የቡሽ አስተዳደር በዳርፉር ጉዳይ ያሳየዉ ለዘብተኝነት | የጋዜጦች አምድ | DW | 25.05.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የቡሽ አስተዳደር በዳርፉር ጉዳይ ያሳየዉ ለዘብተኝነት

80 የሚሆኑ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪና የሃይማኖት ድርጅቶች በጋራ በመሆን በሱዳን ዳርፉር አሁንም ካልበረደዉ ጥቃት ሰላማዊዉን ህብረተሰብ እንዲታደግ የጆርጅ ቡሽን አስተዳደር ጠየቁ።

እነዚህ ወገኖች ለኋይት ሃዉስ በፃፉት ደብዳቤ በተለይ የዋሽንግተን መንግስት ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት የአፍሪካ ህብረት በዳርፉር የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎችን ከሚደርስባቸዉ ጥቃት እንዲከላከል የሚያዝ ዉሳኔ ይስጥ ባይ ናቸዉ።
በተጨማሪም በደብዳቤያቸዉ የቡሽን አስተዳደር የጠየቁት የአፍሪካ ህብረትን ተልዕኮ የሚያግዝ ጠንካራ ዓለም ዓቀፍ ሃይል ወደ ስፍራዉ እንዲያንቀሳቅስ ነዉ።
የተጠቀሰዉ ጠንካራ ኃይል የጦር ኃይል ብቻ ሳይሆን ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ከአፍሪካ ዉጪ ከሚገኙ አገራት የገንዘብና የልዩልዩ አገልግሎት አቅርቦትን ያጠቃልላል።
ቡድኑ ከቡሽ ከፍተኛ ረዳት ያገኘዉ ምላሽ ግን ጉዳዩን እንደሚመለከቱት ሆኖም ለጊዜዉ አስቸኳይ ጉዳይ አለባቸዉ የሚል ነዉ።
በትላንትናዉ እለት የቡድኑ ዳይሬክተር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ለመሆኑ ከሰዉ ዘር ጥፋት የበለጠ ምን አስቸኳይ ነገር አለ? በማለት ጠይቀዋል።
በመቀጠልም እስከዛሬ በዳርፉር እየደረሰ ያለዉን የሰዉ ዘር እልቂት ለማስቆም የተደረገዉ ሁሉ በቂ እንዳልሆነና ህሊና ያለዉ ሰዉ ሊቀበለዉ እንደማይችል አስገንዝበዋል።
በርካቶች ፊርማቸዉን ያሰፈሩበት ይህ ደብዳቤ እንደገለፀዉ እስከ አሁን 400,000ዎች ህይወት በዳርፉር ተቀጥፏል።
የቡድኑ ዳይሬክተር እንደሚሉትም አንድ መፍትሄ ካልተገኘ በቀር በያዝነዉ የፈረንጆቹ ዓመት ማለቂያ አካባቢ የሟቾች ቁጥር 1 ሚሊዮን ይደርሳል።
በዳርፉር አካባቢ የተፈፀመዉ የዘር ማጥፋት ወንጀል በፀጥታዉ ምክር ቤት በተሰየመዉ የተባበሩት መንግስታት ልዩ ኮሚሽን የጭካኔ ተግባር መሆኑ ተጠቅሶ በዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ቀርቦ የምረመራም ሆነ የፍርድ ዉሳኔ እንዲሰጥበት መጠየቁ ይታወሳል።
ባለፉት ዓመታት ጉዳዩን በግንባር ቀደምትነት በመምራት በፀጥታዉ ምክር ቤት እንዲታይና ዉሳኔ እንዲሰጥበት ይጠይቅ የነበረዉ የቡሽ አስተዳደር ለአፍሪካ ህብረትና ለግብረሰናይ ድርጅቶች ከሚያደርገዉ መጠነኛ ድጋፍ ሌላ ካለፉት ወራት ወዲህ በዚህ ጉዳይ ላይ ቸልተኝነት አሳይቷል በሚል እየተወቀሰ ነዉ።
ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚጠቁሙት ሱዳን ላይ አዲስ ማዕቀብ በመጣል በሰላማዊዉ ህዝብ ላይ እየደረሰ የሚገኘዉን ጥቃት ማስቆም ይቻላል።
ሆኖም በሱዳን የነዳጅ ኢንደስትሪ ከፍተኛዉ ድርሻ ላይ ገንዘቧን ያዋለችዉ ቻይና ወይም የጦር መሳሪያ ለካርቱም እያቀረበች በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የምታፍሰዉ ሩሲያ ይህ እርምጃ በፀጥታዉ ምክር ቤት ቢቀርብ ድምፅ የመስጠታቸዉ ነገር እያከራከረ ነዉ።
በዚያ ላይም ዩናይትስ ስቴትስ ልትወስድ የምትሞክረዉ ማንኛዉም ጠንካራ እርምጃ ታሪካዊዉና በብዙ ፈተና ለስምምነት የደረሰዉ የሱዳን መንግስት የተቃዋሚ ኃይሎች የሰላም ጉዳይ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።
ቡሽ ራሳቸዉ ካለፈዉ ዓመት ማብቂያ ጀምሮ በዳርፉር ጉዳይ ዝምታን መርጠዋል የሚለዉ የተቆርቋሪዎቹ ስጋት በቅርቡ በሱዳንና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል «በሽብር ላይ ዓለም ዓቀፍ ጦርነ» በተሰኘ አዲስ ፓሊሲ ሳቢያ የጀመሩት የመረጃ አገልግሎት ትብብር የተዓቅቦዉ ምክንያት ነዉ የሚል ነዉ።
በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ከተፈፀመዉ ከመስከረም 1 1993ቱ የሽብርተኞች ጥቃት በፊት የአልቃይዳዉን መሪ ኦሳማን ቢንላደንን ካርቱም ማስተናገዷን ደግሞ ጠንቅቃ ታዉቃለች ነዉ የሚሉት እነዚህ ወገኖች።
በቅርቡም የካርቱምን የመረጃ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ሳላህ አብደላ ጎሽን በድብቅ ዋስንግተን በማምጣት ከአቻዎቻቸዉ ጋር እንዲወያዩ ተደርጓል።
ሎስ አንጀለስ ታይምስ ሰሞኑን እንደዘገበዉም እኝህ ሰዉ በዳርፉር ለተፈፀመዉ ወታደራዊ ጥቃት ተጠያቂ ከሆኑት ባለስልጣናት መካከል ናቸዉ።
እኝህን ሰዉ ወደ ዋሽንግተን ማምጣት ማለት በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ወቅት በርካታ አይሁዳዉያንን የፈጁትን የናዚ አየርሃይል ሃላፊና ሌሎች አጋሮቻቸዉን እንደማምጣት ነዉ ይላሉ።
በዚህም በመሪዎቹ ዙሪያ የፓሊሲ ለዉጥ እያዩ ነዉ ያ ደግሞ እጅግ የሚያሳስብ ጉዳይ መሆኑን እየገለፁ ነዉ።
ሌላዉ ደግሞ የአሜሪካዉ ምክትል የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሮበርት ዞሊክ ባለፈዉ ወር በሱዳን ጉብኝት ካደረጉ በኋላ የሰጡት አስተያየት ነዉ።
ዞሊክ ባደረጉት ንግግር በዳርፉር የተፈፀመዉ የሰዉ ዘር ማጥፋት ነዉ ለማለት ከመቆጠባቸዉ ሌላ በመብት ተቆርቋሪዎቹም ሆነ በተባበሩት መንግስታት የተጠቀሰዉ የሟቾች ቁጥር የተባለዉን ያህል አይሆንም ብለዋል።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ እነዚህ ተቆርቋሪዎች የሚጠይቁት የማቾች ቁጥር በዛም አነሰ በዳርፉር ለችግርና ጥቃት ተጋልጦ እየጠፋ ያለዉ የሰዉ ህይወት ቀላል አይደለም የሚል ነዉ።
ከ10 ዓመት በፊት ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ በኃይል ገብቶ ከመገላገሉ በፊት 2,000 የቦስንያ ሙስሊሞች ህይወት አልፏል።
አሁንስ ለዳርፉር የሚገባዉን ያህል ሳይሰራ ምንያህል ህዝብ እስኪያልቅ ይጠበቃል?