የቡድን-ሃያ የዓለም የፊናንስ ጉባዔ | ኤኮኖሚ | DW | 23.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የቡድን-ሃያ የዓለም የፊናንስ ጉባዔ

ሶሥተኛው የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች የፊናንስ ጉባዔ ነገና ከነገ በስቲያ አርብ በአሜሪካ ፌደራል ክፍለ-ሐገር ፔንሲልቫኒያ-ፒትስበርግ ላይ ይካሄዳል።

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን

የመንግሥታቱ መሪዎች የፊናንሱን ቀውስ በመታገሉ ረገድ ካለፉት ሕዳርና ሚያዚያ ወራት የዋሺንግተንና የለንደን ጉባዔዎቻቸው ወዲህ ከምን ውጤት እንደደረሱ ይገመግማሉ። በዚህ ጉባዔ ላይ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት ከቀውስ የሚያላቅቁ ጭብጥ ዕርምጃዎችን ለማስፈንም ነው የሚታሰበው። ለመሆኑ እስካሁን ምን የታየ ዕርምጃ አለ? ከጉባዔው ጭብጥና ገቢር ለመሆን የሚበቃ ውጤት ለመጠበቅስ ይቻላል ወይ?

በአሜሪካ የቤት ባለቤቶች የባንክ ብድርን መልሶ ለመክፈል አለመቻል ከአንድ ዓመት በፊት የቀሰቀሰው የባንኮች ክስረት ያስከተለውን ዓለምአቀፍ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም በተለይ በምዕራቡ ዓለም በብዙ ሚሊያርድ ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ፈሷል። ዛሬም መፍሰሱን እንደቀጠለ ነው። ይሁንና ቀውስ ያዛባውን ኤኮኖሚ መልሶ ለማነቃቃት በተደረገው ጥረት ጥቂት የማገገም አዝማሚያ ይታይ እንጂ አደጋው አሁንም በአስተማማኝ ሁኔታ አልተወገደም። የሥራ አጡ ቁጥር ከቀን ወደቀን በመጨመር ላይ ሲሆን የመንግሥታቱም የበጀት ኪሣራ እንደዚሁ እያደገ ነው። ባልፈጠሩት ጣጣ መዘዙ በተረፋቸው በታዳጊ አገሮች እንዲያውም የኤኮኖሚው ቀውስ ዕድገትን ከመግታት ባሻገር ማሕበራዊ ቀውስ እየሆነና ድህነትን ይበልጥ እያባባሰ መሄዱን ቀጥሏል። በጥቅሉ አዲስ ወርቃማ ዘመን ለዓይን የቀረበ ሆኖ አይታይም።

የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች በቀውሱ ማግሥት ባለፈው ዓመት ሕዳር ወር ዋሺንግተን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰበሰቡ ከሁሉም በላይ አስቀድመው ያተኮሩት በፊናንስ ገበዮች ላይ በጊዜው የተፈጠረውን ነውጽና ውዥምብር በማስወገዱ ጉዳይ ነበር። ለዚሁም አርባ ነጥቦች ያዘለ የተግባር መርህ አስፍነው ይለያያሉ። አምሥት ወራት ዘግየት ብሎ ደግሞ በሚያዚያ ወር መግቢያ ላይ ሁለተኛው የመሪዎች ጉባዔ ለንደ ላይ ይካሄዳል። ቀውሱ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ በየቦታው ስር የሰደደበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም ቡድን-ሃያ መንግሥታት የዓለምን ንግድ ለማነቃቃትና በቀውሱ ክፉኛ የተመቱትን የድሃ-ድሃ የተባሉ አገሮች ለመደገፍ 1100 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚጠጋ ግዙፍ ገንዘብ በሥራ ለማዋል ይወስናሉ። ጉባዔው ታሪካዊ መባሉም አልቀረም።

“የዛሬው ዕለት ዓለም ቀውሱን ድል ለመምታት አንድ ሆኖ የተነሣበት ነው። ይህም እንዲሁ በቃላት አይደለም። በዓለምአቀፍ ደረጃ ለማገገም፣ አስፈላጊውን ለውጥ ለማካሄድና ገቢር ለማድረግ የሚያበቃ ዕቅድ በመያዝ ነው”

በጊዜው ይህን ተሥፋ የተመላበት ቃለ የተናገሩት የለንደኑ ጉባዔ አስተናጋጅ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን ነበሩ። ግን የተባለውን ሁሉ ገቢር ማድረጉ የኋላ ኋላ አስቸጋሪ እንደሆነ ገሃድ መሆኑ አልቀረም። በሌላ በኩል የበለጸጉት መንግሥታት ባፈሰሱት በብዙ ሚሊያርድ ዶላር ከውድቀት የዳኑት ባንኮች መልሰው ትርፍ ማስገባት ይዘዋል። አስተዳዳሪዎቻቸው እንደገና ከመጠን በላይ የሆነ አበል እየተከፈላቸውም ነው። ለነገሩ የስዊድኑ የፊናንስ ሚኒስትር አንደርስ ቦርግ እንደሚሉት በተሳሳተ ግምትና የአጭር ጊዜ ስኬት የተነሣ ለአስተዳዳሪዎች የሚከፈለው አበል ከመጠን በላይ መጋነን የቀውስ ዋና መንስዔ እንደነበር ሊዘነጋ ባልተገባው ነበር።

“ይህን የቦነስ-እብደት፤ የአበል ክፍያ ማቆም ይኖርብናል። ባንኮቹ በ 1999፤ ከአሥር ዓመታት በፊት ያለን ይመስል አሁንም በፌስታ ላይ ናቸው። ግን ዛሬ 2009 ዓ.ም. ነው። እናም ይህ የባንኩ ዘርፍ ወግና ዘይቤ ቢዘገይ ፒትስበርግ ላይ ማብቃት አለበት”

በዚህ ጉዳይ አውሮፓውያን መንግሥታት በሰፊው የሚስማሙ ሲሆን ነገና ከነገ በስቲያ ፒትስበርግ ላይ በአንድ ድምጽ ለመናገርም ዝግጁዎች ናቸው።

“ይህ አሳፋሪ የቦነስ ወይም የተጨማሪ ገንዘብ ክፍያ፤ ይህ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት እንደገና ሊጀምር አይገባውም። እንደገና ማበብ የለበትም”

ይህን የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት መሪዎች ለፒትስበርጉ ጉባዔ የጋራ አቋም ለማስፈን ባለፈው ሣምንት አካሂደውት በነበረው ልዩ ስብሰባ ላይ የተናገሩት የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ኒኮላይ ሣርኮዚይ ናቸው። ይሁንና በፒትስበርጉ ጉባዔ የባንክ አስተዳዳሪዎችን ያላግባብ የመካበት ዘይቤ ለማቆም ይቻል አይቻል ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው። በጉዳዩ ጀርመንና ፈረንሣይ በአንድ በኩል አሜሪካና ብሪታኒያ ደግሞ በሌላ ወገን የተለያየ አቋም ሲያንጸባርቁ ነው የቆዩት። እንግዲህ በሰሞኑ ጉባዔ በዚሀ ነጥብ ከአንድነት መደረሱ ጥቂትም ቢሆን ማጠራጠሩ አይቀርም።

መለስ ብለን ካስታወስን በለንደኑ የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ ማንኛውም የፊናንስ ገበያና የፊናንስ እንቅስቃሴ ወደፊት ያለ ቁጥጥርና ያላንዳች ደምብ ሊቀጥል አይገባውም ነበር የተባለው። በመሠረቱ ይሄው የለንደን ውሣኔ ደግሞ ፒትስበርግ ላይ አሣሪ ባህርይ ያለው ሆኖ መቀጠል ይጠበቅበታል። ምክንያቱም በእያንዳንዱ መንግሥታት ገቢር ሊሆን የሚበቃው ይህ ሲሆን ብቻ ነው። በዚህ መልክ ዘላቂ የሆኑ የኤኮኖሚ ዕርምጃዎችን የሚያረጋግጡ መቆጣጠሪያ ደምቦች እንዲሰፍኑ በተለይ አጥብቀው ከሚሟገቱት አውሮፓውያን መሪዎች መካከል አንዷ የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ሆነው ቆይተዋል።

“እንድ ቀን እንደገና የሆነ ባንክ ድንገት ተነስቶ መንግሥት በሚቀጥሉት 12 ሰዓታት ውስጥ ይርዳኝ አለበለዚያ ጠቅላላውን የፊናንስ ስርዓት ይዤ መውደቄ ነው ቢለን ምን ዓይነት ዕርምጃ ነው ለመውሰድ የምንችለው? በዚህ ላይ፤ ለምሳሌ ከአንድ ዓመት በፊት እንደሆነው ሌህማን ብራዘርስን የመሰለ ባንክ ተንኮታኩቶ ቢወድቅ አንድ መንግሥት ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም። ስለዚህም ከአንድ ከዓለምአቀፍ ስምምነት መደረሱ ግድ ነው”

ጥያቄው እንዴት ከአንድነት መድረስ ይቻላል ነው። ከአንድነት ከተደረሰ ደግሞ ምን ዓይነት አንድነት በዓለምአቀፍ ደረጃ ዘላቂ ፈውስ ሊሆን ይችላል? በተለይ ከአዳጊውና ከታዳጊው ዓለም ጥቅም አንጻር ወሣኝነት ይኖረዋል። የወቅቱ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ከሰባ ዓመታት ወዲህ በዓለም ላይ አቻ ያልታየለት ነው። ጥቂት ሃያል መንግሥታት የዓለምን ኤኮኖሚ ለብቻቸው የሚዘውሩበት ጊዜም አልፏል። በነዚሁ ሰፍኖ የቆየውም ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ስርዓት እንዲሁ የለውጥ ያለህ ማለቱ አልቀረም። በዓለም ላይ የፖለቲካው ሃይል ሚዛን እየተለወጠ በመሄድ ላይ ለመሆኑ ብሪክ በሚል አሕጽሮት የሚጠሩት አራት ሃገራት የብራዚል፣ የሩሢያ፣ የሕንድና የቻይና ዕርምጃ ጉልህ መረጃ ነው።

እነዚህ በተፋጠነ ዕድገት በመገስገስ ላይ የሚገኙ መንግሥታት ዛሬ ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ውጤት 15 በመቶውን ድርሻ የያዙ ናቸው። ከዚሁ በተጨመሪ 13በመቶውን የዓለም ንግድ ድርሻ የሚይዙ ሲሆን 2,8 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ከአርባ በመቶ በላይ የዓለም የምንዛሪ ክምችት ባለቤቶችም ናቸው። የጀርመን ባንክ ቀደምት የኤኮኖሚ ባለሙያ ኖርበርት ቫልተር እንደሚሉት ከአነዚሁ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ አገሮች አንዳንዶቹ ወደፊትም የዓለምን የኤኮኖሚ ሚዛን ይበልጥ ለመለወጥ ብቃቱ ያላቸው ናቸው።

“በማያሻማ ሁኔታ፤ በሚቀጥሉት አምሥትና ሰባት ዓመታት ውስጥ ሂደቱ ከመዳከም ይልቅ የሚጠናከር ነው የሚሆነው። የነዚህ አገሮች ድምጽ በንግድና በመዋዕለ-ነዋይ ነክ ውሣኔዎች ላይ ታላቅ ዓለምአቀፍ ክብደት ይኖረዋል። አሜሪካውያንና አውሮፓውያን በፊናቸው መጪዎቹን አምሥት ዓመታት ዝቤትን በማስተካከል ሥራ ተጠምደም ነው የሚያሳልፉት። በመጀመሪያ መዋቅራዊ ይዞታቸውን መልሶ ጤናማ ማድረግና ዕዳቸውን መቀነስ አለባቸው። በአንጻሩ በተራማጆቹ አገሮች የሚታየው አንጻራዊ ዕድገት እየጠነከረ መሄዱ እርግጠኛ ነው”

ለዚህም ነው ብሪክ በሚል አሕጽሮት የሚታወቁት አገሮችና መሰሎቻቸው ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ ለመፍታት በተያዘው ጥረት ከበለጸጉት መንግሥት ጋር በአንድ ጠረጴዛ እንዲቀመጡ መደረጋቸው። ቢዘገይ ካለፈው ሕዳር ወር የዋሺንግተን የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ወዲህ የበለጸጉት መንግሥታት ክበብ የነበረው ቡድን-ስምንት እነዚህን አገሮች በማቀፍ ወደ ቡድን-ሃያ መስፋቱ ችግሩን በቀድሞው ዘይቤ ለመፍታት ላለመቻሉ ግንዛቤ ሥር መስደዱን ነው የሚያመለክተው።

በሌላ በኩል የጊዜውን መለወጥ ተከትሎ የአዳጊዎቹን አገሮች የንግድ ድርሻና የውሣኔ ተሳትፎ ድምጽ የሚያጎላ አዲስ የዓለም ኤኮኖሚ ስርዓት በማስፈኑ ረገድ ብዙም ቁርጠኝነት አይታይም። ይህ በተለይ በድሆቹ ታዳጊ አገሮች ልማት ላይ ብርቱ ተጽዕኖ እንዳለው ይቀጥላል። እንደ ዕውነቱ ለነዚህ አገሮች ዕድገት፤ እንዲያም ሲል ከድህነት መላቀቅ ከተለመደው የዕዳ ምሕረት፣ ልገሣም ሆነ ምጽወታ ይልቅ በአዲስ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ስርዓት የገበያ ድርሻቸውን ማዳበር፤ በአጠቃላይ በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ረገድ መዋቅራዊ ዕርምጃ እንዲያደርጉ ጥርጊያ ቢከፈት ምንኛ በበጀ ነበር።
በነገራችን ላይ የበለጸጉት መንግሥታት ባለፈው የለንደን ጉባዔ ታዳጊ አገሮች ዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም በሚያደርጉት ትግል ለማገዝ 49 ሚሊያርድ ዶላር ለማቅረብ የገቡትን ቃል እስካሁን ሙሉ በሙሉ ዕውን አላደረጉም። አክሺን-ኤይድ የተሰኘው ዓለምአቀፍ ድርጅት በዛሬው ዕለት ብራስልስ ላይ እንዳስታወቀው እስካሁን ግማሹ ገንዘብ ብቻ ነው ነጻ የተለቀቀው። ድርጅቱ አያይዞ እንደጠቀሰው በከፋ ድህነት ላይ ለሚገኙ አገሮች ዘጠኝ ሚሊያርድ ዶላር ብቻ ሲሰጥ በአንጻሩ ሃብታም አገሮች ለራሳቸው 1,1 ቢሊዮን ዶላር አፍሰዋል።

ለማጠቃለል ነገና ከነገ በስቲያ ፒትስበርግ ላይ የሚካሄደው የቡድን-ሃያ የመሪዎች ጉባዔ ለአዲስ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ስርዓት ጥርጊያ እስከሚያበጅ ግብ እንደማይዘልቅ ከወዲሁ ጎልቶ የሚታይ ነው። ሌላው ቀርቶ ባለፈው የቡድኑ የለንደን ጉባዔ የተባለውና የተገባው ቃል ሁሉ ራሱ ተግባራዊ ለመሆን መብቃቱን አሁን በዋዜማው የሚጠራጠሩት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። እርግጥ እንደተለመደው አንድ የስምምነት መግለጫ መውጣቱ አይቀርም። ግን ባለፉት ሁለት ጉባዔዎች ከተሰማው በላይ አዲስ ነገር መጠበቁ በጣሙን ያዳግታል። ምናልባት በዓለም ንግድና በዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበዮች አቀነባበር ላይ የተያዘው ውይይት ከፒትስበርጉ ጉባዔ በኋላም መቀጠሉ የማይቀር ነው የሚመስለው።

MM/DW/epd

SL