የበርሊኑ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ትርዒት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 10.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የበርሊኑ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ትርዒት

ዘንድሮ 90 ዓመት ሞላው፤ የበርሊኑ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት! ከ 9 ዐሠርተ- ዓመት በፊት፣ «ትልቁ የጀርመን የኤልክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት» ይባል በነበረበት ዘመን፤ ሲጀመር፣ ፣ ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ ፣ የዚያን ዘመን

የቴክኖሎጂ ውጤቶቻቸውን ይዘው የቀረቡ 242 ድርጅቶች ነበሩ የተካፈሉ። ራዲዮ፣ ማዳመጫ መሣሪያና የመሳሰሉት ብርቅ በነበሩበት በዚያ ዘመን 180 ሺ ሕዝብ ትርዒቱን መመልከቱንም ነው መዛግብት የሚያስረዱት። ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ሕብረተሰብ ቅንብራችን ፣ ከዘንድሮው የበርሊን ዓለም አቀፍ የኤልክትሮኒክ መሣሪያዎች ትርዒት ጋር ፤ ሥነ ቴክኒክ ኑሮን ለማቃለል ፣ ዘናም ለማድረግ ያለውን አስተዋጽዖና ሳንኩንም እብረን እንቃኛለን ።

Samsung Galaxy Note Smartphone IFA Berlin

ዘንድሮ ፣ ለ 54ኛ ጊዜ፤ በ 150,000 ስኩየር ኪሎሜትር ቦታ ላይ የተዘጋጀውን፤ 1,500 ያህል የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ያቀረቡ ኩባንያዎች የተሳተፉበትንና ዛሬ የተደመደመውን ትርዒት፣ ከ 60 ከማያንሱ አገሮች የመጡ 240 ሺ ያህል ተመልካቾች ሳይጎበኙት አልቀሩም። በዘንድሮው ትርዒት የተመልካቹን ዐይን ከሳቡት አንዱ Ultra HDየተሰኘው መስታውት ሣጥኑ እንደተለመደው ቀጥ ያለ ሳይሆን የታጠፈና ከ 3 ማዕዘን ምሥል የሚያሳይ መኖሪያ ቤትን ሲኒማ ቤት የሚያስመስለው ቴሌቭዥን ነው ተብሏል። ዋጋው፣ ዝቅተኛው 3ሺ ዩውሮ ነው። ከተመለከቱት ጀርመናውያን መካከል አንዱ በመደመም እንዲህ ነበረ ያለው።

1, «ፍጹም እፁብ ድንቅ ነው፤ ይህ ደግሞ ወደፊት ይበልጥ የሚያገለግል ነው። እጅግ አዝናኝ ነው፤ ቀለሙ ፤ ያማረ -የደመቀ ነው። በአጭሩ ፣ ግሩም ነው። »

ትርዒት ተመልካቾች አብዛኛውን ጊዜ በቡድን ጎራ ስለሚሉ፤ በዚያ የተገኙ አባትና ልጅ ከአድናቆት ጋር እንዲህ ሲሉ ነበረ የተደመጡት።

«-ቴሌቭዥን ማየቱን ከሞላ ጎደል ትቼዋለሁ።

-ትመለከታለህ ቴሌቭዥን ወይስ ትተኸዋል?

-እንዴታ! ግን የምመለከተው በኢንተርኔት ነው። አዝናኝ ፤ ማራኪና አዲስም ሆኖ ያገኘሁት እሱን ነው።ያም ሆኖ ለሰዎች ተፈላጊ ነው ብዬ መናገር ይከብደኛል፤ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑም አልታየኝም ፤ ዋጋው ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ፣ አይቀመሰም ፤ ውድ ነው።»

በትርዒቱ ፤ ተመልካቾችን ያማለለው ከቻይና የቀረበ ቻንግሆንግ የተባለ ቴሌቭዥን ነው። በ 3 ማዕዘን ተንቀሳቃሽ ምስልን የሚያሳይ ነው። ያን ከተመለከቱት አንዱ ቀጠል በማድረግ---

«እንደሚመስለኝ ፤ ያለመነጽር ከሚታዩት በለሦስት ማዕዘን ተንቀሳቃሽ ምስል ከሚያሳዩት ቴሌቭዥኖች ይኸኛው እጅግ የሚመረጥ ነው። የዚህ ዓይነት ቴሌቭዥኖችን ሣጥኖች(screens) ባለፉት 7 ዓመታት ስመለከት ቆይቼአለሁ። ግን እንደዚህኛው ያጓጓኝ የለም። በደንብ የሚሠራ፣ ለገበያ ቶሎ ቢቀርብ በሰፊው ሊሠራጭ የሚችል ነው ባይ ነኝ ፣ አስደናቂ ቴሌቭዥን ነውና!»

በሥነ- ቴክኒኩ ዓለም የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን በተመለከተ በየጊዜው የተለያዩና የተቆራኙ ተግባራትን የሚያከናውኑ የረቀቁ አዝናኝ ቁሳቁሶች እንደሚቀርቡ የታወቀ ነው። የሰሞኑ ትርዒት አንዱ ዓላማ የሚመስለው፤ በመጪው የገና ወቅት ገበያ ላይ የሚቀርቡትን ለማስተዋወቅና ትርፍ ጭምር ለመዛቅ ነው። ዘመናዊ እየተባሉ በየጊዜው የሚቀርቡትን ተደራራቢ ጥቅም የሚሰጡትን ለጎብኚ ዐይን አዋጅ የሚያስመስሉበትን የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ዓይነት በተመለከተ ፣የበርሊኑ ዘጋቢአችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል የታዘበውን እንዲያብራራልን ጠይቄው ነበር።--

በየጊዜው የሚቀርቡት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ፤ ወጣት፤ ጎልማሣ ፤ አዛውንትን፣ ሁሉንም እንዲያገለግሉ ታስቦ ሲሠሩ ፤ በጾታም ደረጃ፤ ለሴቶች ይበልጥ ተፈላጊ ወይም አጓጊ የሚመስሉትን የኤሌክትሮኒክሱ ኢንዱስትሪ በሚገባ ሳያተኩርባቸው አልቀረም።

ከሩቅ ፤ በጉዞም ላይ ሆኖ ሰው፤ በመኖሪያ ቤቱ የሚገኙ አንዳንድ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን በዘመናዊው የSdeነ ቴክኒክ ጥበብ ፤ የተፈለገውን እንዲያደርጉ ማዘዝ መቻሉ፤ አንዳንዴም ቅንጦቱን የበዛ ማስመሰሉ የሚካድ አይደለም። ከኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች በተለይ፤ የተለያዩ አገልግሎቶችን ከሚያበረክቱ የእጅ ስልኮች (ስማርትፎንስ) ጋር ያለ ፍቅር ምን ይሆን መጨረሻው የሚል ጥያቄ ቢያስነሣ የሚያስደንቅ አይሆንም። በአውቶቡስ ፤ በትራም ፤ በተለያዩ ቦታዎች ትንሽ ትልቁ ፣ ጸጥ -እርጭ ብሎ ዓይኑን እነርሱ ላይ ተክሎ ማየት በጣም የተለመደ ሆኗልና!

አዳዲስ የዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ውጤት ፤ አንዳንዴ መኖሪያ ቤትን ስቱዲዮ እያስመሰሉት ነው። የበርሊኑን በመሳሰሉ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት ፤ ለጋዜጠኞች ይበልጥ የሚያጓጉ ፤ የሚጠቅሙ ምን ዓይነት ይሆኑ?

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic