የበረራ አገልግሎትና አከራካሪው ገላ-ፈታሽ መሣሪያ፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 06.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የበረራ አገልግሎትና አከራካሪው ገላ-ፈታሽ መሣሪያ፣

ታኅሳስ 16 ቀን 2002 ዓ ,ም፣ በጎርጎሪዮሳውያኑ የገና በዓል፣ ከአመስተርዳም ፣ ኔደርላንድ ፣ ወደ ዲትሮይት ፣ ዩናይትድ እስቴትስ ይበር በነበረ የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን ውስጥ፣ አንድ ናይጀሪያዊ ወጣት፣

default

በድብቅ ባስገባው ፈንጂ ቅመምና ፈሳሻ አጥፍቶ ለመጥፋት ሞክሮ ፣ ይኸው ሙከራው በተሣፋሪዎች መረባረብ ከከሸፈበት ወዲህ፣ ባለፉት 12 ቀናት በመገናኛ ብዙኀን በሰፊው የሚነሣ -የሚጣል ጉዳይ፣ በረራን እንዴት ከአጥፍቶ ጠፊዎች አደጋ መከላከል ይቻላል? የሚለው ሲሆን ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚወሳው፣ አዲሱ የአካል መፈታሻ መሣሪያ ሆኗል። መላ አካል ፈታሽ(Full Body Scanner) ወይም (Nude Scanner) የተሰኘው መሣሪያ በህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላኖች ላይ የሚቃጣ አደጋን የቱን ያህል መግታት ይችላል? ጥቅሙና ጉዳቱ እምን ላይ ነው? በአርግጥ ምንድን ነው ለይቶ ማሳየት የሚችለው?

ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ!በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፣ በረራን ከሰው ሠራሽ አደጋ ለመከላከል እንደ ዋና መፍትኄ ታይቶ በሚመከርበት ገላ ፈታሽ መሣሪያ ላይ እናተኩራለን አብታችሁን ቆዩ።

ባለንበት ዘመን አንዳንድ አንገባጋቢ ፈተናዎች ሲያጋጥሙም ሆነ ከማጋጠማቸው በፊት ሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ መላ የሚያገኙላቸው እስከሆነ ድረስ፣ ጠበብት ማሰብ-ማሰላሰል ብቻ ሳይሆን ፣ አብነቱን ለማግኘት አስቀድመው በአብያተ-ሙከራ በምርምር ከመጠመድ እንደማይቦዝኑ የታወቀ ነው። መንገደኞች ካንድ ቦታ ወይም አገር ወደሌላው ለመጓዝ አኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ሲደርሱ መላ አካል የሚፈትሸው ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ፣ በአርግጥ ምን -ምን፣ መመርመር ይችላል? በጀርመን ሀገር የኃይለኛ ሞገድ ነክ ፊዚክስ የምርምር ተቋም ባልደረባ ሔልሙት ኤሰን--

«አካላትን የሚፈትሸው መሣሪያ በመሠረቱ የብረታ-ብረት ዓይነቶችን ፣ የሸክላና የመፈንዳት ባህርይ ያላቸውን ቅመማት ነው፣ ከልብስ ሥርከአካል ቆዳ ላይ ተደብቀው እንደሁ የሚያሳየው። በአካል ውስጥ የሚገኝ ካለ ግን መመልከት አይቻልም። ማየት የሚቻለው በአካልና በልብስ መካከል የተደበቀውን ነው።»

መስከረም 1 ቀን 1994 ዓ ም፣ አሸባሪዎች፣ በኒው ዮርክ ፣ የዓለም የንግድ ማዕከል የሆኑትን ሁለት ሰማይ ጠቀስ መንትያ ህንጻዎች በሁለት የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላኖች በመደርመስ የ 3,000 ያህል ሰው ህይወት ካጠፉ ወዲህ፣ የበረራ ጸጥታ አጠባበቅን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ ቢቀጥልም፣ ጦር መሣሪያና ፈንጂ ቅመማት ደብቀው አኤሮፕላን ውስጥ ለማስገባት የሚጥሩ አሸባሪዎችን ተግባር ፈጽሞ መግታት እንዳልተቻለ ያለፈው ሰሞን ድርጊት ጭምር በቂ ምሥክር ነው። ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ፣ መላ-አካል ፈታሹ መሣሪያ፣ በጀርመን ሀገርም ዐቢይ የመወያያ ርእስ ሆኗል። ይኸው አከራካሪ ሥነ-ቴክኒክ ፣ ከጤንነትና ሰብአዊ ክብር ጋር ተያያዞም ጥያቄዎች ቀርበውበታል። የጀርመን የሀገር አስተዳደር ሚንስትር፣ ቶማስ ደ መዚር፣ ገላ-ፈታሹ መሣሪያ፣ በአኤሮፓላን ማረፊያ ጣቢያዎች ሥራ ላይ እንዲውል አዘዋል። ያም ሆኖ፣ ሦስት ቅድመ-ግዴታዎች መሟላት እንዳለባቸው ደ መዚር አያያዘው ነው የገለጡት። --

«መሣሪያዎቹ፣ ከአካለት ውጭ የተደበቀ ነገርን ፣ፕላስቲክን ጭምር ለይተው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ሁለተኛ ለጤና ጠንቅ እንደማይሆኑ መታወቅ አለበት። እንዲሁም ሦስተኛ ፣ ገመናን የሚያጋልጡ መሆን የለባቸውም። የግለሰቦች ክብርን መብት መጠበቅ አለበት»

እነዚህ ሚንስትሩ የጠቀሷቸው 3 ጉዳዮች ተሟልተዋል?ወደፊትስ ፣ በትክክል ተፈጻሚዎች ይሆናሉ ወይ? ከርክር አስነስቷል።አሁን በመጣመር የአስተዳደር አባል የሆነው ነጻ ዴሞክራቱ ፓርቲ (FDP) በተቃውሞ ጎራ ተሰልፎ በነበረበት ወቅት ፣ ገላ ፈታሹ መሣሪያ ፣ ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርድና ለጤንነትም የሚያሳስብ ነው በማለት እንደማይቀበለው ነበረ ሲገልጽ የነበረው። አምና በመጸው እርቃን ስለሚያሳየው ፈታሽ መሣሪያ በፓርላማ ክርክር እንደተነሣ፣ FDP መቃወሙ አይዘነጋም። አሁን ከክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና ከክርስቲያን ሶሺያል ኅብረት ጋር በመጣመር የሥልጣን ተጋሪ የሆነው ነጻ ዴሞክራት ፓርቲ ፣ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጊዶ ቬስተርቨለ እንደተናገሩት የአቋም ለውጥ ሳያደርግ አልቀረም። ቬስተርቨለ ስለ አከራካሪው ሥነ-ቴክኒክ፣ ሲነገሩ፣ «ለደኅንነት ሲባል የሚከናወን ፍተሻ» የሚል ዘይቤ አሰምተዋል ። --

«አሁን ገላ ፈታሽ መሣሪያ አቅርበናል። ሰዎች በዚህ መሳሪኢ ዕርቃናቸውን አይታዩም። ይሁን እንጂ፣ ጦር መሣሪያና ፈንጂ ቅመማት በተሣካ ሁኔታ ይመረመሩበታል። እንደሚመስለኝ ይህ አንድ የሥነ-ቴክኒክ እመርታ ነው። እናም አዲስ የፍተሻ መሣሪያ ማቅረብ ተፈላጊ ሆኗል።»

የነጻ ዴሞክራቱ ፓርቲ አባል የሆኑት የፍትኅና ፍርድ ሚንስትርም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሠነዘሩት። ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ ገላ ፈታሹ መሣሪያ ሥራ ላይ የሚውልበት ሁኔታ የፖለቲካ እክል የሚገጥመው አልመሰለም፤ ከተቃውሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከግለሰቦች የመረጃ ሰነድ ጠባቂ መ/ቤት የሚቀርበው አንጻራዊ አቋም በቂ ድጋፍ የለውምና።

ያም ሆኖ ፣ ጀርመን፣ የሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ቃል አቀባይ እሽቴፋን ፓሪስ እንዳሉት፣ በብዙኅኑ የአውሮው ኅብረት አባል ሀገራት የድምፅ ብልጫ የሚወሰን ጉዳይ እንጂ፣ ብሔራዊ መንግሥታት በተናጠል ተግባራዊ የሚያደርጉት አይደለም። እርግጥ በአመስተርዳም ተጨባጭ ፈተና ያገጠማት ኔደርላንድ፣ የራሷን የፍተሻ እርምጃ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች። በጀርመን ሀገር፣ የገላ መፈተሻው መሣሪያ እንዳከረከረ ሲሆን፣ አስተማማኝነቱ 30 ከመቶ ያህል አጠያያቂ ስለመሆኑ፣ የፖሊሶች ማኅበር ሊቀ-መንበር ኮንራድ ፍራይበርግ አልደበቁም።

«የሲቭል ልብስ የለበሱ ፖሊሶች፣ ጦር መሣሪያና የጦር መሣሪያ ክፍሎችን በመያዝ የተከለከሉ ቦታዎችን አልፈው ለመግባት ችለዋል። እናም ብዙ ስህተቶች ይሠራሉ። ይህን ደግሞ ደጋግመን ከማሳወቅ የቦዘንንበት ጊዜ አልነበረም። በአንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደማይዘለቅ የአኤሮፕላን ጣቢያ አስተዳዳሪዎችን ነግረናቸዋል። እነርሱ፣ የጸጥታ ግብር ከመንገደኞች እንደሚሰበስቡም የታወቀ ነው። ይህም ለጸጥታ አጠባበቅ ወጪ መክፈል ይኖርባቸዋል ማለት ሲሆን፣ እነርሱ ግን ለፀጥታው የሚያስፈልገውን ሳይከፍሉ ገንዘብ መቆጠቡን ነው የተያያዙት።»

እርግጥ ነው፣ ገላ ፈታሹ መሣሪያ፣ መሠረታዊውን የፀጥታ ችግር ያስወግዳል ማለት ዘበት መሆኑን የሚናገሩ ተከራካሪዎች ጥቂቶች አይደሉም። የሽለስቪኽ ሖልሽታይን ፌደራል ክፍለ-ሀገር፣ የግለሰቦች የመረጃ ሰነድ አጠባበቅ ጉዳይ ማእከል ሥራ አስኪያጅ ፣ Thilo Weichert እንደሚሉት ፣ እጅግ አደገኛ የሆኑ ፈንጂ ቅመማትን ሁሉ፣ በዚሁ የፍተሻ መሣሪያ አማካኝነት ለይቶ ማወቅ የሚቻል አይደለም። ወጀለኞችን የሚከታተለው የጀርመን ፌደራዊ መሥሪያ ቤት ሊቀመንበር ክላውስ ያንሰን «ፈንጂ ቅመም በተለይ በአካል ውስጥ ከተደበቀ በገላ ፈታሹ መሣሪያ አማካኝነት ማወቅ አይቻልም። ለዚህ በቂ ምሳሌ፣ ሱስ አስያዥ ቅመማትን በአካላቸው ውስጥ እየደበቁ ሳይነቃባቸው ከቦታ ቦታ ካገር አገር የሚያመላልሱ ሰዎች ናቸው »፣ ብለዋል ።

በመሆኑም፣ የጀርመን የምርምር ጉዳይ ሚንስትር ወ/ሮ አኔተ ሻባን ፣ እስከመጪው የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ሞቃት ወራት ድረስ ፣ የተሻሻሉ ገላ ፈታሽ መሣሪያዎች ተሠርተው እንደሚቀርቡ ተስፋ ያላቸው መሆኑን ገልጠዋል።

በጀርመን ሀገር ፣ የሚንስትርዋን ተስፋ እውን ያደርጋሉ ተብለው ከሚገመቱት የምርምር ተቋማት መካከል አንዱ ፍራውንሆፈር የተሰኘው ስመ-ጥር ድርጅት ነው።

ፍራውንሆፈር ተቋም፣ ወደፊት የፈንጂነት ባኅርያት ያላቸውን ሰው-ሰራሽም ሆኑ የተፈጥሮ ቅመማት አሽትቶ መለየት የሚችል የኤልክትሮኒክ አፍንጫ ያለው መሣሪያ ለችግሩ አብነት ማስገኘቱ አይቀርም ይለናል። ለምሳሌ ያህል በዛ ያሉ ሰዎች፣ በአኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ለበረራ ወደተዘጋጁ አኤሮፕላኖች አልፈው ከመሣፈራቸው በፊት በጠባብ ቦታ ተከታትለው በሚያልፉበት ጊዜ፣ ከብዙዎቹ ተሣፋሪዎች መካከል ሁለት አሸባሪዎች በጃኬታቸው የተለያዩ ፈንጂ ቅመማት ደብቀው ያልፋሉ እንበል! ተሣፋሪዎቹ፣ በተቆጣጣሪ ካሜራዎች ብቻ አይደለም የሚፈተሹት። በመተላለፊያው በር በድብቅ የተቀመጡ ልሺ የኤሌክትሮኒክ መሣሪኢዎችም፣ የሠለጠነ ውሻ አነፍንፎ እንደሚጠቁመው ሁሉ እንዚሁ መሣሪያዎች፣ የተጠቀሱትን ቅመማት ደብቆ የያዘ ሰው ካለ፣ ሲያልፍ የማስጠንቀቂያ ደወል ያሰማሉ። ተቆጣጣሪው ሰው በመቆጣጠሪያው የኮምፒዩተር መስኮት ሰዎቹን ይመለከታል። አደገኛውን የፈንጂ ቅመም የያዘው የትኛው ሰው እንደሆነ በሁለተኛው ዙር ፍተሻ ለይቶ መጠቆም ይችላል። ይህ በቤት ሙከራ የተሣካ ውጤት የተመዘገበበት ፍተሻ መሆኑን በ ቫኽትበርግ ፣ የፍራውንሆፈር የምርምር ተቋም አረጋግጧል ነው የተባለው። የፍራውንሆፈር የመገናኛና የመረጃ ማጣሪያ ክፍል ጠበብት፣ አስተማማኝ ያሉትን የፀጥታ መጠበቂያ ሥርዓት፣ በአንግሊዝኛው አገላለጽ፣ Hazardous Material Localization and Person Tracking በአህጽሮት (HAMLeT) ብለውታል። የዚሁ ምርምር ኀላፊ ዶ/ር ቮልፍጋenge ኮህ፣ እንደገለጹት የረቀቀው መሣሪያ፣ የፈንጂ ባህርያት ያሏቸውን ቅመማት ተከታትሎ ይጠቁማል። ይኸው የኤሌክትሮኒክ አፍንጫ፣ የቅመማቱን ንጥር ሞገዳዊ ነጸብራቅም ሆነ እንቅሥቃሴ ከማሳየቱም ሌላ፣ የተቀባበረ ተግባር የሚያከናውነው የኤሌክትሮኒክ ፈታሽ መሣሪያ፣ ፈንጂ ቅመም የያዘውን ሰው እንቅሥቃሤም ይጠቁማል። ስለሆነም፣ የ 2ኛው ክፍል የማጣሪያ ተግባር ወሳኝነት ያለው ነው፣ ማለት ነው። ልዩ ጨረር ባለበት በገላ ፈታሹ መሳሪያ አማካኝነት የተጠርጣሪውን ሰው እንቅሥቃሴ፣ ጊዜውንና የሚገኝበትን ቦታ መጠቆም ይቻላል። በ«ሃምሌት» የኤሌክትሮኒክ ተቆጣጣሪ መሣሪያ የሰዎችን እንቅሥቃሤና የተያዘን አደገኛ ፈንጂ ቅመም በትክክል ለይቶ ማሳየት ይችላል። በዚሁ ልዩ የፍተሻ መሣሪያ፣ የጀርመን መከላከያ ሚንስቴር ለሙከራ ያህል ባካሄደው ምርመራ፣ የተደበቁ ፈንጂ ቅመማትን ይዘው ለማለፍ የሞከሩ 5 ሰዊዎችን ለይቶ ለማወቅ መቻሉ ተነግሮአል።

በአሁኑ ጊዜ በዚሁ ዘርፍ ያተኮሩ የሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ጠበብት፣ መሣሪኢው የተሳሳተ መረጃ እንዳያቀርብ በይበልጥ ተሻሽሎ እንዲሠራ ጥረታቸውን መቀጠላቸው ነው የሚነገረው።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ