የቡሩንዲ ቀዉስና የሙሴቬኒ ሽምግልና | አፍሪቃ | DW | 15.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቡሩንዲ ቀዉስና የሙሴቬኒ ሽምግልና

የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የቡሩንዲን መንግስትና የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችን ማደራደር ጀመሩ። ለ29 አመታት ዩጋንዳን የመሩት ሙሴቬኒ የቡሩንዲ ተቀናቃኞች ጎሰኝነትን በማስወገድ ለአንድነት ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:01
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:01 ደቂቃ

የቡሩንዲ ቀዉስና የሙሴቬኒ ሽምግልና

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቡሩንዲ ፖለቲከኞች ልዩነቶቻቸውን መፍታት ካልቻሉ 300 ሺ ሰዎች ወደሞቱበትና 12 ዓመታት ወደዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት ልትመለስ ትችላለች በማለት ስጋቱን ገልጧል።


የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የቡሩንዲውን ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ እና ተቃዋሚዎቻቸውን መሸምገል ጀመሩ። ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ የቡሩንዲ መንግስት ተወካዮችንና የተቃዋሚ መሪዎችን አግኝተው አነጋግረዋል። ውይይቱን በቡሩንዲ ታዋቂ የተቃዋሚዎች መሪ የሆኑት አጋቶን ርዋሳ እንደታደሙበት ነው የተገለጸው። ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ከውይይቱ ቀደም ብሎ በሰጡት አስተያየት የቡሩንዲ መሪዎች ለአንድነት ጠንክረው እንዲሰሩና የልማት ጠንቅ ነው ያሉትን ጎሰኝነት እንዲያስወግዱ አሳስበዋል። የቡሩንዲ መንግስት ተቃዋሚዎችን መግደልን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎች ይፈጽም ነበር የተባለውን የመንግስት ደጋፊ የወጣቶች ቡድን ትጥቅ በማስፈታቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከጎርጎሮሳዊው 1986 ዓ.ም. ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙትና ለሽምግልናው በምስራቅ አፍሪቃ አገራት ማህበረሰብ የተመረጡት ሙሴቬኒ የፖለቲከኞቹ መከፋፈል በአገሪቱ እድገት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብለዋል።

Uganda Präsident Museveni

ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ

«እንዲህ ዓይነት በርካታ ሆቴሎችና ፋብሪካዎች ሲኖሯችሁ ነው ቡሩንዲ የምታድገው። የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪዎች ሊያድጉ የሚችሉት እዚህ ባሉት ሰዎች ምክንያት ነው። ነገር ግን የፖለቲካ አመራሩ እንዲህ ዓይነት ባህሪ ካሳየ ፣ ሁልጊዜም ግጭት ብቻ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ጥለው ይጠፋሉ። በዚህ ደግሞ ቡሩንዲ ልታድግ አትችልም።»

አሁን አገሪቱን የሚያስተዳድረው «ሲ ኤን ዲ ዲ-ኤፍ ዲ ዲ»ፓርቲ ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛን ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በእጩነት ማቅረቡን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ግጭትና ተቃውሞ አገሪቱን ወደርስ በርስ ጦርነት ይመልሳታል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ባለፈው ግንቦት ወር በፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ላይ በጦር መኮንኖች የተሞከረው መፈንቅለ መንግስት በደጋፊዎቻቸው ቢከሽፍም ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ዜጎች መካከል 77 ሰዎች ተገድለዋል።

የቡሩንዲ ምርጫ ከታቀደለት ጊዜ ለሁለት ሳምንታት ቢራዘምም አሁንም በተቃዋሚዎችና በገዢው ፓርቲ መካከል ያለው መቃቃር በአገሪቱ ደህንነት ላይ እንዳጠላ ነው። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የጸጥታ ሃይሎች በሰሜናዊ ቡሩንዲ የሙዪንጋ ግዛት ከ100 በላይ ዓማጽያንን ከነጦር መሳሪያቸው በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ደጋፊ የነበሩት ጄኔራል ሊዮናርድ ንጌዳኩማና በፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ መንግስት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዘጋጀታቸውን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

መፍትሄ ያጣው የሁለቱ ወገኖች ፍጥጫ በብሩንዲ ዜጎች ላይ ስጋት ማጫሩ ግን አልቀረም። ሳራ የተባሉ የልጆች እናት በስጋት ውስጥ ከሚኖሩ ዜጎች መካከል አንዷ ናቸው።
« ወደ መሀል አገር እሄዳለሁ። በቡጁምቡራ በምንኖርበት አካባቢ ሁሌ ሲተኮስ እንሰማለን። ሕፃናት ልጆች አሉኝ። ሁኔታው ለኔ ለትልቋ እንኳን እጅግ አስፈሪ ነው። ተኳሾቹ ማን እንደሆኑ አናውቅም። ምክንያቱም የሚተኩሱት ማታ ነው። ከዚህ ሌላ ደግሞ፣ ሰዎች የዚህ ወይም የዛኛው የፖለቲካ ፓርቲ አባል ናችሁ በሚል ይታሰራሉ፣ ይከሰሳሉ። እና ጋደኛህ ሲገደል ወይም በየቀኑ የተኩስ ድምፅ ስትሰማ፣ በተለይ ሕፃናት ባሉበት፣ በጣም አሰቃቂ ነው።»

nach Putschversuch - Präsident Pierre Nkurunziza zurück im Amt

ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ

የፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ መንግስት ጎረቤት አገር ርዋንዳ ተቃዋሚዎችን ትረዳለች ሲል ይከሳል። ርዋንዳ በብሩንዲ እየተባባሰ በመጣው ግጭት ውስጥ እጄ የለበትም ስትል አስተባብላለች።

በግጭቱ ና የፖለቲካ ውጥረቱ ምክንያት 150 ሺ የቡሩንዲ ዜጎች የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው መሸሻቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል። አብዛኞቹ ወደ ሩዋንዳ የተሰደዱ ሲሆን 30 ሺ ያህሉ ከዚህ ግጭት መቀስቀስ በኋላ በተቋቋመው የማሃማ የስደተኞች ጣቢያ ይኖራሉ። የህግ ባለሙያው ዶሜስየን አሁን በቡሩንዲ የተቀሰቀሰው ግጭት ሁሉንም የአገሪቱን ክፍሎች መጉዳቱን ያምናሉ።

« በኃይል እርምጃው አንዱ ከሌላው ሰፈር ይበልጥ ተጎድቶዋል ለማለት አልችልም። እርምጃው መላይቱን አገር ጎድቶዋል ብዬ ነው የማምነው። ምክንያቱም እኔ እንደታዘብኩት፣ ሰዎች ተቃውሞ ባካሄዱባቸው ባንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ ሰፈሮች ፣ ክፍላተ አገር ሁሉ ተደብድበዋል። »

የቡሩንዲ ጦር ባለፈው ሰኞ 31 ተጠርጣሪ አማጽያንን መግደሉንና 170 በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።ባለፈው ግንቦት ወር የተካሄደውና የንኩሩንዚዛ ፓርቲ በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ ያሸነፈበት የእንደራሴዎች ምርጫ በተቃዋሚዎች ተቀባይነት ያጣ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ክፉኛ መተቸቱ አይዘነጋም።


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic