የቡርኪና ፋሶ አጠቃላይ ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 28.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቡርኪና ፋሶ አጠቃላይ ምርጫ

የቡርኪና ፋሶ ሕዝብ በነገው ዕለት፣ በጎርጎሪዮሳዊው ህዳር 29 ቀን 2015 ዓም አዲስ ፕሬዚደንት እና አዲስ ምክር ቤት ይመርጣል። ሕዝቡ ይህንን ቀን በትልቅ ጉጉት ነው የሚጠባበቀው፣ ምክንያቱም፣ ይህ በሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ነው የሚታሰበው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:46

የቡርኪና ፋሶ አጠቃላይ ምርጫ

ነገ በሕዝብ ድምፅ የሚመረጥ መንግሥት፣ የቀድሞው ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬ በሕዝብ ዓመፅ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ባለፉት 13 ወራት ሃገሪቱን ሲመራ የቆየውን የሽግግር መንግሥት ይተካል።  

19 ሚልዮን ሕዝብ በሚኖርባት ቡርኪና ፋሶ ነገ የሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ሃገሪቱን እንደገና ወደ ዴሞክራሲያዊው ስርዓት የሚመልስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። «ባሌ ሲትዋያ» የተባለው የሕዝብ ንቅናቄ ከሲቭሉ ማህበረሰብ ጋር ባንድነት በጎርጎሪዮሳዊው ጥቅምት ፣ 2014 ባካሄደው ዓመፅ ስልጣን ላይ 27 ዓመታት የቆዩትን እና ሕገ መንግሥቱን በማስቀየር ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ፈልገው የነበሩትን ብሌዝ ካምፓዎሬን ከስልጣን ማስወገዱ የሚታወስ ነው።

ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ላይ በተወዳዳሪነት የቀረቡት እጩዎች የሽግግሩ መንግሥት አባል ያልነበሩ መሆን አለባቸው። ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በተወዳዳሪነት ከቀረቡት 14 እጩዎች መካከል ሁለቱ ለከፍተኛው ስልጣን የመብቃት ዕድላቸው ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል። በቡርኪና ፋሶ ካሉት ፓርቲዎች መካከል የታወቁት የመሻሻል እና ለውጥ ህብረት ፓርቲ፣ እንዲሁም፣ በምህፃሩ «ኤም ፒ ፒ» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የመሻሻል የሕዝብ ንቅናቄ ፓርቲ ናቸው። የመጀመሪያው በምህፃሩ «ኤም ፒ ፒ» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የመሻሻል የሕዝብ ንቅናቄ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር የ58 ዓመቱ ሮኽ ካቦሬ እና የመሻሻል እና ለውጥ ህብረት ፓርቲ እጩ የቀድሞው የገንዘብ ሚንስትር ዲያብሬ ሴፍሪን ናቸው። ሁለቱ እጩዎች በመላይቱ ሃገር በመዘዋወር ባደረጉት የምርጫ ዘመቻ ላይ በግብርና ላይ ያተኮረውን የሃገሪቱን ኤኮኖሚ ለማሳደግ ቃል ገብተዋል።

የሃገሪቱ ነዋሪዎች፣ ብሎም፣ ቡርኪናቤዎቼ የነገውን የምርጫውን ዕለት በትልቅ ጉጉት በመጠባበቅ ላይ ሲሆኑ፣ ምርጫዉ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እና ሕዝቡ እየዋሸዉ ለረዥም ዘመን የሚገዛዉ መሪ ሳይሆን ታማኝ የሆነ መሪ እንደሚፈልግ ያስታወቀው ድምፁን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠው የስነልቡና ተማሪ ፉሴይኒ ናኮሌምዳ ትክክለኛ ርምጃ ለመውሰድ ቆርጦ መነሳቱን ገልጾዋል።

Burkina Faso Präsidentschaftswahl Fousseni Nakolemda

ፉሴይኒ ናኮሌምዳ

« ከ27 የካምፓዎሬ አምባገነን አገዛዝ ዓመታት በኋላ በሃገራችን ሁኔታዎችን መቀየር የኛ ፈንታ ነው። እና አሁን ጥሩ ምርጫ ማካሄድ አለብን። ይኸው ምርጫችንም እያንዳንዱ ፓርቲ ፣ እያንዳንዱ እጩ ለወጣቶች ይዞ በሚቀርበው ፕሮግራም ላይ ጥገኛ ይሆናል። ሕዝብን የሚያጋጭ ፖለቲካ አንፈልግም። እውን የማይሆን ቃል እንዲገባልንም አንፈልግም። ምክንያቱም በመጨረሻ ባዶ እጃችን የምንቀረው እኛ ነን። የምንፈልገው ሀቀኛ ለውጥ ነው።»

ከቡርኪና ፋሶ ሕዝብ መካከል 65% ከ25 ዓመት በታች የሚገኝ ወጣት ነው። ለምርጫ የቀረቡት ተወዳዳሪዎች ሁሉ ወጣቱን ለመሳብ ብቻ ሳይሆን፣ ሙስናን ለመጥፋት፣ የስራ ቦትን ለመፍጠር እና የሃገሪቱን መሰረተ ልማት ለማሻሻል በምርጫ ዘመቻ ወቅት ቃል ሲገቡ ተደምጠዋል። ይሁንና፣ ተወዳዳሪዎቹ የገቡትን ቃል ማሟላት መቻላቸውን በመዲናይቱ ዋጋዱጉ የሚገኘው ሀንስ ዛይድል የተባለው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ራልፍ ቪቴክ ተጠራጥረውታል።

« አንዱ እጩ እንኳን የገባውን ቃል እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርግ አሳማኝ ማስረጃ አላቀረበም። ማብቂያ የሌለው ቃል ይገባሉ። አንዳንድ ብዙ ትኩረት ያላገኙ እና የመመረጥ ዕድል የሌላቸው እጩዎች አሉ። ፕሮግራማቸውን ግልጽ እና ትክክል በሆነ መንገድ ያቀረቡትን ዦን ባብቲስት ናታማን መጥቀስ ይቻላል።

5,5 ሚልዮን የመምረጥ መብት ያለው ሕዝብ ድምፁን እንዲሰጥ የተጠራበት ፕሬዚደንታዊ እና ምክር ቤታዊ ምርጫ ከሶስት አሰርተ ዓመታት በኋላ በቡርኪና ፋሶ የሚካሄደው የመጀመሪያ ነፃ ምርጫ ይሆናል። ከሁለት ወር በፊት ከሃገሪቱ ጦር ኃይል መካከል ከፊሉ የሽግግሩን መንግሥት ለመገልበጥ ሙከራ ያካሄደባት የቡርኪና ፋሶ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ የሽግግሩ መንግሥት ከ20,000 የሚበልጡ የፀጥታ ኃይላት አሰማርቶዋል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic