የበረኃዋ እንቁ ፓልሚራ ከ«IS» ይዞታ በኋላ | ባህል | DW | 08.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የበረኃዋ እንቁ ፓልሚራ ከ«IS» ይዞታ በኋላ

ለሰባት ወራት ያህል እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራዉ ሽብርተኛ ቡድን ተይዛ የቆየችዉ የበራኃዋ አልማዝ ተብላ የምትታወቀዉየሶርያዋ ጥንታዊት ከተማ ፓልሚራ ከሁለት ሳምንታት ወዲህ በሶርያዉ ፕሬዚዳንት አሳድ መንግሥት እጅ እስር መልሳ መግባትዋ በተልይ ደግሞ የታሪክና የቅርስ ጥናት ዘርፍ ባለሞያዎች የፓልሚራ መልሶ መለቀቅ እሰየዉ አሰኝቶአል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:25
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
16:25 ደቂቃ

የበረኃዋ እንቁ ፓልሚራ ከ«IS» ይዞታ በኋላ

የሶርያ ጥንታዊ ቅርስ ጥናት ምሁርዋ ፈረንሳዊትዋ የታሪክ ተመራማሪ አኒ ሳርትር ፎሪያ ነገሩ እፎይታን ቢሰጥም ለበረሃዋ እንቁ ለፓልሚራ አሳድም ቢሆኑ ከ«IS» አይሻሉም ባይ ናቸዉ። በሶርያ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ከ 40 ዓመታት በላይ ምርምርና ጥናት ያካሄዱት አኒ ሳርትር ፎሪያ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ አሸባሪዉ ቡድን «IS» በከፊል ያወደማትንና በመንግሥታቱ ድርጅት እዉቅና ያገኘችዉ ፓልሚራን ዳግም መልሶ መገንባት፤ የአሻንጉሊት አልያም የሕጻናት መጫወቻ መንደር ማድረግ ነዉ ማለታቸዉም ተገልፆአል። ጤና ይስጥልኝ አድማጮች አንደምን ሰነበታችሁ በእለቱ ዝግጅታችን እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ስር ወድቃ የነበረችዉና የዛሬ ሁለት ሳምንት

ግድም በሶርያዉ ፕሬዚዳንት አሳድ መንግሥት ወታደሮች ቁጥጥር ሥር መልሳ የገባችዉን የሶርያ ታሪካዊ ከተማ ፓልሚራን አስመልክቶ ከፈረንሳዊትዋ የሶርያ ጥንታዊ ቅርስ ጥናት ምሁር ጋር የተደረገን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል ።

በተመ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO» በዓለም ቅርስነት መዝገብ የሰፈረችዉ የሶርያዋ ጥንታዊ ታሪካዊ ከተማ «ፓልሚራ» በሶርያዉ ፕሬዚዳንት አሳድ ወታደሮች እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራዉ አሸባሪ እጅ ካስለቀቁና አካባቢዉን ከተቆጣጠሩ ሁለት ሳምንት ግድም ሊሆናቸዉ ነዉ።

የሶርያዉ ታሪካዊና ጥንታዊ አካባቢ በፕሬዚዳንት አሳድ ወታደሮች ቁጥጥር እንደገባ በተለይ የታሪክና የጥንታዊ ቅርስ ጥናት ጥበቃ ምሁራን ደስታቸዉን ገልፀዋል። ፈረንሳዊትዋ የታሪክ ተመራማሪ አኒ ሳርትር ፎሪያ በተለይ በሶርያ ጥንታዊ ቅርሶችና ታሪካዊ ቦታዎች ላይ ከ 40 ዓመታት በላይ ጥናት አድርገዋል። እጅግ ታሪካዊና ጥንታዊ ስለሆነችዋ ስለ ሶርያዋ የበረሃዋ እንቁ ስለፓልሚራ በርካታ መጽሐፍትን ጽፈዋል። ፈረንሳዊትዋ የሶርያ ቅርስ ጥናት ምሁር በሶርያ ስለሚገኙት ጥንታዊ ቅርሶች ለመንግሥታቱ ድርጅት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«UNESCO» በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ከሚያደርጉት ምሁራን ቡድን መካከልም አንዷ ናቸዉ።

የሶርያዋ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ፓልሚራ በፕሬዚዳንት ባሽር አልአሳድ ወታደሮች ከ አሸባሪዉ ቡድን ከ«Is» እጅ ነፃ ከወጣች በኋላ በምን ሁኔታ ላይ ትገኝ ይሆን? ፤ አኒ ሳርትር ፎሪያ

« ባለፉት ሁለት ቀናቶች በሶርያ ከማዉቃቸዉ የከርሰ ምድር ጥናት ባለሞያዎች በርካታ ፎቶግራፎች ደርሰዉኛል። በእነዚህ ፎቶዎች ላይ እንደሚታየዉ ከሆነ የበሽር ኧል-አሳድ ወታደሮች ታሪካዊ ቅርሶች ስብርባሪ ያሉባቸዉን ቦታዎችን ሲመትሩና ሲለኩ ይታያል። ዛሬ የደረሰኝ ፎቶ ደግሞ ባል የተሰኘዉ ጥንታዊ ቤተ-መቅደስ የዉስጠኛዉ ክፍልን የሚያሳይ ነዉ። በፊት ይህ ቦታ ላይ ቦንብ አለ ተብሎ ስለሚፈራ ከዉስጥ በኩል ፎቶ ማንሳት አይቻልም ነበር»

የሶርያዋ ታሪካዊትዋና ጥንታዊ ከተማ ፓልሚራ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን እጅ ነፃ በመሆንዋ እፎይታን አግንቻለሁ፤ በሌላ በኩል ግን ይህ ተለቀች የተባለዉ ዜና ሙሉ በሙሉ እፎይታ እንዳልሆነ የተናገሩት የሶርያ ጥንታዊ ቅርስ ጥናት ምሁርዋ አኒ ሳርትር ፎሪያ በመቀጠል።

« እፎይታን አግንቻለሁ አላገኘሁምም። በርግጥ ቦታዉ ከጀሃዲስቶቹ ነፃ በመሆኑ እፎይታን አግንቻለሁ። በዓለም የቅርጽ መዝገብ ላይ ሰፍሮ የነበረዉ ታሪካዊዉ ፓልሚራ ከተማ ላይ ከፍተኛ ጥፋትን አድርሰዋል። ግን እነሱ ከቦታዉ ላይ ስለለቀቁም ይህን ያህል ቀለለኝ ማለትም አልችልም። በሽር ኧል-አሳድ ፓልሚራ ከተማ ላይ ምን ያህል ከፍተኛ ጥፋት ማድረሳቸዉ መቼም ከእምሮዬ የሚጠፋ አይደለም። በሶርያ ከጎርጎረሳዊዉ 2012 ዓ,ም እስከ 2015 ዓ,ም ድረሰ በነበረዉ አብዮት የሶርያ ጦር ሠራዊት የፓልሚራን ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማን ተቆጣጥሮ ሳለ ከፍተኛ ጥፋትን አድርሶአል። ሠራዊቱ ሮኬቶችና ቦንቦችን በዚሁ ጥንታዊና ታሪካዊ ቦታ ላይ አፈንድድቶ የተለያዩ ኃዉልቶችን ምሶሶዎችን አፈራርሶአል። ከዚህ በተጨማሪ ጦር ሠራዊቱ አካባቢዉ ላይ የሚገኘዉን ጥንታዊ መካነ መቃብሮች በመሰባበርና በመስረቅ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ አዉጥቶ ሸጦአል። በዚህም ምክንያት ፓልሚራ አሁንም በአሳድ እጅ ዉስጥ እስካለች ድረስ አካባቢዉ አሁንም ይወድማል፤ በድጋሚም በሌቦች ይበዘበዛል የሚል ፍራቻ ነዉ አለኝ።»

ፓልሚራ ከአሸባሪዉ እጅ ነፃ እንደተለቀቀች የሶርያ የጥንታዊ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መሥርያ ቤት ዋና ተጠሪ ማሙን ኧብዱል ካሪም እንደገለፁት፤ ፕሬዚዳንት ባሽር ኧል-አሳድ ፓልሚራን መንከባከብ እንደሚፈልጉ እንዲሁም ይህን የዓለም የታሪካዊ ቅርስ በመንግሥታቱ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«UNESCO» በመታገዝ ዳግም ለመገንባት እንደሚሹ ነዉ ያመላከቱት። ፓልሚራ ነፃ ወጣች ማለት በሶርያ የጀመረዉ የርስ በርስ ጦርነት አቆመ ማለት አይደለም ያሉት አኒ ሳርትር ፎሪያ በመቀጠል፤

«የብዙኃን መገናኛዎች ፓልሚራ ከተማ ከአሸባሪዉ ቡድን እጅ ነፃ የመዉጣቷን ዜና በደስታ መዘገባቸዉን አዉቃለሁ። ግን ፓልሚራ ዳግም በበፈላጭ ቆራጩ የአሳድ መንግሥት እጅ ሥር ገባች ማለት በሶርያ የሚታየዉ ጦርነት ጨርሶ አበቃ ማለት አይደለም። በዚህም ምክንያት ፓልሚራን በተመለከተ ያለኝ ግምት ሁሉ ጥሩ ነዉ ማለት አይቻልም። በመጀመርያ ደረጃ ሠላም መስፈን አለበት፤ ፓልሚራን መልሶ ለመገንባትና ወደ ቀድሞ አቋሟ ለመመስ ከመሞከሩ በፊት አካባቢዉ ደሕንነቱ የተረጋገጠ መሆን ይኖርበታል። ፓልሚራ ታሪካዊ ቦታ ላይ ዳግም መጠገን የሚችሉት ነገሮች ሁሉ እንዲጠገኑ እፈልጋለሁ። በፎቶ ላይ እንደተመለከትኩት የድል ምሶሶ ላይ ያለዉ አግዳሚ ግንብ ሊጠገን ይችላል። ምክንያቱም ተመቶ ጉዳት ደረሰበት እንጂ በቦንብ በአየር ላይ አልነጎደም። ባል የተሰኘዉ ቤተ-መቅደስ ግን ሊጠገንም ሊታደስም አይችልም የሚል ጥርጣሪ ግን አለኝ። ምክንያቱም ከዚህ ጥንታዊ ቤተ- መቅደስ የተረፉት ትናንሽ ስብርባሪ ድንጋዮች ብቻ ናቸዉ። »

እንደኔ እንደኔ ፓልሚራ ሙሉ በሙሉ ዳግም ባይታደስ ልባዊ ፍላጎቴ መሆኑን በግልፅነት እናገራለሁ። ያሉት አኒ ሳርትር ፎሪያ በመቀጠል ፤

«ፓልሚራ ሙሉ በሙሉ ዳግም ባይታደስ ልባዊ ፍላጎቴ መሆኑን በግልፅነት እናገራለሁ። ምክንያቱም ፓልሚራ የሚገኘዉ ጥንታዊ ትያትር ቤት እድሳት የተደረገለት በጣም በቅርቡ ነበር። ትያትር ቤቱ የታደሰበት አዳዲስ ድንጋይ ሁሉ ሳይቀር ይታያል። ቤቱ የጥንታዊነት ታሪኩ ሁሉ ጠፍቶአል። አሁን ደግሞ ባል የተሰኘዉን ጥንታዊ ቤተ-መቅደስ ልክ እንደ ትያትር ቤቱ ሁሉ ቢታደስ ታሪካዊነቱ ጥንታዊነቱ ጠፍቶ በተረት ተረት ላይ የሚሰማዉ አይነት የአሻንጉሊት አይነት ቤት ይሆናል። ይህን አይነቱን ሁኔታ እንዳይከሰት ስል ነዉ በአዲስ እንዳይታደስ የምፈልገዉ።»

ለአስር ወራቶች እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ተይዛ የነበረችዉ የሶርያዋ ታሪካዊ ከተማ በፓልሚራ ከአሸባሪዉ ቡድን ነፃ ከሆነች በኋላ ያልወደመ ታሪካዊ ቅርስ ይገኛል ቡሉ የገመተ ማንም አልነበረም። ታሪካዊ ቅርሶቹ በሚገኙበት አካባቢ የምድር መንቀጥቀጥ እንደደረሰበት የተሰባበረና ጨርሶ የወደመ ፍርድራሽና ስብርባሪ የቀረበት ቦታ ተብሎ ነበር ዓለም ያመነዉ። የፕሬዚዳንት በሽር ኧል-አሳድ ወታደሮች ፓልሚራን አስለቅቀዉ ከያዙ በኋላ እንደታየዉ ግን በታሪካዊትዋና ጥንታዊትዋ ፓልሚራ ከተማ የደረሰዉ ጉዳት 20 % ያህል መሆኑ ነዉ የታየዉ። ምናልባት « IS» ፓልሚራ ላትመለስ ወድማለች የሚለዉን መረጃ ያስፋፋዉ ዓለም እንዲያምነዉ ያሰራጨዉ ፕሮፖጋንዳ ይሆን? አኒ ሳርትር ፎሪያ እንደሚሉት አሸባሪ ቡድኑ ፓልሚራ ዉስጥ እጅግ ግዙፍና ዋንኛ ቅርሶችን ነዉ ያወደመዉ።

«በፓልሚራ 20% የሚሆነዉ ታሪካዊ ቅርስ ብቻ ነዉ የሚለዉ መረጃ ከወደመዉ ነገር ጋር ሲነጻጸር በእዉነቱ ጥቂት ነዉ። አሸባሪዎቹም ቦታዉ ላይ ይገኙ የነበሩትንና ዋና የሚባሉትን የዓለም ቅርሶች ነዉ ያወደሙት። ሁለቱ ጥንታዊ

ቤተ-መቅደሶች ማለት ባል ቤተ- መቅደስና ባልሻሚን ቤተ መቅደስ በፓልሚራ ጥንታዊና እጅግ ዉብ የእጅ ሥራ ዉጤቶች ናቸዉ። ከዚህ ሌላ ሰባት ጥንታዊ የመቃብር ማማዎችና በኃዉልቶች ላይ የቆመ ዛብያ ወድሞአል። በርካታ የኃዉልት ላይ ገጽታዎች ተሰርቀዋል። እነዚህ ጥንታዊ ቅርሶች በፕሬዚዳንት አሳድ ወታደሮች ተሰረቁ አልያም በአሸባሪዉ ቡድን በ «IS» ተሰረቁ ፤ የከርሰ ምድር ምሁራኑ፤ የታሪክ ተመራማሪዎቹ፤ አልያም ሌሎች በምርምር ላይ የነበሩት ምሁራን በቀጣይ ለምርምር የሚፈልጉት ቁስና አካባቢ ነዉ የተጎዳዉ። ታሪክ ነዉ የጠፋዉ። ስለዚህ 20% በመቶ ስንል ማገናጠብ ያለብን፤ ዋንኛና አስፈላጊ ተብሎ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበዉ የታሪክ ማህደር 20 % ድምጥማጡ ጠፍቶአል ማለት ነዉ። »

ከሰባት ወራት በላይ በአሸባሪዉ ቡድን በ«IS» ተይዛ የነበረችዉ የሶርያዋ ጥንታዊትና ታሪካዊት ከተማ ፓልሚራ ምን መደረግ አለበት። ?

« ከሚታደስ መልሶ ቢገነባ እመርጣለሁ። ቢሆንም በፓልሚራ ምንም እንዳልደረሰ ሁሉ ሁሉም ነገር መቀበሉን አልደግፍም። ፓልሚራ የደረሰዉን ዉድመት የሚያሳይ አንዱን ክፍል ለታሪክ ምስክርነት እንደ መታሰብያ መቅረት ይኖርበታል። »

እራሱን እስላማዊ መ ንግሥት ብሎ የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ፓልሚራን አወደምኩ ማለቱ ፕሮፖጋንዳ ነበር ማለት ይሆን?

« አዎ በርግጥ ፕሮፖጋንዳ ነበር። በ« IS» አመለካከት ፓልሚራ በሁለት ዓይነት መንገድ መዉደም እንደነበረባት ማሰቡን ግን በቀላሉ ማረጋገጥ አይቻልም። በመጀመርያ ፓልሚራ ለምዕራባዉያን አንድ ትልቅ ቅርስ መሆንዋ አንዱ ነዉ። ግልጽ ሊሆን የሚገባዉ ነገር «Is» ይህን የእስላምና ታሪክን የሚመሰክሩና የሚያሳዩ እንደ መስጊድና የእስላም መቃብሮችን ማዉደሙ ነዉ። በሁለተኛ ደረጃ ፓልሚራ የሶርያ ማንነት ምልክትም በመሆንዋ ነዉ። ለምሳሌ በሶርያ የፖስታ ቴምብሮች እንዲሁም የመገበያያ ገንዘብ ላይ ሁሉ የፓልሚራ ጥንታዊ ቅርስ ምስል ተቀርሶ ይገኛል።»

የታሪክ ተመራማሪዎ የፓልሚራን ነፃ መዉጣትን እንዴት ይመለከቱታል? የፓልሚራ ነጻ መዉጣት ፕሬዚዳንት በሽር አልኧሳድ የግል ጥቅማቸዉን ያስጠብቁበት ይሆን ይላሉ?

«በጎርጎረሳዉያኑ 2015 ግንቦት ወር ፕሬዚዳንት በሽር አልኧሳድ ፓልሚራ እያወቁ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ለሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን መልቀቃቸዉ የፖለቲካ መጠቀምያ ዒላማ አድርገዉ ነበር ። ስትራቴጂያቸዉ የነበረዉ «IS» ፓልሚራን ሲቆጣጠር ምዕራባዉያን ይህን የዓለም ቅርስ ቦታ ለማስለቀቅ ለርዳታ ይመጣሉ ብለዉ በማሰብ ነበር። እናም በመጀመርያ ያሰቡት አልተሳካላቸዉም ፤ ምክንያቱም ምዕራባዉያኑ እንደ አሳድ የመሰለዉን ፈላጭ ቆራጭ መርዳት ባለመፈለጋቸዉ ነበር። የሶርያ አየር ኃይል ተቆጣጣሪዎች የ«IS» ሠራዎቶች በረሃዉን አቋርጠዉ ወደ ፓልሚራ እየተጠጉ መሆናቸዉንም በትክክል አይተዉም ነበር። ጽንፈኞቹን ለመከላከልም የወሰዱት ምንም ዓይነት ርምጃ አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ ምዕራባዉያን ፓልሚራን ለመከላከል ይመጣሉ ብለዉ በማሰብ ነበር። ጀሃዲስቶቹ ወደ ፓልሚራ እንዳዳይገቡና ታሪካዊዉን ቦታ እንዳያወድሙ ከመከላከል ይልቅ ቦንብና ሮኬቶች ይዘንቡ የነበሩት አሌፖ ከተማ ላይ ነበር። አሁንም የሚታየዉ የዚሁ ዓይነት ተመሳሳይ ሁኔታ ነዉ። ፕሬዚዳንት አሳድ ሩስያንና ሄዝቦላን አስከትለዉ ፓልሚራን ከ «IS» ነፃ አድርገዉ፤ ድል እንደቀናቸዉ ደግሰዋል። አሳድ በቀጣይ ምዕራባዉያን ለሰላም ድርድር ይቀበሉኛል ብለዉ ተስፋን ሰንቀዋል። ይህ ደግሞ የፖለቲካ ጨዋታ ነዉ።» ፈረንሳይትዋ የሶርያ ቅርስ ጥናት ባለሞያ በመቀጠል

« አሳድ ገና ለመናገር አ ሲሉ ነዉ መዋሸት የሚጀምሩት። የሶርያዉያንን ስልት ከ40 ዓመታት በላይ አዉቀዋለሁ። በ1971 ዓ,ም ወደ ሶርያ እንደመጣሁ ከፕሬዚዳንት ባሽር ኧልኧሳድ አባት ጋር ተገናኝቼ ነበር። ፕሬዚዳንት አሳድ የአባታቸዉን በትረ ስልጣን ሲረከቡ ቦታዉ ላይ ሆኜ ለመከታተል እድሉ አጋጥሞኛል። በሶርያ በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ,ም አብዮት ሲጀምር ቦታዉ ላይ ነበርኩ። ባሽር አልኧሳድን አጭበርባሪ ሆነዉ ነዉ ያገኘሁዋቸሁ። በሶርያ ማፍያና አንባገንን መንግሥት ነዉ ያለን።»

የአሳድ አንድኛና ዋንኛ ዓላማ ሶርያ እሳቸዉ እንደሚፈልጓት በዚሁ እንድትቀጥል በስልጣን መቆየት ነዉ። ሶርያ የራሳቸዉ የግል ሃብታቸዉ አድርገዉ ነዉ የሚወቆጥሩዋት። በዚህም ምክንያት የተፈለገዉን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ። 300 ሺህ ሰዎችን መጨፍጨፍ ማለት ለሳቸዉ ምንም ማለት አይደለም፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶርያዉያን ከቤት ከሃገር ቀያቸዉ እንዲፈናቀሉ ዳርገዋል፤ በርካቶች በእስር ቤቶች በእንግልት ተገድለዋል ሲሉም አኒ ሳርትር ፎሪያ ገልፀዋል።

ከተደራዳሪዎቹ ከአሳድ ጋር ለድርድር በጠረቤዛ ዙርያ መቀመጥ የሚፈልጉ ከሆነ ትልቅ የመደራደርያ ነጥብን ይዘዉ መቅረብ ይኖርባቸዋል ምክንያቱም ለድርድሩ የሚቀመጡት ከሰይጣን ጋር በመሆኑ ነዉ ሲሉም አኒ ሳርትር ፎሪያ አስተያየታቸዉን አክለዋል። ግን ፓልሚራ አሁንም መጠቀምያ ሆና ትቆይ ይሆን ?

« አዎ አሳድ በፓልሚራ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። እራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ከፓልሚራ በመዉጣቱ ደስተኛ ነኝ። ነገር ግን «IS» ከፓልሚራ በመዉጣቱ አሳድን አላመሰግንም። »

የሶርያ ጦር በፓልሚራ የአርባ ሰዎች አስከሬን የያዘ የጅምላ መቃብር ማግኘቱ ተዘግቦአል። አሸባሪዉ ቡድን «አንገታቸውን ተቀልተው አሊያም በጥይት ጭንቅላታቸውን ተመትተው የተገደሉ ናቸው።» ያሉት የጦር መኮንኑ አስከሬኖቹ ወደ ግዛቲቱ ዋና ከተማ ሆምስ መወሰዳቸውን ተናግረዋል። መቀመጫውን በለንደን ያደረገው የሶርያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ፤ ጽንፈኛው ታጣቂ ቡድን በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሎ ከፓልሜራ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኙ አካባቢዎች ቀብሯል ሲል አስታውቋል። ፓልሚራ በቀጣይ የዓለም የቅርስ ማኅደር ሆና የዓለም ታሪክ ተመራማሪዎችን ታሰባስብ ይሆን? ይህ በጊዜዉ የሚታይ ይሆናል።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic