የበዓል ገበያ በኢትዮጵያ | ኤኮኖሚ | DW | 14.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የበዓል ገበያ በኢትዮጵያ

ዘንድሮ የአዲስ አመት እና የኢድ አል አድኻ በዓላት ግብይት በተቃውሞ እና አለመረጋጋት ደብዝዘዋል። በዓላቱም እንደ ወትሮው የፌሽታ አልነበሩም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:33

የበዓል ገበያ

የዘንድሮ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት እና የኢድ አል አድኻ (አረፋ) በዓላት በገበያ አለመረጋጋት ውስጥ ተከብረዋል። በኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች የተስተዋሉት ተቃውሞዎች እና ግጭቶች በበዓል ገበያው ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አልቀረም። ለምሳሌ እንኳ ከኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች የቀንድ ከብቶችን ወደ አዲስ አበባ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች በአለመረጋጋቱ ሳቢያ ንግዳቸውን ለመከወን መቸገራቸው ተሰምቷል። የሳምንታዊው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘጋቢ ዳዊት እንደሻው የአዲስ አመት ግብይቱን ፈትሾ እንደወትሮው እንዳልነበር ታዝቧል።
አዲስ አመት ከመከበሩ ቀደም ብሎ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች በማህበራዊ ድረ-ገፆች በጠሩት የግብይት አድማ ሱቆች መዘጋታቸውን፤ ከተሞች እና የመገበያያ ሥፍራዎች ፀጥ ረጭ ማለታቸውን ፌስቡክን በመሰሉ የማህበራዊ መገናኛ አውታሮች የተሰራጩ ምሥሎች አሳይተዋል። በተወሰኑ ከተሞች አድማውን ተላልፈው አገልግሎት ለመስጠት የሞከሩ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። ዶይቼ ቬለ በፌስቡክ ማህበራዊ ድረ-ገፅ የግብይት አድማውን ላይ ባካሔደው ውይይት አወዛጋቢ ዘለፋን ጨምሮ ተፃራሪ ሐሳቦች አስተናግዷል።
በምዕራብ ሐረርጌ ጭሮ ከተማ ነዋሪ እንደሆኑ የገለጡት አንቲሽ ሳልቫቶር «እኛ ያለንበት አካባቢ ምንም ዓይነት ለውጥ የለም፣ ተዘወውረን ሁሉን አይተነዋል። ሠላማዊ ግብይት ነው ያለው።» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። በቡራዩ ከተማ ከታ አካባቢ ነዋሪ ነኝ ያሉት ኬና ለሚ «ሁሉም ሱቆች ዝግ ናቸው። የሞባይል ካርድ ፍለጋ ያልሔድኩበት የለም። እንደ እድል ሆኖ ግማሽ መስኮቱን ከፍቶ የተወሰኑ ሸቀጦች የሚሸጥ ሱቅ አገኘሁ። ይህ በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር የሚደረገውን ትብብር ይጠቁማል።» ብለዋል። አኒ ዲዴ በበኩላቸው «እኔ አሁን ባለሁበት አካባቢ (አምቦ) በሚገርም ሁኔታ አድማው እየተተገበረ ነው። ሲጀመር አዲስ አመት ብሎ ነገር የለም።» ብለው ነበር። አብዱላሒ አሊ ግን « እንደ እኔ አስተያየት ተቃውሞው የሰዎችን ነፃ አስተሳሰብ እና ፍላጎት ያላከበረ ፤ያላስተናገደ ነው። ምክንያቱም አድማውን ያልተቀበለ ግለሰብ ዛቻ እና ድብደባ እንዲሁም በንብረቱ ላይ ጉዳት ማድረስ ይከተላል፡፡» ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጠዋል። የግብይት አድማውን ሐሰት ያሉ አልፈውም መረን የለቀቀ ዘለፋ የፃፉም አልጠፉም። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ግን በኦሮሚያ ክልል የተካሔደው የግብይት ተቃውሞ ስኬታማ ነበር ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ 2008ን ሸኝታ 2009ኝ ልትቀበል ሽር ጉድ ስትል የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለመጪዎቹ በዓላት የበግ አቅርቦት እጥረት ገጥሞኛል ማለቱ ተሰምቶ ነበር። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው አለመረጋጋትም ይሁን በኦሮሚያ ለአንድ ሳምንት የተጠራው የግብይት አድማ በቀንድ ከብት፤ በግ እና ፍየል አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ ስለማሳደሩ የተጠየቁት የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገ/ሚካኤል ግን «በፍፁም» ሲሉ ይናገራሉ። ኃላፊው ድርጅታቸው ለሁለቱ በዓላት ከቀደሙት አመታት የበለጠ ደንበኞቹን ማስተናገዱንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሥጋ አምራቾች እና ላኪዎች ማሕበር በሥሩ አስራ አንድ አባላት አሉት። የማሕበሩ አባላት በአመት እስከ 19 ሺ ቶን የበግ እና የፍየል ሥጋ ዱባይ፤ ጅዳ እና ሪያድን ወደ መሳሰሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ከተሞች ይልካሉ። በዚህም ከ95 እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ለአገሪቱ ገቢ ያስገኛሉ። በኢትዮጵያ የተከሰተው አለመረጋጋት በስራቸው ላይ ተፅዕኖ ስለ ማሳደሩ የማሕበሩን ዋና ፀኃፊ አቶ አበባው መኮንን ጠይቂያቸው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት ወቅታዊው የፖለቲካ ውጥንቅጥም ይሁን በኦሮሚያ ክልል ተጠርቶ የነበረው የግብይት አድማ ምንም አይነት ተፅዕኖ አላሳደረም ብሏል። ጋዜጠኛ ዳዊት እንደሻው ግን በቀንድ ከብት ብቻ ሳይሆን በጥራጥሬ እና የጤፍ ግብይት ላይ ጭምር ለውጦ መኖራቸውን ታዝቧል።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic