የቡድን-ሃያ መሪዎች የካን ጉባዔና ሚናው | ኤኮኖሚ | DW | 02.11.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የቡድን-ሃያ መሪዎች የካን ጉባዔና ሚናው

የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች በፈረንሣይ መዝናኛ ስፍራ በካን ነገና ከነገ በስቲያ ተሰብስበው በተለይም የኤውሮ ምንዛሪ ሃገራት የዕዳ ቀውስን ለመቋቋም በቅርቡ ባደረጉት ስምምነት ላይ ይነጋገራሉ።

default

በኢንዱስትሪ ልማት ለበለጸጉትና በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ ለሚገኙት ሃያ መንግሥታት ነገ የሚከፈተው የመሪዎች ጉባዔ የአሜሪካው የመዋዕለ-ነዋይ ባንክ ሌህማን ብራዘርስ ከከሰረ ወዲህ ስድሥተኛው መሆኑ ነው። ያኔ የተፈጠረው ቀውስ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት ተንኮታኩቶ ከመውደቅ ብርቱ አደጋ ላይ ነበር የጣለው። ስለዚህም የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ በፍጥነት ተጠርቶ ቀውሱን ለማስወገድና ስርዓቱንም ለመጠገን እስከዚያው ያልታየ ታላቅ ጥረት ይጀመራል።

ታዲያ ስብስቡ ሁኔታውን ለማለዘብ ጠቃሚ ዕርምጃዎችን መውሰዱና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ስኬት ማግኘቱ አልቀረም። ይሁን እንጂ ለውጡ የተፈለገውን ያህል ተራምዷል ለማለት አይቻልም። ለነገሩ የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች በሰሞኑ የካን ጉባዔያቸው ለመነጋገር ያቀዱት በአንድ አዲስ ዓለምአቀፍ የምንዛሪ ስርዓት በሚሰፍንበት ሁኔታና የጥሬ ዕቃን ዋጋ ያላግባብ በማስወደድ በሚደረገው ንግድ ላይ ነበር። ግን ይህ ተሻሚ ዓቢይ ችግር ተደቅኖበታል። ለቡድን-ሃያ በወቅቱ የኤውሮ-ዞን የዕዳ ቀውስ የተነሣ እንደገና የእሣት አደጋ መከላከል ሚና መያዙ ግድ ነው የሆነው። በሌላ አነጋገር የመንግሥታቱ መሪዎች ዓቢይ ትኩረት የሚያርፈው በኤውሮ ምንዛሪ ሃገራት ችግር ላይ ነው።

መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል በሌህማን ብራዘርስ ባንክ ክስረት የጀመረው የአሜሪካ የፊናንስ ቀውስ ለመላው ዓለም ከተረፈ ይሄው ሶሥት ዓመታት አለፉት። የፊናንስ ገበዮች ውዥቀት በውዥቀት ሲሆኑ የዓለም ኤኮኖሚም ከሰባ ዓመታት ወዲህ ያልታየ ብርቱ የቀውስ አደጋ ይደቀንበታል። የፊናንሱ ቀውስ ዓለምአቀፉ ንግድ እንዲቀንስና በዓለም ዙሪያ ብዙ ክስረት እንዲከተል ሲያደርግ ችግሩን ለመግታት በተቻለ ፍጥነት አንድ መላ መፈለጉ ግድ ነበር የሆነው። መፍትሄ በማፈላለጉ ረገድም ተሥፋው በቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች ላይ ይጣላል። እንግዲህ ቡድን-ሃያ እስከዚያው በፊናንስ ሚኒስትሮች ደረጃ ብቻ ሕያው ሆኖ ሲቆይ የመሪዎቹን ጉባዔ የወለደው የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ዋሺንግተን ላይ ከተካሄደው ከመጀመሪያው ጉባዔ በኋላ እንደገለጹት ዓለምን የወጠረው የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ነበር።

“ቀውሱ እንዳይደገም የማድረግ ታላቅ የጋራ ፍላጎት እንዳለ አምናለሁ። አስፈላጊው ነገር መላውን የገበያ ተሳታፊዎች፣ ምርቶችና ገበዮች መቆጣጠር ወይም መከታተል መቻል ነው። አንዳች ቀዳዳ መቅረት የለበትም። እና ይሀ እንደሚሳካልንም እርግጠኛ ነኝ። በገበዮች ላይ የሚከሰት ትርፍ የማጋበስ ችግር የምንፈልገውን ሁሉ የሚያጠፋ ሊሆን አይገባም”

የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች በዋሺንግተኑ የ 2008 ጉባዔ ፍጻሜ ሃምሣ ገደማ የሚጠጉ በፍጥነት ገቢር መሆን ያለባቸውን ዕርምጃዎች ባቀፈ የጋራ ውሣኔ ይስማማሉ። ከዚያም ከመንፈቅ በኋላ ደግሞ ሁለተኛው የመሪዎች ጉባዔ እ.ጎ.አ. በሚያዚያ ወር 2009 ዓ.ም. ለንደን ላይ ይካሄዳል። ይህም ጉባዔ “የዕድገትና የጥገና የተግባር ዕቅድ” የተሰኘ መርህ የተላለፈበት ነበር። ዕቅዱ በፊናንስ ገበዮች ተዋንያን ላይ ልጓምን ጠበቅ ማድረግንና የግብር ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚከማችባቸውን ቦታዎች ዝርዝር ማውጣትን ጭምር የሚጠቀልል ነበር። የጊዜው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን ዕቅዱን ያስታወቁት ታሪካዊ ግምት በመስጠት በታላቅ ስሜት ነበር።

“ይህ ዕለት ዓለምአቀፉን ቀውስ ለማሸነፍ ዓለም በአንድ ላይ የቆመበት ነው። ይህ ደግሞ እንዲሁ በቃላት አይደለም። ይልቁንም በዓለም ዙሪያ ዕድገትንና ለውጥን ለማስፈን በሚያስችል ዕቅድ ነው”

እንደገና መንፈቅ ያልፍና በመስከረም 2009 ደግሞ የቡድን-ሃያ የመሪዎች ጉባዔ በፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተናጋጅነት አንዴ የአሜሪካ የብረታ-ብረት ኢንዱስትሪ ማዕከል በነበረችው በፒትስበርግ ይካሄዳል። በዚህ ጉባዔ የፊናንሱን ገበዮች ሂደት በመቆጣጠሩ ጉዳይ ጥቂት የወደፊት ዕርምጃ መደረጉም አልቀረም። ከዚሁ በተጨማሪ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የአይ.ኤም.ኤፍ. በጀት ከፍ እንዲልና በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራትም በተቋሙ ውስጥ የበለጠ ክብደት እንዲኖራቸው ይደረጋል። ባራክ ኦባማ ቢዜው ዕርምጃውን ተሥፋ ሰጭ አድርገው ነበር የተመለከቱት።

“ከስድሥት ወራት በፊት የለንደኑን ጉባዔ የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስን ለማስወገድ በምናደርገው ጥረት የለውጥ አቅጣጫን ያመላከተ ነው ብዬ ነበር። እዚህ ፒትስበርግ ውስጥ ደግሞ የኤኮኖሚ ዕድገታችንን ለማጠናከር፤ አስተማማኝ፣ ሚዛን የጠበቀና ቀጣይነት ያለው ለማድረግ ብዙ ጠቃሚ ዕርምጃዎችን ለማድረግ ችለናል። በአጭሩ የዓለም ኤኮኖሚን ከለየለት ውድቀት አድነናል። እና የዛሬው ዕለት ለረጅም ጊዜያት ጽናት ለሚኖረው ብልጽግና መሠረት የጣልንበት ነው”

ባለፈው 2010 ዓ.ም.ም የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች ሁለት ጉባዔዎችን አካሂደዋል። አንዱ በሰኔ ወር ካናዳ-ቶሮንቶ ላይ ሌላው ደግሞ በሕዳር ወር ደቡብ ኮሪያ ርዕሰ-ከተማ ሶውል ውስጥ የተደረገው ነበር። ነገር ግን ከዚያን ወዲህ ዓለምን ከፊናንስና ከኤኮኖሚ ቀውስ ለማዳን የተነሣው ትግል እየቀዘቀዘ ነው የመጣው። እርግጥ የዓለም ኤኮኖሚ ከሞላ-ጎደል በሰፊው አገግሟል። ለምሳሌ በዚህ በበለጸገው ዓለም ጀርመንን ብንወስድ አገሪቱ ከባድ ከነበረ ቀውሷ በፍጥነት በመላቀቅ ዛሬ እንደገና ዕድገት እያደረገች ነው። ግን ቁጠባ ወይስ ተጨማሪ ገንዘብ ማፍሰስ፤ ትክክለኛውን የኤኮኖሚ ዘይቤ በተመለከተ ክርክር መነሣቱ አልቀረም። የጀርመን መንግሥት የቁጠባውን መንገድ ሲመርጥ ይህም በቶሮንቶው ጉባዔ ላይ ብዙ ተሰሚነትን ያገኘ ነበር።

“በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ሃገራት የበጀት ኪሣራን እስከ 2013 ዓ.ም. በግማሽ ለመቀነስ የተጣለው የጊዜ ክልል ስልታዊ ግብ ሆኖ ሊታይ የሚገባው ነው። ብዙ ዕዳ ውስጥ ከገባንበት የኤኮኖሚ ፕሮግራም በመሰናበት እንደ ኢንዱስትሪ መንግሥታት ዕዳውን መቀነስ ይኖርብናል። ይህ ደግሞ ዕውነቱን ልናገር ይሆናል ብዬ ከጠበቅሁት በላይ ነው። በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት መንግሥታት በጠቅላላ ተቀባይነት ማግኘቱ ትልቅ ስኬት ነው”

እርግጥ የፊናንስ ገበዮችን ቁጥጥር የሚመለከተው ለውጥ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወደፊት መራመዱ አልቀረም። ይሁን እንጂ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ጠንካራው የባንኮች ተጽዕኖ ጥብቅ ደምቦች እንዳይሰፍኑ መሰናክል ሆኖ ነው የሚገኘው። ከዚሁ ሌላ አንዱ ትልቅ ጥያቄ አንድ ባንክ በሚከስርበት ጊዜ መላውን የፊናንስ ዓለም ይዞ ገደል መግባት እስከሚችል ድረስ ግዙፍ እንዳይሆን ከወዲሁ እንዴት መግታት ይቻላል? ገና በቂ ምላሽ አላገኘም። ሆኖም የጀርመኗ ቻንስለር በአንድ በተፋጠነ ዕድገት ላይ በሚገኝ አገር ለመጀመሪያ በተካሄደው የቡድን-ሃያ መሪዎች ጉባዔ በደቡብ ኮሪያ እስከዚያ የተደረገው ሁሉ ትክክል እንደነበር ነው የተናገሩት።

“ይህን ቀውስ በመታገሉ ረገድ በሰላሣኛዎቹ ዓመታት የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት ከተደረገው አንጻር ብዙውን ነገር በተሻለ መንገድ ነው ያከናወንነው። በጉዳዩ አያያዝ ስርዕት ፈጥረናል፤ የዕድገት በጀት ፓኬት እንዲቋጠር ስናደርግ ቁጠባንም ከመጠን በላይ ፈጥነን አልጀመርንም። አሁን ደግሞ ጠቃሚው ነገር ያኔ የተደረገውን ሶሥተኛ ስህተት አለመፈጸም፤ ማለት ገበያን ከመከለል መቆጠብ ነው”

ይህ ለነገሩም ከዚያን ወዲህ ብዙም አላነጋገረም። የችግሩ መልክ ዛሬ ለወጥ ብሏል። የወቅቱ ችግር የዕዳ ቀውስ የተሰኘ ሲሆን መለያዎቹም በዚህ በአውሮፓ ግሪክ፣ ስፓኝ ወይም ኢጣሊያ ሆነዋል። ይሁን እንጂ የባንኮችና የመንግሥታት የዕዳ ቀውስ እርስበርሳቸው ትስስር ያላቸው ሣይሁኑ አልቀረም። የአውሮፓን የወቅቱን ቀውስ መነሻ ከአሜሪካ ባንኮች ክስረት ጋር ማያያዝ ይቻላል። መንግሥት ጠቅላላው የፊናንስ ስርዓት ተንኮታኩቶ እንዳይወድቅ በሚሰጋበት ጊዜ ባንኮችን ከክስረት ለማዳን መርዳት ይጀምራል። ይህም ለክስረት ያጋልጠዋል ማለት ነው። በጀርመን የኮሎኝ ዩኒቨርሲቲ የባንክ ሙያ ፕሮፌሰር ቶማስ-ሃርትማን-ቬንደልስ እንደሚያስረዱት፤

“ባንኮችን በምናድንበት ጊዜ የመንግሥትን ዕዳ ከፍ ነው የምናደርገው። እናም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የመንግሥቱ የመበደር ብቃት ይመነምናል። በአንጻሩ ደግሞ ባንኮች ለመንግሥት ብድር አቅራቢዎች እንደመሆናቸው መጠን ሁኔታው እነርሱንም መልሶ የሚጎዳ ነው”

ለምሳሌ አሁን ግሪክ ከመጠን በላይ ዕዳ በመሽከሟ ዋጋ እያጡ የሄዱ ሰነዶቿን የገዙ ባንኮችም የችግሩ ቀማሽ እየሆኑ ነው። እንደ ግሪክ ሁሉ በስፓኝና በኢጣሊያም ሁኔታው ይመሳሰላል። በተለይ መንግሥታዊ ክስረት የሚለው አስደንጋጭ ቃል ዛሬ ቋሚነት እያገኘ በመሄድ ላይ ነው። የማዳኛ በጀት ተፈጥሮ እንዲተልቅ ለማድረግ አስቸኳይ ጥረት ተይዟል። የዕዳው መዘዝም ከባድ ተጽዕኖውን እያደር እያሳየ ነው። ነገ ካን ላይ የሚከፈተው የቡድን-ሃያ መሪዎች ጉባዔ ቀደም ባለ ዕቅዱ በመሠረቱ የዓለም ምንዛሪ ስርዓትን ዓቢይ ርዕሱ ባደረገ ነበር። ግን የአጀንዳ ለውጥ ግድ ነው። እናም ዓበይቱ ጥያቄዎች አውሮፓውያን የዕዳ ቀውሱን ለመቋቋም በቅርቡ ውሣኔ ቢያስተላልፉም የኤውሮ ምንዛሪ ክልል ባለበት ሕያው ሆኖ ለመቀጠል ይችላል ወይ? የቡድን-ሃያስ የወደፊት ዕጣ? የሚሉት ይሆናሉ።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች