የቡድን-፰ ዓቢይ ጉባኤ በሲ አየላንድ/ጆርጅያ | ኤኮኖሚ | DW | 10.06.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የቡድን-፰ ዓቢይ ጉባኤ በሲ አየላንድ/ጆርጅያ

በዩኤስ ፈደራዊ ክፍለሀር ጆርጅያ ሲ-አይላንድ ላይ ዓቢዩን ጉባኤ የሚያካሂዱት የሰባቱ ዓበይት እንዱስትሪ-ሀገራትና የሩሲያ ርእሳነ-ብሔርና መራህያነ-መንግሥት ዛሬም ፋታ በማይሰጥ ሰፊ ውይይት እንደባተሉ ናቸው። ሆኖም፣ የዛሬው ውይይት ሂደት እንዳሳየው፣ በብዙ ጥያቄዎች ረገድ መሪዎቹ ተመሳሳይ አመለካከት ነው ያላቸው---ለምሳሌ በዓለም ኤኮኖሚ ወቅታዊ ሁኔታና እየናረ በተገኘው የነዳጅ ዘይት ዋጋ አኳያ ግምገማቸው ተቀራራቢ ነው። ግን አስተናጋጁ ፕሬዚደንት ቡ

default

ሽ ስለ ማዕከላይ ምሥራቅና ስለተጎራባቾቹ አካባቢዎች ያንቀሳቀሱት ሐሳብ ብዙ የሚያከራክር ሆኖ ነው የተገኘው።

በዩኤስ አሜሪካ ፈደራዊ ክፍለሀገር ጆርጅያ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ጠረፍ ላይ በሚገኘው መዝናኛ ቦታ ሲ አይላንድ ለጉባኤው ተሳትፎ የተሰበሰቡት መሪዎች በሚያደርጉት የሐሳብ ልውውጥ ረገድ አግባቢው ነጥብ በልቀት የሚንፀባረቅ ሆኖ ነው የሚታየው። የዓቢዩ ጉባኤ ኣስተናጋጅ ፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ ይኸው ጉባኤ ለጋራው ዓላማ ዓይነተኛውን ምልክት የሚፈነጥቅ እንደሚሆን ነው ተሥፋ የሚያደርጉት። ለዚሁ የጋራ ስሜት አዎንታዊውን ሁኔታ የፈጠረው፥ የተባ መ ፀጥታ ጥበቃ ምክርቤት ስለ ኢራቅ የቀረበውን ረቂቅ ውሳኔ ባለፈው ማክሰኞ በሙሉ ድምጽ የተቀበለበት ድርጊት ነው። ይኸው አዎንታዊ ሁኔታ ነበር ትናንት የስምንቱ ክበብ ውጥረት በሌለበት መንፈስ የኤኮኖሚ ጥያቄዎችን ለማውሳትና ለጉባኤው ተሳትፎ ከተጋበዙት ዓረባውያን መሪዎችም ጋር በጽሞና ለመነጋገር፣ ፕሬዚደንት ቡሽ ለማዕከላይ ምሥራቅ ያቀረቡት የሰላም ዕቅድ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ያስቻለው። ግን የፖለቲካና የኤኮኖሚ ተሐድሶ ለውጥ እንዲኖር ፕሬዚደንት ቡሽ ያንቀሳቀሱት ሐሳብ በውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ እንደመግባት ተቆጥሮ ነበር በዓረባዊው ዓለም ውስጥ የተነቀፈው። ይኸው ጉዳይ በራሱ በቡድን-፰ ዙሪያም ነበር ብዙ ክርክር የተፈራረቀበት። አሁን ታዲያ፥ “ጥምረት ለዕድገትና ለጋራው መፃኢ እጣ” በተሰኘው ርእስ ላይ ውይይት እንዲደረግ ጥሪው ጎልቷል።

የሰሜንአትላንቲኩ የጋራ መከላከያ ኪዳን ድርጅት ናቶ ኢራቅ ውስጥ የበለጠ ያረጋጊነት ሚና መያዝ እንዳለበት ፕሬዚደንት ቡሽ ያጎሉት ማስገንዘቢያም ነበር ሂስን ያስከተለው። በዚሁ ጥያቄ ረገድ ቁጥብነትን ካሳዩት መሪዎች አንዱ የሆኑት ጀርመናዊው መራሄመንግሥት ጌርሃርት ሽረደር፥ ኢራቅ ውስጥ በሚወሰደው የመልሶ ግንባታ ርምጃ የጀርመንም እንዱስትሪ-ኩባንያዎች በተቻለ መጠን ብዙ ኮንትራቶችን ሊቀበሉ እንደሚችሉ ተሥፋ ያላቸው መሆኑን ግልጽ ነበር ያደረጉት። የፈረንሳይም ፕሬዚደንት ዣክ ሺራክ የፕሬዚደንት ቡሽ ማሳሰቢያ ተመዛዛኝ አይደለም በማለት ነበር ያጣጣሉት።

ለኢራቅ የእዳ ምኅረት የሚደረግበትም ጥያቄ ነበር የመጨረሻውን ስምምነት ሳያስገኝ የቀረው። ሆኖም፣ በፓሪሱ ክበብ ውስጥ የተጣመሩት አበዳሪ መንግሥታት በዚሁ ጥያቄ ረገድ አንድ ውሳኔ ላይ ሊደርሱ የሚችሉበት ገላጋይ ሐሳብ መከሰቱም ነው የተገለፀው። እንዲያውም፣ ጀርመናዊው መራሔመንግሥት ጌርሃርት ሽረደር ራሳቸው እንዳረጋገጡት፥ የጉባኤው ሂደት በጠቅላላው ሲታይ፥ ውይይቱ ሁሉ ፍሬነገሩን ያልሳተበትና፣ በጣም የጎላውን ወዳጃዊ ስሜት ያንፀባረቀ ነበር።

የቡድን-፰ መሪዎች ለዓለም ኤኮኖሚ ጥያቄዎችም ነበር ከፍተኛውን ትኩረት የሰጡት። የዓለም ኤኮኖሚ ከመሰናክል ይድን ዘንድ፣ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በተመዛዛኝ ደረጃ ላይ መረጋጋት እንዳለበት ያስገነዘቡት መራሔመንግሥት ሽረደር የነዳጅዘይት ዋጋ አሁን እየናረ ለተገኘበት ሂደት በተለይ አረጠኞችን ነው ተጠያቂ የሚያደርጉት።

በዩኤስ-አሜሪካው በጀት ውስጥ የተፈጠረው ግዙፉ ጉድለት የሚያሠጋቸው እንደሚሆን አውሮጳውያኑ የጉባኤ ተሳታፊዎች በግልጽ ቃላት ነበር ያስገነዘቡት። ሆኖም፣ በዶሃ/ቃታር የተጀመረው የንግድ መሰናክል ማስወገጃው ድርድር እንደገና መነቃቃትና መንቀሳቀስ እንደሚገባው ሁሉም ናቸው የተስማሙበት።

የቡድን-፰ ዓቢይ ጉባኤ ዛሬ በተለይ ያተኮረበት ጉዳይ የልማትን መርሕ ነበር የተመለከተው። በዓለም እጅግ ድሆቹ ሀገሮች የተሸከሙት ግዙፉ የውጭ እዳ እንዲቃለል የሚደረግበት መርሐግብር መራዘም እንዳለበትም ነው መሪዎቹ የተስማሙት። በ፫ ቀናቱ ጉባኤ መደምደሚያ ላይ አፍሪቃን በመወከል ከቡድን-፰ ሀገራት መሪዎች ጋር የሚነጋገሩት የደቡብ አፍሪቃ፣ የናይጀሪያ፣ የኡጋንዳ፣ የጋና እና የሴኔጋል ፕሬዚደንቶች “ለአፍሪቃ ልማት አዲስ አጋርነት”/በአሕጽሮት ኔፓድ የተሰኘውን የተሐድሶ ለውጥ መርሐግብር ነው የሚያወሱት።