አስወስነዉ ብቻዋን ለመንዳት ደፋ ቀና እያሉ ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ከወዳጅ ተከታዮችዋ እንዳትነጠል ትራምፕን የሚማፀኑት ሐገራቸዉ ከአዉሮጳ ሕብረት እንድትነጠል ያስወሰኑት፤ዉሳኔዉን ገቢር ለማድረግ ደፋ ቀና የሚሉት ቴሬሳ ሜይ መሆናቸዉ ብዙዉን ታዛቢ እፁብ ድንቅ እያሰኘ ነዉ።

 «እዚሕ እንዳሉት እንደሌሎቹ መሪዎች ሁሉ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ ዉል ለመዉጣት በመወሰንዋ በጣም ቅር ብሎኛል።ፕሬዝደንት ትራምፕ ዳግም የፓሪሱን ሥምምነት እንዲቀየጡ እጠይቃለሁ።ብሪታንያ ለፓሪሱን ዉል እና የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቋቋም ያላት ቁርጠኝነት እንደሁል ጊዜ  ጠንካራ ነዉ።»

የደቡብ አሜሪካዋ የምጣኔ ሐብት መዘዉር የብራዚሉ ፕሬዝደንት ሚሼል ቴመር እንደ ጄኮብ ዙማ ሁሉ የሙስና ቅሌት ከትልቁ ቤተ-መንግስታቸዉ ገፍትሮ እንዳይጥላቸዉ እየተፍረመረሙ ነዉ።ለነገሩ ቤተ-መንግሥቱን የያዙትን አለቃቸዉን አስወርዉረዉ ነበር።የአርጀቲናዉ ፕሬዝደንት ማወሪቾ ማክሪ ትኩረታቸዉ የቡድን 20ን የመሪነት ሥልጣን ከሜርክል ሲረከቡ የሚመሩት ሥልት ነዉ።

የአረቡ ዓለም ብቸኛ

ተወካይ የሳዑዲ አረቢያዉ ንጉስ በጉባኤዉ ላይ አልተካፈሉም።እንድሜም፤የጤና እጦትም የተጫቻናቸዉ ንጉስ ሠልማን ትንሺቱን ጎረቤታቸዉን ቀጠርን የሚያንበረክኩበትን ሴራ ከሸረብ የሚተርፍ አቅም ማግኘታቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።

ሳዑዲ አረቢያዎች ሰዉ ሞልቶ ተርፏቸዉ ሰዉ ያባርራሉ።የባልስልጣን ግን እጥረት ሳይኖርባቸዉ አይቀርም።አልጋወራሽነቱንም፤ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነቱንም፤ መከላከያ ሚንስትርነቱም ጠቅልለዉ የያዙት የ31ድ ዓመቱ የንጉሱ ልጅ  ከዓለም መሪዎች ጋር የሚያጠፉት ጊዜ ያገኙ አልመሰሉም።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ እና የደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት ሙን ጄን ኢን ትኩረት-ሥጋታቸዉ እኒያ «ከይሲ» የሚሏቸዉ ኪም ጆንግ ኡን ያን መከረኛ ሚሳዬል ወይም ኑክሌር ማወንጨፍ አለማወንጨፋቸዉ ነዉ።የቱርክ  ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻን ጉባኤዉ ላይ የተገኙት እንደ ሩሲያዉ አቻቸዉ ሁሉ ከምዕራብ አዉሮጳ መሪዎች ጋር በሚወዛገቡበት መሐል ነዉ።የሜክሲኮዉ ፕሬዝደንት ኤንሪኮ ፔና ኒቶ የሰሜን ጎረቤታቸዉ ልዕለ ኃያል ሐገር መሪ ድንበር ላይ ለሚያስገነቡት አጥር ወጪዉን ቢጠይቋቸዉ የሚመልሱትን አሰናድተዉ ነዉ።

ጉባኤዉን በሙሉ እርጋታ የተሳተፉ የመሠሉት የቻይና፤የኢንዶኔዢያ፤ የአዉስትሬሊያ፤የፈረንሳይ፤ የሕንድ፤ የኢጣሊያና የካናዳ መሪዎች ናቸዉ።

አሸባሪነትን መዋጋት የሚለዉን ርዕሥ ያክል ሁሉንም ያግባባ የለም።ጉባኤተኞች ሥለ ንግድ ባደረጉት ክርክር የፕሬዝደንት ትራምፕን ዛቻና ፉከራ ተቋቁመዉ  መግባባት ላይ መድረሳቸዉ ከአፍሪቃዉ ጉዳይ ቀጥሎ ለሜሪክል አስደሳች ለጉባኤዉ ድል ነዉ-የሆነዉ።

«ንግድን በሚመለከተዉ ርዕሥ ላይ ከፍተኛ ክርክር መደረጉ ግልፅ ነዉ።ገበያዎች ክፍት መሆን እንደሚኖርባቸዉ በግልፅና በተገቢዉ መንገድ በመናገራችን ተደስቻለሁ።ይሕ ማለት የኔብቻ ማለትንና ተገቢ ያልሆነ የንግድ ሥርዓትን ከመዋጋት የሚቆጠር ነዉ።»

የዘላቂ ልማት ዕቅድ፤ ሴቶችን የምጣኔ ሐብት ባለቤት ማድረግ፤ ስደተኞች አዉሮጳ እንዳይገቡ ማገድ የሚሉ ርዕሶችን ጉባኤዉ እንዳለ ተቀብሏቸዋል

።ለየገቢራዊነታቸዉ ግልፅ ዕቅድ ግን አልነደፈም።«ሁሉን አቀፍ ዕድገት» ለተባለዉ ትልቅ ርዕሥ ዋና መሠረቱ ገበያን ክፍት የማድረጉ ሥምምነት ነበር።ጉባኤተኞች ንግድን ወይም ገበያን መክፈትን በሚለከተዉ ርዕሥ ላይ «ተግባቡ» እንጂ አልተስማሙም።

ሜርክል ሥለ ምርጫ እያሰቡ፤ ትራምፕ «አሜሪካ ትቅድም» እያሉ፤ ሜይ ትልቅ ሐገራቸዉን ከትልቁ ማሕበር እያባረሩi፤ፑቲን ካዉሮጳ-አሜሪካኖች፤  ኤርዶኻን ከአዉሮጶች ጋር እየተነታረኩ እንዴት ይግባቡ።አቤ እና ሙን ከሰሜን ኮሪያ ኑኬር-ሚሳዬል፤ ዙማ ና ቴሜር ከሙስና ቅሌት የሚያመልጡበትን ዘዴ እያወጡ-እያወረዱ ሥለ ዓለም ልማትና ዕድገት እንዴት ይጨነቁ።ብቻ መጡ፤ አወሩ፤ በሉ ጠጡ ሔዱ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

 

Audios and videos on the topic