የቡርኪና ፋሶ ጊዚያዊ ሁኔታ | አፍሪቃ | DW | 03.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቡርኪና ፋሶ ጊዚያዊ ሁኔታ

ብሌዝ ኮምፓዎሬ ከቡርኪና ፋሶ ፕሬዝደንትነት መልቀቃቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ጦር የሽግግር መንግስት መመሥረቱን ይፋ አድርጓል። ይሁንና ተቃዋሚዎችና ተከታዮቻቸው በሉቴናንት ኮሎኔል ያኮባ ኢዛክ ዚዳ የሚመራው የሽግግር መንግስት ስልጣኑን እንዲያስረክብ በመወትወት ላይ ናቸው።

ብሌዝ ኮምፓዎሬ የ27 ዓመት መንበረ ስልጣናቸውን በ 15 ሰከንድ ንግግር ቢለቁም ቡርኪና ፋሶ መረጋጋት ርቋታል። የቀድሞው ፕሬዝደንት ስልጣን መልቀቃቸውን ባረጋገጡ ቅጽበት በዋና ከተማዋ ኡጋዱጉ የታየው ደስታና ሃሴት እንዳጀማመሩ አልቀጠለም። የሳምንቱን የመጨረሻ ቀናት ሱቆች ተዘግተው ቢቆዩም የሽግግር መንግሥቱን እንዲመሩ የተመረጡት ሉቴናንት ኮሎኔል ያኮባ ኢዛክ ዚዳና የጦር ሠራዊቱ አዲስ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የመሠረቱት የትብብር መድረክ የሽግግር መንግስቱን በሚመራው ወታደራዊ መንግስት ደስተኛ አይመስሉም። በመድረኩ ተሳታፊ ከሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መካከል ለቢቢሲ አስተያየታቸው የሰጡት አዳም ካናዞ ሉቴናንት ኮሌኔል ያኮባ ኢዛክና የጦር ሠራዊቱ የሽግግር መንግስቱን መምራት እንደሌለባቸው ያምናሉ።

''ይህን ሽግግር በጋራ ልንመራ ይገባል። ቢሆንም የሽግግር መንግስቱ በሲቪል ነዋሪ ሊመራ ይገባል። ምክንያቱም የቡርኪና ፋሶ ዜጎች ዴሞክራሲያቸውን በጦር ሠራዊቱ ሲነጠቁ ማየት አይፈልጉም።''

የአፍሪካ ህብረት፤ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ ትብብር ማህበረሰብ(ECOWAS)፤ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ወታደራዊው መንግስት በአስቸኳይ ስልጣኑን ለሲቪል እንዲያስረክብ እና የቡርኪና ፋሶ ዜጎች ተቃውሞ የማድረግ ነጻነታቸውን እንዲያከብር አሳስበዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ጦር ሠራዊቱ ስልጣኑን ካላስረከበ ማዕቀብ እንደሚጥል አስጠንቅቋል። ሙዚቀኛ ና የተቃውሞ ጎራ መሪ የሆኑት ሳማስ ኬ ሌጃህ ወታደራዊው መንግሥት የተወሰነ ጊዜ ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ።

''አሁን በሃገሪቱ የተወሰነ ሰላም አለ። አሁን ወደ ምርጫ የሚመራንን ነገር በጋራ በመወያየት ማግኘት ይኖርብናል። አንዳንድ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች ህዝቡ 'ወታደሮች አንፈልግም' በማለት እንዲቃወም ጥሪ የሚያደርጉበት ምክንያት አልገባንም። መጀመሪያ ቁጭ ብለን በመወያየት ለችግሩ መፍትሄ ማምጣት አለብን። ሳራ ሴሬሜ የተባሉ ፖለቲከኛ ለምሳሌ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሆናቸውን ለማወጅ ወደ ብሄራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያው ሄደው ነበር። እንዲህ አይነቱን ነገር ፈጽሞ መረዳት አንችልም። አሁን በሀገሪቱ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለመረዳት እየሞከርን ነው። ቢሆንም በቅርብ ጊዜ ነገሮች ለሁሉም ግልጽ ይሆናሉ ብለን እንጠብቃለን።''

ለጊዜው የሽግግር መንግስቱን የሚመሩት ሉቴናንት ኮሎኔል ያኮባ ኢዛክ ዚዳ እና ጦር ሰራዊቱ 'ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር'በሚል ተቃዋሚዎችን ከአደባባዮችና ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያው በተኩስ ጭምር ለመበተን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ሁኔታውን በሠራዊቱ የተፈጸመ መፈንቅለ መንግስት ለማለት ዳር ዳር እያሉ ናቸው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic