የቡድን ሰባት ጉባኤና ተቃዉሞዉ | ዓለም | DW | 08.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የቡድን ሰባት ጉባኤና ተቃዉሞዉ

ቻይና ከተራ-አዳጊ ሐገርነት ወደ ዓለም ሁለተኛ ሐብታምነት ተመንድጋለች።ደቡብ ኮሪያ፤ ሕንድና ብራዚል ድሕነትን አራግፈዉ ጥለዋል።ወይም እያራገፉ ነዉ።ሶቬት ሕብረትና ይጎዝላቪያ ተፈረካክሰዋል።ጀርመን ተዋሕዳለች፤ኤርትራ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ምሥራቃዊ ቲሞር ነፃነት አዉጀዋል። ያ ቡድን ግን ከስድስት ወደ ሰባት፤ከሰባት ወደ ስምንት እንደገና ሰባት---

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:23
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
13:23 ደቂቃ

የቡድን ሰባት ጉባኤና ተቃዉሞዉ

የቀድሞዉ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ቫለሪ ዢስካርድ ደ ስታ በ1975 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የአምስቱን ሐገራት መሪዎች ለጉባኤ ሲጋብዙ ሥለ ወቅቱ የዓለም ሁኔታ «መደበኛ ባልሆነ ሥብስሰባ በእርጋታ እና ዘና ብለን እንነጋገር ብለዉ ነበር።የዘንድሮዉን ጉባኤ ያስተናገዱት የጀርመን ባለሥልጣናትም የባየሩን ተራራማ ዉብ መዝናኛ ሥፍራ የመረጡት የቡድን ሰባት ጉባኤተኞች ገለል፤ቀለል፤ ዘና፤ለቀቅ፤ ደልቀቅ ብለዉ እንዲነጋገሩ ነዉ።ወይም ነበር።ከቅዳሜ ጀምሮ ግን ለወትሮዉ ጥድፊያ፤ ወከባ፤ትርምስ የበዛበትን ዓለም በአርምሞ የሚመለከት የሚመስለዉ የጋርሚሽ-ፓርተንኪርሸን መንደር በተአስተናጋጅ ተስተናጋጅ ግርግር፤በሠልፈኛ ጩኸት ጫጫታ፤ በፀጥታ አስከባሪዎች ቱማታ፤ በመኪና ሔሊኮብተሮች ኩርኩርታ ይተራመስ ይዟል።

ብሪታንያዊዉ ጋዜጠኛ አንድሬዉ ሐሞንድ «በይፋ ያልታወጀ ሁለተኛዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት» ይለዋል ቡድን ሰባትን።«የሽሎስ ኤልማዉ ጉባኤም» ቀጠለ ጋዜጠኛዉ ቅዳሜ ባሳተመዉ መጣጥፉ፤«የቡድኑን አወዛጋቢ ሚና ከማረጋገጥ ባለፍ ሌላ አይጠበቅበትም።» በርግጥም ቡድኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ዓለም አቀፍ ማሕበር የዓለምን ሁለንተናዊ ሒደትና እዉነት መከታተልና መወሠን ከቻለ የሚወስነዉ በፀጥታ ምክር ቤቱ አማካይኝነት ነዉ።

ከምክር ቤቱ ቋሚ አባላት ወይም ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ካላቸዉ አምስት መንግሥታት ሰወስቱ (ታላቋ ብሪታንያ፤ፈረንሳይና ዩናይትድ ስቴትስ) የቡድን ሰባት አባላት ናቸዉ።በሠወስቱ ላይ የተቀሩት አራቱ (ጀርመን፤ኢጣሊያ፤ጃፓንና ካናዳ) ሲደመሩ ከዓለም የተጣራ ሐብት 65 ከመቶዉን ይቆጣጠራሉ።263 ትሪሊዮን ዶላር።

ሰባቱ መንግሥታት በቋሚነት በየጉባኤያቸዉ የሚያስከትሏቸዉ የአዉሮጳ ሕብረት እና የዓለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) የሚቆጣጠሩት ሐብት እና ሐይል ሲደመርበት ጋዜጠኛዉ እንዳለዉ ዓለም በርግጥ ከሰባቱ እንጂ የዓለም ከሚባለዉ ግዙፍ ማሕበር ብዙም ሊጠብቅ አይገባም።

ከሌሎቹ መሪዎች ቀድመዉ ከጉባኤዉ ሥፍራ የደረሱት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት የባራክ ኦባ መልዕክትም አወዛጋቢዉን እዉነት የሚያረጋግጥ ነዉ።

«ሥለ ምንጋራዉ የወደፊት ሁኔታ እንነጋገራለን።ሥራና ብልፅግናን የሚፈጥር የዓለም ምጣኔ ሐብት፤ ጠንካራና የበለፀገ የአዉሮጳ ሕብረትን ማፅናት፤በአትላንቲክ ማዶ-ለማዶ ሐገራት መካከል አዲስ የንግድ ሽርክና መመሥረት፤ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን መቃወም፤ፅንፈኝነን ከመዋጋት እስከ የዓየር ንብረት ለዉጥ ያሉትን እንወያያለን።»

ሰባት ቢሊዮኑ የዓለም ሕዝብ ሰባቱ መሪዎች በሚቀይሱላት ቦይ መፍሰስ ግዱ ነዉ።ግዱን እዉነት አልቀበልም ያለ፤ ለማለት የሚቃጣዉም እስካሁን አልተሰማም።የዓለም ሁለንተናዊዉ ሒደትን ሲወስኑ ግን ባግባቡ ይወስኑ ባዮች በርግጥ ቢሊዮኖች ናቸዉ።ካለፈዉ ሳምንት እስከ ዛሬ በርሊን፤ሙንሽን (ሙኒክ)ኤልማዉ በየአደባባዩ የተሠለፉ፤የጮኹ፤ በየአዳራሹ የመከሩ የተናጋገሩትም የእኒያ ቢሊዮኖች ተቆርቋሪዎች ናቸዉ።

ከተፈጥሮ ሐብት አስከባሪዎች፤ እስከ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ ከጦርነት፤ረሐብ፤ ሙስና ተቃዋሚዎች፤ እስከ ፀረ-ካፒታሊስት ፖለቲካ አቀንቃኞች በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የጉባኤተኞች እርምጃ፤ዉሳኔ፤ዕቅድ ለዓለም ሠላም፤ለሕዝብ ፍትሕ፤ እኩልነት የሚበጅ እንዲሆን ተማፅነዋል።ጮኸዋል።ዛሬም-ጭምር።

ፕሬዝደንት ኦባማ እንዳሉት ዛሬ ተሰያት ላይ ያበቃዉ ጉባኤ ከተነጋገረባቸዉ ጉዳዮች አንዱ የአየር ንብረት ለዉጥን መቀነስ ነዉ።እሳቸዉ እንደሚሉት ግን የአየር ንብረት በካዩ ማን ሆነና። «ቡድን ሠባት የዓለም እጅግ ወሳኝ ሰዎች ናቸዉ።በዚሕም ምክንያት የተፈጥሮ ሐብት ለመጥፋቱ ተጠያቂ ናቸዉ።» ።እነሱ ደግሞ ካፒታሊስቱን ሥርዓት የሚቃወሙ ናቸዉ።

«እኒያ እዚያ የሚሰበሰቡት ሰባቱ የአንድ ሥርዓት ብቻ መሪዎች ናቸዉ።»የዓለም ሐብት የተነፈጋቸዉ ድሆች ተቆርቋሪዎች ደግሞ-እንዲሕ ይላሉ።«የልማት ርዳታ ላይ ሰላሳ ዓመታት ሠርቻለሁ።የዚሕ (ቡድን) መርሕ የሚያስከትለዉን መጥፎ ዉጤት አይቻዋለሁ።ሥለዚሕ መርሁን አቃወማለሁ።»

የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ታላላቅ እንግዶቻቸዉን የሚያስተናግዱበትን ያን ተራራማ የጥንታዊ ቤተ-መንግሥት መንደርን ጥንታዊ ባሕል ከዘመናዊነት ጋር የቀየጠ ብለዉታል።

«እዚሕ ክፍለ-ሐገር ባሕላዊና ዘመናዊነት በጥብቅ ተሳስረዋል።የጀርመን ምርጥ አካባቢ ነዉ።»ሜርክልና እንግዶቻቸዉ ከሠልፈኛዉ ተቃዉሞ፤ጫጫት፤ ግርግር ርቀዉ እንዲነጋገሩ አስራ-ሰባት ሺሕ ፖሊስ አካባቢዉን ከብቧል።ተቃዉሞዉ ጠንከር ካለ ደግሞ ሌሎች ሁለት ሺሕ ፖሊሶች ተወርዉረዉ ከጉባኤዉ ሥፍራ ለመድረስ በተጠንቀቅ ላይ ናቸዉ።

ጀርመንን ከኦስትሪያ ጋር የሚያገናኘዉ ድንበርን እንዲጠብቁ ደግሞ በሺሕ የሚቆጠሩ ፀጥታ አስከባሪዎች ዘምተዋል።የጉባኤዉ ሥፍራና አካባቢዉ ከአየር በሔሊኮብተር፤ከምድር፤ የዘመኑን ረቂቅ መሳሪያ በታጠቁ ሐይላት ይጠበቃል።የፖሊስ ቃል አቀባይ ፔተር ራይሽል ዉልፊጥ የሚል ካለ እኛም አለን ይላሉ።«በሁለተኛዉ በኩልም በግልፅ የቆመ ሐይል አለን።እንዲያዉ ምናልባት የጨዋታዉን ሕግ የሚጥሱ ካሉ እኛም እዚያዉ እንዳለን ያዉቃሉ።»

ጉባዉን ለማስተናገድ ከ140 ሚሊዮን በላይ ዩሮ ወጥቷል።ከትናንት ወዲያ ቅዳሜና ትናንት ወደ አካባቢ ለመጠጋት የሞከሩ ሠልፈኞችን ፖሊስ እያንጠለጠለ ካካባቢዉ ወስዷቸዋል።የፖሊስን እርምጃ የተቃወሙ ሰልፈኞች ፤ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዉም ነበር።የቡድን ሰባትን መርሕ የሚቃወሙት ክርስቶፍ ፕሬሾፍ ይጠይቃሉ፤የፖሊስ ግዛት ማለት ከዚሕ በምን ይለያል-እያሉ።«ለኔ፤ የገዢዎችን የሐብት ክምችትና የኩባንዮቻቸዉን ፍላጎት የሚቃወም (እንቅስቃሴ) ካለ የፖሊስ (የሐይል) አስተዳደር ለመመስረት ወደኋላ እንደማይሉ የሚጠቁም ነገር ነዉ የሚታየኝ።»

ፕሬዝደነት ቫለሪ ዢስካር ደ ስታ በ1975 የዛሬዉን ቡድን ሲያሰባስቡ የቡድኑ አባላት ስድትስት ነበሩ።ፈረንሳይ፤ ብሪታንያ፤ኢጣሊያ፤የያኔዋ ምዕራብ ጀርመን፤ዩናይትድ ስቴትስና ጃፓን።ባመቱ ካናዳ ተቀየጠችና ሰባት ሆኑ።

የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ከተፈረካከስች በኋላ ሞስኮ ላይ እንዳዲስ የተዋቀረዉ የሩሲያ መንግሥት ተመልሶ ወደ ኮሚንስታዊዉ ሥርዓት እንዳይገባ ለማባበል ሲባል የሩሲያ መሪዎች ከ1994 ጀምሮ ለአራት ዓመት ያሕል በእንግድነት ኋላ ደግሞ በሙሉ አባልነት ጉባኤዉን ይሳተፉ ነበር።

ከ1994 እስከ 1998 ድረስ የነበረዉ የቡድኑ ስብጥር ጋዜጠኞችን ግራ በማጋባቱ አንዳዴ ፖለቲካዊ ቡድን 8፤ ሌላ ጊዜ ቡድን 7+1 እያሉ ለመጥራት ተገደዉ ነበር።ከ1998 ጀምሮ በቡድን ስምንትነቱ የፀናዉ ስብሰስብ ሩሲያ ባለፈዉ ዓመት መጋቢት ከአባልነት በመታገዷ የቡድኑ አባላት ሰባት ብቻ ሆነዋል።

ወትሮም ከምጣኔ ሐብት። ይልቅ በጦር ሐይል አቅሟ፤ ኮሚንስታዊዉ ሥርዓቷ እንዳያንሠራራ ለማባበል ሲባል፤ ቡድኑን እንድትቀየጥ የተፈቀደላት ሩሲያ ከቡድኑ አባልነት የተወገደችዉፕሬዝደንት ባራክ አባማ ዩክሬንን በመዉረሯ ባሉት ምክንያት ነዉ።የሩሲያ ባለሥልጣንት አሁን በቅርቡ ከሠርቢያ እስከ አፍቃኒስታን፤ ከኢራቅ እስከ ሊቢያ የሆነዉን እየጠቃቀሱ «ወራሪስ ባለበት አለ» ዓይነት መልስ አላቸዉ።

የዩክሬኑ ቀዉስ እንደ አሜሪካ ፖለቲከኞች «ወረራ» ተባለ፤ ወይም የርስ በርስ ጦርነት ሰባቱ መሪዎች ትናንትና ዛሬን ጨምሮ ከተነጋገሩባቸዉ ትላልቅ ርዕሶች አንዱ ነዉ።ሰባቱ መሪዎች ዛሬ በተጠናቀቀዉ ጉባኤያቸዉ እንደሌላዉ ርዕስ ሁሉ ሥለዩክሬን ቀዉስም «አዲስ» ያሉትን ዉሳኔ ማሳለፋቸዉ አልቀረም።የዩክሬንን አማፂያንን ትረዳለች ወይም ዩክሬንን ወርራለች የሚሏትን ሩሲያን ከማዉገዝ ያለፈ ለዩክሬን ባጭር ጊዜ ሠላም የሚያወርድ እርምጃ ግን የለም።

ብዙ ታዛቢዎች እንደሚተቹት በርካታ ሕዝብ የሚያልቅበትን ፤ ብዙ መንግሥታትና ቡድናት የተነካኩበትን የዩክሬንና የሶሪያን ዓይነቱን ጦርነት ለማስቆምም ሆነ፤ ምዕራባዉያን መንግሥታት ከኢራንና ከሠሜን ኮሪያ ጋር የገጠሙትን ዉዝግብ በሠላም ማስወገድ የሚቻለዉ የሩሲያ ፍቃድና ይሁንታ ሲገኝ ብቻ ነዉ።

የሩሲያ ፈቃደኝነት የሚገኘዉ ደግሞ በማግለል ሳይሆን በማሳተፍ ነዉ።መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንደሚሉት ግን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የያዘችዉ አቋም እስካልተለወጠ ድረስ ይሕን በመሰለዉ የሐያል ሐብታሞች ጉባኤ ላይ እንድትካፈል አትጋበዝም።

«ሩሲያ ክሪምን በሕይል በመያዝዋ እና በዶኔትስክ እና ሉጋንስክ (ጦርነት) ጣልቃ በመግባትዋ ልዩነት እንዲፈጠር አድርጋለች።ሥለዚሕ፤ እኛ እስካሁን ደረስ ባለን እምነት ሩሲያ (ቡድኑን) ዳግም መቀየጥ አትችልም።»

የሶሪያ ጦርነት፤ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ ከሚጠራዉ አክራሪ ደፈጣ ቡድን ጋር የሚደረገዉ ዉጊያም ከመሪዎቹ ዋና ዋና ርዕሶች አንዱ ነበር።ISISIን ጨምሮ ዓለም አቀፍ አሸባሪነትን በመዋጋቱ ሒደት ላይ ሰባቱ መሪዎች ከአፍሪቃና ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ከጋበዟቸዉ ሰባት መሪዎች ጋር ተነጋግረዋል።ከአፍሪቃ ከተጋበዙት አምስት መሪዎች አንዱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ናቸዉ።

መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለማርያምን መጋበዛቸዉን በመቃወም ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ሙንሽን ዉስጥ የአደባባይ ሠልፍ አድርገዉ ነበር።የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ ሰማያዊ ፓርቲም ተቃዉሞዉን ለመራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በላከዉ ደብዳቤ ገልጧል።

የቡድን ሰባት ጉባኤ ከፖለቲካ፤ ምጣኔ ሐብቱ፤ ዉይይት፤ ክርክር፤ ከተቃሞ ሠልፍ ደብዳቤዉ፤ ከፖሊስ፤ ሠልፈኛዉ ግጭት ጋር የፕሬዝደንት ኦባማን ጀርመንኛ አሰምቶ-ጭፍጋጋዉን ድባብ አፍግጎታል።«የፈጣሪ ሠላምታ ይድረሳችሁ።የቆዳ ሱሪዬን እረስቼ መምጣቴን ማመን አለብኝ።»

ቡድን ሰባት ከተመሠረተ ሰላሳ ዓመት አለፈዉ።በዚሕ ሰላሳ ዓመት ዉስጥ ቻይና ከተራ-አዳጊ ሐገርነት ወደ ዓለም ሁለተኛ ሐብታምነት ተመንድጋለች።ደቡብ ኮሪያ፤ ሕንድና ብራዚል ድሕነትን አራግፈዉ ጥለዋል።ወይም እያራገፉ ነዉ።ሶቬት ሕብረትና ይጎዝላቪያ ተፈረካክሰዋል።ጀርመን ተዋሕዳለች፤ ሆንግ ኮንግ ከቻይና ተቀይጣለች።ኤርትራ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ምሥራቃዊ ቲሞር ነፃነት አዉጀዋል።ዓለምን ባሻዉ የሚያሽከረክዉ ያ ቡድን ግን ከስድስት ወደ ሰባት፤ከሰባት ወደ ስምንት እድጎ እንደገና ሰባት ላይ ይረግጣል።ሰላሳ ዓመት።

ለነገሩ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ መንግሥታት ቁጥርም ከ1945 ጀምሮ አምስት ላይ እንደቆመ አይደል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic