1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን ሰባት ሀገራት በአፍሪካ መዋዕለ-ንዋይ እና መሠረተ-ልማት ለማስፋፋት ቃል ገቡ

Eshete Bekele
ሰኞ፣ ሰኔ 10 2016

በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የቡድን ሰባት ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰባት ሀገራት ተግባራዊ የሚደረግ “ኢነርጂ ለአፍሪካ ዕድገት” የተሰኘ መርሐ-ግብር እንደሚጀምሩ ገልጸዋል። “በጠንካራ የአፍሪካ ሀገራት ባለቤትነት” ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ዕቅድ “ዘላቂ፣ የማይበገር እና አካታች ዕድገት እና የኤኮኖሚ ልማት” ለመፍጠር ውጥን አለው።

https://p.dw.com/p/4h9WC
ጣልያን የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ
የጀርመን፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ አሜሪካ፣ ጃፓን እና ዩናትድ ኪንግደም መሪዎች የተሳተፉበት የቡድን ሰባት ጉባኤ ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል አፍሪካን የተመለከቱ ይገኙበታል። ምስል Alex Brandon/AP Photo/picture alliance

የቡድን ሰባት ሀገራት በአፍሪካ መዋዕለ-ንዋይ እና መሠረተ-ልማት ለማስፋፋት ቃል ገቡ

በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የቡድን ሰባት ሀገራት ኢነርጂ ለአፍሪካ ዕድገት የተሰኘ መርሐ-ግብር እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰባት ሀገራት ተግባራዊ የሚደረገው መርሐ-ግብር የንጹህ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት በመላ አፍሪካ ለማስፋፋት የታቀደ ነው። “በጠንካራ የአፍሪካ ሀገራት ባለቤትነት” ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ዕቅድ “ዘላቂ፣ የማይበገር እና አካታች ዕድገት እና የኤኮኖሚ ልማት” ለመፍጠር ውጥን አለው።

ኢትዮጵያ፣ ኮትዲቯር፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ደቡብ አፍሪካ ዕቅዱ ተግባራዊ የሚደረግባቸው የአፍሪካ ሀገራት እንደሆኑ የቡድን ሰባት ሀገራት ባለፈው ቅዳሜ ያወጡት የአቋም መግለጫ ይጠቁማል።

የቡድን ሰባት አባል ሀገራት “በማደግ ላይ በሚገኙ” ባሏቸው ሀገራት በተለይም በአፍሪካ “በዋጋ ተመጣጣኝ፣ አስተማማኝ፣ ዘላቂ፣ ንጹህ እና ዘመናዊ ኢነርጂ” መኖሩን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለጹት በጣልያኗ ፔጉሊያ ለሦስት ቀናት ያካሔዱትን ዓመታዊ የመሪዎች ጉባኤ ሲያጠናቅቁ ነው።

የመሪዎቹ መግለጫ በተለይ በአፍሪካ ጉዳይ በበርካታ አማላይ ዕቅዶች የተሞላ ነው። ይሁን እንጂ ኢነርጂ ለአፍሪካ ዕድገት የተሰኘው መርሐ-ግብር ዝርዝር አፈጻጸም ምን እንደሚመስል የሚታወቅ ነገር የለም። ዕቅዱን ለማስፈጸም የተመደበ ገንዘብ መኖሩም አልተገለጸም።

በጉባኤው ሁለተኛ ቀን በአፍሪካ መዋዕለ-ንዋይ እና በመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በተደረገ ውይይት የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሀገራት ከዚህ ቀደም ሲከተሉት የነበረውን መንገድ ሊቀይሩ እንደሚችሉ ጥቆማ ሰጥተዋል።

ሜሎኒ “ለረዥም ጊዜ አፍሪካ ዓለም በተሳሳተ መንገድ የተረዳት፣ የተበዘበዘች እና የተናቀች አኅጉር ናት። ነገር ግን አፍሪካ ልዩ የሚያደርጋትን ዕምቅ አቅም የምትጠቀምበት ሁኔታ ከተፈጠረ ልታስገርም የምትችል ነች” ሲሉ ተደምጠዋል።

“አብሮ ለማደግ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በአቻ ግንኙነት መተባበር እና አዳዲስ የልማት ዕድሎችን መገንባት የእኛ ኃላፊነት ነው” ያሉት ሜሎኒ “እንዲህ አድርጉ አታድርጉ በሚል ትዕዛዝ እና በሰነዶች ሳይሆን በሐቅ አማካኝነት ልንሰራው እንፈልጋለን” ብለዋል።

የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ “ሁላችንም አፍሪካ ችሮታ እንደማትፈልግ ተረድተናል። አፍሪካ የምትጠይቀው ዕኩል የምትወዳደርበት ዕድል ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Andrew Medichini/AP Photo/picture alliance

ውይይቱ ዓለም አቀፍ የመሠረተ-ልማት እና ኢንቨስትመንት አጋርነት (PGII) ላይ ያተኮረ ነበር። ይኸ አጋርነት የቡድን ሰባት ሀገራት መቀነት እና መንገድ የተሰኘውን የቻይና ዕቅድ የሚገዳደር እንዲሆን ፍላጎት አላቸው።

“ለመሠረተ ልማት መዋዕለ-ንዋይ አማራጭ እንዲሆን እንፈልጋለን” ያሉት የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን “ዓለም አቀፍ የመሠረተ-ልማት እና ኢንቨስትመንት አጋርነት አስደናቂ የሚያደርገው ያለው የገንዘብ አቅም ብቻ አይደለም። ዘላቂ በመሆኑ ለዓለማችን ጠቃሚ ነው። ለሀገራቱም ጥሩ ነው። ይኸ ጥምረት እኛ የምናቀርበውን አማራጭ ከሌሎች የተለየ ያደርገዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የመሠረተ-ልማት እና ኢንቨስትመንት አጋርነት (PGII) በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 2022 ይፋ የተደረገ የቡድን ሰባት ሀገራት ዕቅድ ነው። እስከ ጎርጎሮሳዊው 2027 በዚህ ዕቅድ የቡድን ሰባት ሀገራት 600 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የማድረግ ዕቅድ አላቸው። የአጋርነቱ አቀንቃኝ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሀገራቸው አሜሪካ እስካሁን 60 ቢሊዮን ዶላር ከመንግሥት እና ከግሉ ዘርፍ ለዕቅዱ ማሰባሰቧን ተናግረዋል።

ባይደን “የምንገነባው መሠረተ ልማት እና በየዓለም አቀፍ የመሠረተ-ልማት እና ኢንቨስትመንት አጋርነት በኩል ሥራ ላይ የምናውለው መዋዕለ-ንዋይ አካሔዳችን በጠንካራ መንገድ ላይ እንዲጓዝ ይረዳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

በዕቅዱ ከተካተቱ መሠረተ ልማቶች አንዱ የሎቢቶ ኮረደር ነው። በዚህ ዕቅድ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከዛምቢያ ማዕድናት ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ለማጓጓዝ የሚያስችል የባቡር መስመር ይገነባል። ዕቅዱ አውሮፓ እና አሜሪካ ለኢንዱስትሪዎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ወሳኝ ማዕድናት ለማግኘት በአፍሪካ ከርሠ ምድር አይናቸውን እንደጣሉ የሚያሳብቅ ነው።

በዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ግምት ከ2020 እስከ 2040 ባሉት ዓመታት የዓለም የኒኬል እና የኮባልት ፍላጎት በ20 እጥፍ ይጨምራል። የአውሮፓ ኅብረት በሎቢቶ ኮሪደር ሥር ተግባራዊ የሚደረግ የወሳኝ ማዕድናት የአቅርቦት ሰንሰለት ዝግጅት የመግባቢያ ሥምምነት ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከዛምቢያ ጋር ተፈራርሟል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ 1300 ኪሎ ሜትር ለሚረዝመው የባቡር ማጓጓዣ 500 ሚሊዮን ዶላር ለመመደብ ቃል ገብቷል። ባለፈው ሣምንት በተካሔደው የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ ጣልያን ተጨማሪ 320 ሚሊዮን ዶላር እንደምትመድብ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ይፋ አድርገዋል።

በአፍሪካ መሠረተ-ልማት ለማስፋፋት የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች ሲመክሩ ግን ከአኅጉሪቱ የተገኙት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪንዉሚ አዲሺና ብቻ ናቸው። የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት፣ የአሜሪካው ማይክሮ ሶፍት እና የጣልያኑ ኤኒን የመሳሰሉ የግል ኩባንያዎች ውይይቱን ታድመዋል።

“ሁላችንም አፍሪካ ችሮታ እንደማትፈልግ ተረድተናል። አፍሪካ የምትጠይቀው ዕኩል የምትወዳደርበት ዕድል ነው። መሠረተ-ልማት ከሌለ ይኸን ማድረግ አይቻልም” ያሉት የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ “መንግሥታት ብቻቸውን ሊሰሩት አይችሉም። የግሉ ዘርፍ ብቻውን ሊሰራው አይችልም። ዓለም አቀፍ የልማት ባንኮች ብቻቸውን ሊሰሩት አይችሉም። ነገር ግን ሁላችንም በጋራ ልናሳካው እንችላለን” ብለዋል።

ወግ አጥባቂዋ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጎልተው የታዩበት የቡድን ሰባት ስብሰባ የሩሲያ ጦርነት በዩክሬን እና ላለፉት ስምንት ገደማ ወራት በጋዛ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚደረገው ውጊያ ትልቅ ትኩረት ያገኘበት ነበር።

የ47 ዓመቷ ሜሎኒ በኢንዱስትሪ የበለጸጉትን የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች በእንግድነት የተቀበሉት ፓርቲያቸው በአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ ባሸነፈ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው። ጉባኤው በድምሩ 40 ትሪሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ያላቸው ሰባት ሀገራት መሪዎችን ያገናኘ ነው።

አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ካናዳ፣ ጃፓን እና ብሪታኒያ የቡድን ሰባት እየተባለ የሚጠራው አባላት ናቸው። ሀገራቱ ከዓለም ሕዝብ የ10 በመቶ፤ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን በአንጻሩ 40 በመቶ ድርሻ አላቸው። የአውሮፓ ምክር ቤት እና የአውሮፓ ኮሚሽን ኃላፊዎችም ታድመዋል።

በዋናው የመሪዎች ጉባኤ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ፣ የዮርዳኖስ ንጉሥ አብደላ ሁለተኛ፣ የዩክሬን፣ ሕንድ፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ቱርክ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ የኬንያ፣ የአልጄሪያ፣ የቱኒዝያ እና የሞሪታኒያ መሪዎች ተጋብዘዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

የቡድን ሰባት ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ታዳሚዎች በጣልያን
የቡድን ሰባት ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ከአፍሪካ የኬንያ እና የሞሪታኒያ መሪዎችን እንዲሁም የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን በዚህ ዓመት ጋብዟል። ምስል Ciro Fusco/ZUMA Press/IMAGO

ለጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ አንገብጋቢ የሆነው የስደት ጉዳይ በጉባኤው ሁለተኛ ቀን ቀዳሚ አጀንዳ ነበር። ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን መቆጣጠር የሚችሉባቸው መንገዶች እና የስደተኞች መነሻ በሆኑ ሀገሮች ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ትኩረት ተደርጎባቸዋል።

ጉዳዩ ስደተኞች ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ከሚሻገሩባቸው ሀገራት አንዷ ለሆነችው ጣልያን ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው። በስደት ጉዳይ ጠንከር ያለ አቋም የሚያራምዱት ቀኝ አክራሪዋ ሜሎኒ ወደ አውሮፓ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቀነስ ለአፍሪካ ሀገራት ኢንቨስትመንት እና የገንዘብ ድጋፍ ማሳደግ ይፈልጋሉ።

የስደት ጉዳይ ለወግ አጥባቂዋ ሜሎኒ ብቻ ሳሆን ለአብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገራት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ለቀኝ አክራሪዎች ማንሰራራት በዋንኛነት ከሚጠቀሱ ገፊ ምክንያቶች አንዱ ይኸው የስደት ጉዳይ ነው።

ምርጫ የሚጠብቃቸው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሺ ሱናክ “ዩናይትድ ኪንግደም ለአፍሪካ የመደበችውን አዲስ የልማት እርዳታ እና የጣልያን አዲሱ የአፑሊያ የምግብ ሥርዓት መርሐ ግብር ጨምሮ ቡድን ሰባት መፍትሔ የሚሰጥባቸው መንዶች ላይ ትኩረት ሰጥቷል” ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሺ ሱናክ የጠቀሱት የአፑሊያ የምግብ ሥርዓት ማሻሻያ የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በተካሔደበት የጣልያን ግዛት የተሰየመ ነው።

መርሐ ግብሩን ከጥቂት ወራት በፊት ይፋ ያደረጉት የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ አውሮፓ የሚደረገውን ፍልሰት ለመግታት ለአፍሪካ ዕገዛ ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም አላቸው። ይኸ ዕቅድ ቡድን ሰባት ስደት ለመግታት በ15 ዓመታት ይፋ ያደረገው አራተኛ የምግብ ዋስትና ማሻሻያ ነው። ነገር ግን በቂ ገንዘብ ካልተመደበለት እንደ ቀደሙት ሁሉ ሊከሽፍ እንደሚችል በርካታ ባለሙያዎች ሥጋት አላቸው።

ምዕራባውያኑ ሀገራት ግን የዕዳ መለዋወጥ አሠራሮችን ገቢራዊ በማድረግ ደሐ ሀገሮች ለምግብ የሚመድቡትን በጀት ለማጠናከር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይኸ አሠራር በማደግ ላይ የሚገኙ የሚባሉት ደሐ አገሮች ቁልፍ ሥነ-ምኅዳሮች የመጠበቅ ሥራ ሲያከናውኑ ዕዳቸው እንዲቀነስላቸው መንገድ ይከፍታል።

መሪዎቹ በጉባኤው መጨረሻ ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫ “ሕገ-ወጥ የስደተኞችን ዝውውርን ለመከላከል እና ለመግታት” ያለመ የቡድን ሰባት ሀገራት መርሐ-ግብር መጀመራቸውን አስታውቀዋል። በጋራ የአቋም መግለጫው መሠረት ሰባቱ ሀገራት “መደበኛ ያልሆነ ስደት ዋና ዋና መንስኤዎች፣ የድንበር ቁጥጥር ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶች፣ ድንበር ተሻጋሪ የተደራጁ ወንጀሎች እና ደሕንነታቸው የተጠበቀ መደበኛ የስደት መንገዶች” ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ