የቡሽ የአንድ ሳምንት የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት ፍጻሜና ውጤቱ፧ | ዓለም | DW | 17.01.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የቡሽ የአንድ ሳምንት የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት ፍጻሜና ውጤቱ፧

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደ. ቡሽ፧ በመካከለኛው ምሥራቅ ለአንድ ሳምንት ያካሄዱትን ጉብኝት በእሥራኤል ጀምረው፧ ትናንት ግብፅ ላይ በመደምደም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

ፕሬዚዳንት ቡሽና የግብፁ ርእሰ-ብሔር ሆስኒ ሙባረክ፧ በጭውውት ላይ፧

ፕሬዚዳንት ቡሽና የግብፁ ርእሰ-ብሔር ሆስኒ ሙባረክ፧ በጭውውት ላይ፧

ቡሽ፧ የመካከለኛውን ምሥራቅ የሰላም ሂደት ይበልጥ ለማንቀሳቀስና ሌላም ሌላ ተግባር ለማከናወን ፍላጎታቸው እንደነበረ ይገለጽ እንጂ፧ በመጨረሻው፧ ስምንተኛ ዓመት የሥልጣን ዘመን ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት፧ መርኀ-ግብራቸውን በትክክል እንዳላዘጋጁና፧ በዚህም ሳቢያ ያስገኙት ውጤት አነስተኛ መሆኑን ነው የዶቸ ቨለ ባልደረባ ፔተር ፊሊፕ፧ በጽሁፉ ላይ ያሠፈረው። ተክሌ የኋላ፧ የፔተር ፊሊፕን ሐተታ፧ እንደሚከተለው፧ ሰብሰብ አድርጎ አጠናቅሮታል።
መካከለኛውም ምሥራቅ ለስምንት ቀናት ያሰሱት ፕሬዚዳንት ቡሽ፧ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ጉዳዮች አከናውናለሁ ብለው ይንቀሳቀሱ እንጂ፧ ለራሳቸው በእርግጥ፧ ሀቀኛ ሆነው ከቀረቡ፧ ያቀዱት ሁሉ፧ በአመዛኙ ሊሳካ እንደማይችል ከመጀመሪያውም የሚታወቅ ነበረ ማለት ይቻላል። ፕሬዚዳንት ቡሽ፧ በእሥራኤልና በፍልስጤማውያን መካከል የሰላሙ ሂደት እንደገና እንዲቀሳቀስ፧ ከኢራቅ አንጻር የኅብረቱ ግንባር ሰፋና ጠንከር እንዲል፧ በአካባቢው ዴሞክራሲ እንዲገነባ፧ የነዳጅ ዘይት ዋጋም መጠነኛ ይሆን ዘንድ የእርምጃው ተሳታፊ ለመሆን ፈልገው ነበር አንዱም የተሳካላቸው አይመስልም። ሌላው ያልተነገረው ተስፋም ሳይሟላ የሚቀር ነው የመሰለው። ራሳቸው ቡሽ፧. በመጨረሻው የሥልጣን ዘመናቸው፧ መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ አንድ ዓይነት የተሣካ ውጤት እንዲከሠት በማብቃት፧ በታሪክ የሚመዘገብ የክብር ምዕራፍ የሚያገኙበትንም ሁኔታ ማሰላሰላቸው አልቀረም።
ዋናው ርእሰ-ጉዳይ፧ ያላንዳች ጥርጥር፧ የእሥራኤልና የፍልስጤማውያን ውዝግብ ነው። ሰባት ዓመታት ሙሉ፧ በቀጥታ በጉዳዩ ገብተው ጥረት ባለማድረጋቸው፧ በመጨረሻው የሥልጣን ዘመናቸው መፍትኄው ይገኛል ማለት ዘበት ነው። ይሁን እንጂ፧ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኤሁድ ኦልመርትና የፍልስጤማውያን ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ በበኩላቸው ለፖለቲካ ኅልውናቸው ሲሉ ከመተባበራቸውም፧ በዋናው የውዝግቡ ነጥብ ላይ በማትኮር ከምር ለመደራደር እንደገና ተገናኝተው መምከራቸው አልቀረም።
በዚህም ሳቢያ፧ ኤሁድ ኦልመርት፧ ከተጣማሪዎቻቸው መካከል ወግ አጥባቂዎች የሚባሉትን አጥተዋል። በሌላ በኩል፧ ህገ-ወጥ ከሆኑት የሠፈራ ጣቢያዎች አንዱንም እንዲፈርስ አላደረጉም፧ በፍልስጤም ዝግ እንደሆኑ የሚገኙ መንገዶችም እንዲከፈቱ አላዘዙም። በአንጻሩ፧ በጋዛ ወሽመጣዊ ግዛትና በምዕራቡ የዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ፧ በ«ሃማስ« ላይ የጀመሩትን የማጥቃት ዘመቻ እንዳጠናከሩ ናቸው። ላቅ ያለ ሁኔታዎችን የማርገብ እርምጃ ቢወሰድ፧ ለፕሬዚዳንት አባስ፧ የህዝባቸውን ኑሮ ማሻሻል ብቻ ሳይሆን፧ ራሳቸው ቡሽ፧ በፋርስ ባህረ-ሰላጤ አካባቢ በሚገኙ የዐረብ አገሮች፧ በስዑዲ ዐረቢያና በግብፅ ያደረጉት ውይይትም ይበልጥ ሊሠምር በቻለ ነበር። የእሥራኤልና የፍልስጤማውያን የሰላም ሂደት እንዲሠምር የመደገፍ አዝማሚያም ሆነ ዝግጁነት አለ። የዐረብ መንግሥታት ማኅበር፧ ጉዳዩን በጥሞና ሲከተታል ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን ከዋሽንግተን በኩል ከሚሠነዘሩ ያማሩ ቃላት ባሻገር፧ እሥራኤል፧ ባይል የያዘቻቸውን ግዛቶች ለመልቀቅ ዝግጁ ትሆን ዘንድ ነው የሚጠብቅባት።
ይህ እስካልሠመረ ድረስ ደግሞ፧ ቡሽ ከኢራቅ አኳያ የሚከተሉት ፖለቲካ ድጋፍ ያገኛል ተብሎ ከዐረቦች በኩል የሚጠበቅ አይሆንም። ኢራን፧ የአቶም ጦር መሣሪያ በመታጠቅ አደጋ ታስከትላላች ከሚለው የቡሽ ብርቱ አቋም በማፈንገጥ፧ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት፧ ይህ አለመሆኑን አረጋግጧል። ዕረፍት ማግኘት ነው የተፈለገው። ከኢራን ጋር በጀብደኛነት ለመፋለምና ፍጻሜው ወደማይታወቅ ውዝግብ መግባት የሚሻ የለም። በመጨረሻም ዴሞክራሲን መገንባት የሚለውን ዐቢይ ጉዳይ ያለበት ሐሳብ ከቡሽ መቀበል የሚፈልግ አልተገኘም። ሥልጣን ላለማጣት ካለ ጉጉት ብቻ ሳይሆን፧ ዩ ኤስ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ዴሞክራሲ ይገነባ ዘንድ ያደረገችው አስመሥጋኝ ተግባር ባለመኖሩም ነው የዐረብ መንግሥታት መሪዎች ደንታቢስነትን የሚያንጸባርቁት። በኢራቅ የሚታየው ምስቅልቅልም ሌላው ምክንያት ነው።