የቡድን-ሃያ የፊናንስ ጉባዔና አፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 30.06.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የቡድን-ሃያ የፊናንስ ጉባዔና አፍሪቃ

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትና በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ላይ የሚገኙት የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች ባለፈው ሰንበት ካናዳ-ቶሮንቶ ላይ ተሰብስበው ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት ለመጠገንና ቀውስ ላይ ወድቆ የቆየውን ኤኮኖሚ ለማረጋጋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ተነጋግረዋል።

default

የበለጸጉት መንግሥታት በተለይም የበጀት ኪሣራቸውን ለመቀነስ ሲስማሙ የፊናንስ ገበያው ለውጥ ግን ለፊታችን ሕዳር የሶውል ጉባዔ እንዲሽጋሸግ ነው የተደረገው። የበጀት ኪሣራን ለመቀነስ የተደረገው ስምምነት ታዲያ በሌላ በኩል የልማት ዕርዳታን እንዳይጫን ማሳሰቡ አልቀረም። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ባን-ኪ-ሙን የበለጸጉት ሃገራት የቁጠባ ዕቅዳቸውን በድሆች አገሮች ትከሻ ላይ እንዳያካሂዱ ነው ያስጠነቀቁት። የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች በታቀደው ጊዜ ዕውን የመሆን ተሥፋም አጠያያቂ እንደሆነ ይቀጥላል።

ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ካናዳ-ቶሮንቶ ላይ የተካሄደው የቡድን-ስምንትና የቡድን-ሃያ ድርብ ጉባዔ በበለጸጉት መንግሥታት የዕዳ ቅነሣ ስምምነት ተፈጽሟል። ከዚህ ስምምነት መደረሱ ከቀውሱ መላቀቅ የሚቻልበትን ዘዴ በተመለከተ በዋዜማው በተለይም በጀርመንና በአሜሪካ መካከል ተነስቶ ከነበረው የሃሣብ ልዩነት አንጻር በሰፊው ያልተጠበቀ ነው። ምርጫው አዲስ ዕዳ ወይስ አዲስ የቁጠባ ፖሊሲ የሚል ነበር።
ከጉባዔው የተገኘው ውጤት ዕዳን በመቀነስ ላይ የተመሰረተ ዕድገት የሚል ሲሆን ይህም የጀርመኗን ቻንስለር የወሮ/አንጌላ ሜርክልን አቋም የሚያጠናክር ነው። እርግጥ ቀደምቱ ባለ ኢንዱስትሪ መንግሥታት የበጀት ኪሣራቸውን እስከ 2013 ዓ.ም. በግማሽ ለመቀነስ ያደረጉት ስምምነት ሕጋዊ አሳሪነት የለውም። ገቢር መሆኑ የእያንዳንዱ መንግሥት ፈንታ ነው። ቢሆንም የጀርመኗ ቻንስለር ሂደቱን ከተጠበቀው ዕርምጃ በላይ ሆኖ አግኝተውታል።

“እስከ 2013 ኪሣራውን በግማሽ ለመቀነስ የተያዘው ዕቅድ ግልጽ የሆነ መውጫ ስልት ነው። ዕዳችንን ካበራከተው የኤኮኖሚ ድጎማ እንላቀቃለን። በዚህ መንገድ የኢንዱስትሪው ዓለም ዕዳ መቀነሱ ትልቅ ነገር ይመስለኛል። ሃቁን ለመናገር ውጤቱ ከጠበቅኩት በላይ ነው። በተለይ ደግሞ የመላውን የበለጸጉ መንግሥታት ድጋፍ ማግኘቱን ትልቅ ስኬት አድርጌ ነው የምመለከተው”

G20 Gipfel Toronto Harper Merkel Flash-Galerie

ሜርክል በሌላ በኩል በዓለምአቀፍ ደረጃ የፊናንስ ንግድ ግብር ለማስፈን ያደረጉት ግፊት አልሰመረላቸውም። ይህ በተለይም ባንኮቻቸውን ከቀውስ ለማዳን በሚሊያርድ የሚቆጠር የግብር ገንዘብ ማፍሰስ ባልነበረባቸው እንደ ካናዳ ያሉ ሃገራት ዘንድ ጥብቅ ተቃውሞን ነው ያስከተለው። ብራዚልን የመሰሉት ተራማጅ ሃገራትም አልተቀበሉትም።

“በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራት ቀውሱን የፈጠርነው እኛ አይደለንም ባይ ናቸው። እናም ቀውሱ ያስከተለውን ዕዳ መልሶ ማስወገዱን ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው አይመለከቱም። በበኩሌ እንደ ቡድን-ሃያ የጋራም የተለያየም ሃላፊነት እንዳለብን ተረድተን ደረጃ በደረጃ አብረን ማደግ እንዳለብን ነው የማምነው። ተራማጁ መንግሥታት ጉዳዩን የሚመለከቱትም እንዲህ ነው። በአጠቃላይ የፊናንስ ገበዮችን ስርዓት ለማስተካከል በተያዘው ጥረት እስከሁን ብዙ ዕርምጃ ተደረጓል። ግን የሚቀር ነገር አለ። ይህም ነው በሚቀጥለው የሶውል ጉባዔ ላይ ዋናው ነገር የሚሆነው”

በካናዳው ጉባዔም የበለጸጉት መንግሥታት ከአምሥት ዓመታት በፊት የልማት ዕርዳታቸውን አሁን በያዝነው 2010 ዓ.ም. በ 50 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ለማድረግ በግሌንኢግልስ ገብተውት የነበረው ቃል እንደገና ገቢር ባለመሆኑ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው። ጉዳዩ ሌላው ቀርቶ እንዳለፉት ዓመታት በጉባዔው ማጠቃለያ ሰነድ ላይ እንኳ አልሰፈረም። በመሆኑም ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች የበለጸጉት መንግሥታት በታዳጊ አገሮች የእናቶችንና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ 8 ሚሊያርድ ዶላር ለማቅረብ የገቡትን አዲስ ቃል አምኖ መቀበሉ አቅቷቸዋል። ጉባዔው ከቃል አልፎ የረባ ነገር አላስከተለም ከሚሉት ተቺዎች መካከል አታክ በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባልደረባ ሁጎ ብራውንም ይገኙበታል።

“ለነገሩ ጉባዔው እንደየትኛውም ጉባዔ ሁሉ ብዙ የተባለበት ከመሆን አልፎ የወጣው ጭብጥ ነገር የለም። የፊናንስ ሽግግር ግብር ለማስፈን አልተቻለም። ለሕጻናትና ለእናቶች የተመደበው ገንዘብ በአሳፋሪ ሁኔታ ዝቅተኛ ነው። በ 2005 ስኮትላንድ-ግሌንኢግልስ ላይ ለአፍሪቃ ተገብቶ የነበረው ቃል ገቢር እንዲሆን ምንም ነገር አልተደረገም። ገና ሃያ ሚሊያርድ ዶላር እንደጎደለ ነው። እናም ጉባዔው በጥቅሉ የከሰረ ነበር ነው የምለው”

የፊናንስ ሽግግር ግብር በማስፈን ለልማት ዕርዳታ ገንዘብ እንዲከማች አለመደረጉም የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ባልደረባ ዮርን ካሊንስኪ እንደሚሉት በጣሙን አስቆጪ ነው።

“ካናዳ ውስጥ የቡድን-ስምንትና የቡድን-ሃያ ጉባዔ ተቀራርቦ ተካሂዷል። ይህ ደግሞ የልማትና የፊናንስ ጥያቄዎችን አጣምሮ ጎን ለጎን ለመወያየት ከዚህ ቀደም አዘውትሮ ያልተለመደ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። እናም ከዚህ አንጻር ለቀውሱ በአብዛኛው ተጠያቂ የሆኑት ወገኖች ጉዳቱን እንዲያስወግዱ መጠየቅም በተቻለ። ወሣኙ ነገር በተባለው ግብር ብዙ ገንዘብ ቢሰበሰብ የበለጸጉት መንግሥታት ለምሳሌ የገቡትን የልማት ዕርዳታ ቃል ሊየከብሩና መልሰው ብቁ ሊሆኑም በጫሉ ነበር”

ግን ይህ አልሆነም፤ የልማት ዕርዳታው በተገባው ቃል መሠረት ሊቀርብ ሳይችል መቀጠሉ የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ግቦች በቀሩት አምሥት ዓመታት ውስጥ በከፊል እንኳ ዕውን የመሆን ተሥፋ የመነመነ የሚያደርግ ነው። አፍሪቃ ለነገሩ ያልፈጠረችው ቀውስ ሰላባ ስትሆን የዕድገቷ ማገገምና ቀጣይነትም በዓለምአቀፉ የፊናንስ ስርዓት መረጋጋት ላይ ጥገኛ ነው። ይህም በመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዘመቻ የአፍሪቃ ሃላፊ ቻርልስ አቡግሬ ጉባዔው በጥሩ ውጤት ቢፈጸም እንደሚጠቅም ነበር ባለፈው ሣምንት ናይሮቢ ላይ የገለጹት።

“ተሥፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም አፍሪቃ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ስርዓት ላይ በደረሰው ቀውስ ተጎድታለች። ከዚያ ቀደም ሲል በ 5 እና በ 5,3 ከመቶ እያደገች ነበር። የፊናንሱ ቀውስ ቀጥተኛ ውጤት ደግሞ ዕድገቱ ባለፈው ዓመት ወደ 2,5 በመቶ እንዲያቆለቁል ነው ያደረገው። አፍሪቃ በጥሬ ዕቃ ላይ ጥገኛ ናት። እናም ዓለምአቀፉን ፍላጎት የሚነካ ስርዓት አፍሪቃንም ይነካል..”
ቻርልስ አቡግሬ እንደሚያምኑት የበለጸጉት መንግሥታት የፊናንስ ስርዓታቸውንና ዓለምአቀፉን የምንዛሪ ልውውጥ ካረጋጉ ግን አፍሪቃ ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች። መረሳት የሌለበት ነገር አብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች የገንዘብ ክምችታቸውን የሚያስቀምጡት በውጭ ነው። በተለይም በዶላር! እናም የምንዛሪው ውጣ ውረድ ብርቱ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አንድና ሁለት የለውም። በሌላ በኩል ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በአፍሪቃ ላይ ተጽዕኖ ያደረገውን ያህል ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ለክፍለ-ዓለሚቱ ችግሮች ቢቀር የሚገባውን ያህል ትኩረት ሰጥቷል ለማለት አይቻልም።

“በቂ አይደለም። የዓለምአቀፉን ምንዛሪ ተቋም ገንዘብ በመጨመር ጥቂት ነው የተደረገው። የምንዛሪው ተቋም ለአፍሪቃ የሚያበድረው አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህል አለው። ግን ይህ በፊናንሱ ቀውስ አፍሪቃ ካጣችው ሲነጻጸር የጥቂት ጠብታን ያህል ነው። ብዙ የአፍሪቃ አገሮች ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ አስፈላጊውን ማካካሻ ይሰጣል ብለው ተሥፋ አድርገው ነበር። ግን ይህ አልሆነም”

ቻርልስ አቡግሬ አያይዘው እንደሚያስረዱት በሁለተኛ ደረጃም የበለጸጉት መንግሥታት ዕርዳታቸውን ቀንሰዋል። በዚሁ የተነሣም የአፍሪቃ አገሮች የሚያገኙት ዓለምአቀፍ ዕርዳታ ከቀድሞው ያነሰ ነው። የውጩ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትም እንዲሁ! ለዚህ ደግሞ በቂ ማካካሻ አይሰጥም። የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ማቆልቆሉ እንግዲህ ለዚህ ነው። ቀውሱን ከፈጠሩት አንጻር ሲታይ ሁኔታው ጨርሶ ፍትሃዊ አይደለም። ታዲያ ከዚህ አንጻር ከሚሌኒየሙ ግቦች በጊዜው መድረሱ ቢቻል እንኳ ከባድ ጥረትን የሚጠይቅ ነው የሚሆነው። የዘመቻው ሃላፊ አቡግሬ እንደሚሉት የአፍሪቃ አገሮች የራሳቸውን የውስጥ ጥረትም ማጠናከር አለባቸው።

“በብዙ ደረጃዎች ወደፊት መግፋት አለብን። በአፍሪቃ አገሮች ደረጃ የውስጥ አቅምን ለማሰባሰብ የበለጠ መደረግ ይኖርበታል። የግቡ ስርዓት ፍቱን ሊሆን ይገባዋል። ሃብታሞቹ ግብር መክፈል ሲኖርባቸው መንግሥት ይህንኑ በአግባብ ስራ ላይ ማዋሉም ግድ ነው። ሲቪሉ ሕብረተሰብም ሙስናን ለመታገልና ገንዘቡ በሚሌኒየሙ ግቦች ላይ ይውል ዘንድ እንዲሰራ መነሳት ይኖርበታል ...”

ይህ እንግዲህ ከአፍሪቃ በኩል የሚጠበቀው ነው። የበለጸጉት መንግሥታትም በፊናቸው የገቡትን ቃል ገቢር ማድረግ አለባቸው። ጀርመንን ጨምሮ የአውሮፓ መንግሥታት እስከያዝነው 2010 ዓ.ም. ዕርዳታቸውን ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው አንጻር እስከ 0,56 በመቶ ከፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ይታወቃል። ግን ቃል እስካሁን ገቢር አልሆነም።

መስፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ