የበረሃ አንበጣ መንጋ የመፍጠር ባሕሪ  | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 28.10.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የበረሃ አንበጣ መንጋ የመፍጠር ባሕሪ 

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለከፋ የምግብ እጥረት የሚዳርግ የበረሃ አንበጣ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ይህንን ጉዳት እንዴት ማቆም ይቻላል? እነዚህ ተበታትነው የሚኖሩ ነብሳትስ ለምን ይሰባሰባሉ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:35

አንበጣዎቹ ስጋት የሚኾኑኑት መቼ ነው?

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለከፋ የምግብ እጥረት የሚዳርግ የበረሃ አንበጣ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።ይህንን ጉዳት እንዴት ማቆም ይቻላል? እነዚህ ተበታትነው የሚኖሩ ነብሳትስ ለምን ይሰባሰባሉ? የሚለውን ለመመለስ ተመራማሪዎች በቅርቡ በነብሳቱ ባህሪ ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር አድርገዋል።በዚህ ምርምርም ነብሳቱ መንጋ እንዲፈጥሩ የሚያደርግ የተለዬ ንጥረ ነገር መኖሩንና ይህ ንጥረ ነገር እነሱኑ መልሶ ለመዋጋት እንደሚያስችልም ፍንጭ ተገኝቷል። 

የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ውጤታማ ክትባት ወይም መድኃኒት በጉጉት የምትጠብቀው ዓለማችን በቅርቡ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በምስራቅ አፍሪቃ በመካከለኛው ምስራቅና በደቡብ ምዕራብ ኤዥያ ሀገራት ባለፉት 70 አመታት ያልታዬና ሚሊዮኖችን ለምግብ እጥረት የሚዳርግ ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።ኢትዮጵያም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ነች። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ የነብሳቱን ባህሪ ለመረዳትና ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ያግዛል በሚል ከወደ ቻይና የተደረገ አንድ ምርምር ለችግሩ መፍትሄ የሚጠቁም ይመስላል። «ኔቸር» በተባለው የሳይንስ መፅሄት በቅርቡ የወጣው ይህ ምርምር ተበታትነው የሚኖሩ አንበጣዎች እንዲሰባሰቡና መንጋ እንዲፈጥሩ ብሎም ሰብል እንዲያወድሙ የሚያደርግ በሳይንሳዊ መጠሪያው «4 ቪኒላኒሶል»የተባለ ንጥረ ነገር በውስጣቸው መኖሩን አመልክቷል።ይህ ንጥረ ነገር በጥሩ መዓዛው የሚለይ ሲሆን እነዚህን ነፍሳት ለማጥመድ እና የሚያስከትሉትን የሰብል ውድመት ለመከላከል ሊያገለግል እንደሚችልም ምርምሩ ጠቁሟል።ምርምሩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህርና የነብሳት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኢልማና ጌቱ እንደሚሉት ስለ ነብሳቱ ባህሪ ሲነሳ ሁለት ደረጃዎችን ማስተዋል ይቻላል። 

«በዋናነት አንበጣ ሁለት ደረጃዎች ነው ያሉት ።አንደኛው «ሶሊታሪ ፌዝ»ነው።ራሱን ችሎ አንድ በአንድ ተበታኖ ነው የሚበላው።ከጎረቤቱ ሌላ አንበጣ ሊኖር ይችላል ነገር ግን ለብቻው ነው የሚበላው።»ካሉ በኋላ ሁለተኛውና አደገኛው የሚሰባሰቡበትና መንጋ የሚፈጥሩበት ደረጃ መሆኑን አመልክተዋል።አያይዘውም «ዋና እንዲሰባሰቡ የሚያደርጋቸው ምክንያት ለየብቻ በሚበሉበት ጊዜ ምግብ ማለቁን ይገነዘባሉ። ስለዚህ ምግብ እያለቀብን ስለሆነ አንድ ላይ እንሰብሰብና ምግብ ፍለጋ እንሂድ ነው።ይሄ እንሰብሰብ የሚለው እንዴት ነው የሚከሰተው?»ይህ ትልቁ ጥያቄ ነው ብለዋል።።

በመጀመሪያው ማለትም ተበታትነው በሚኖሩበት ጊዜ አንበጣዎቹ ብዙም ጉዳት የማያደርሱና በቀላሉ መከላከል የሚቻል ሲሆን፤በሁለተኛውና መንጋ በሚፈጥሩበት ደረጃ ግን በሰብል ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት ለመንጋው መፈጠር ምክንያት የሆነውን ነገር መለየት የመጀመሪያው የተመራማሪዎች ስራ ነው።ይህንን በተመለከተ ሁለት ሳይንሳዊ መላ ምቶች መኖራቸውን ፕሮፌሰር ኢማና ይገልፃሉ።የመጀመሪያውንና በቅርቡ በጥናት የተረጋገጠውን በማስቀደም ይጀምራሉ። 

«መንጋው እንዴት ነው የሚፈጠረው በሚለው ሁለት መላ ምቶች አሉ።አንደኛው መላ ምት ምንድነው።በእርግጥ በጥናት ተረጋግጧል።በ«ሶሊታሪ ፌዝ» እያሉ ቁጥራቸው እየበረከተ ሲሄድ ይነካካሉ።ለምን እንደሚነካኩ እስካሁን ማብራሪያ የለም ግን ይነካካሉ።ሲነካኩ በኋላ እግራቸው ነው የሚነካኩት።የኋላ እግራቸው «ፊመር»የሚባል ነገር አለ።እዚያ ላይ በሚነካኩበት ጊዜ የባሰ ሌሎቹንም ይጠራል።በዚህ የሰውነት ንክኪ ይሰባሰቡና መንጋ ይፈጠራሉ።»ነው ያሉት ፕሮፌሰር ኢልማና። 

ለአንበጣ መንጋ መፈጠር ሁለተኛው መላ ምት ደግሞ በእንስሳቱ አካል ውስጥ በሚገኝ «አሚኖ አሲድ»አማካኝነት የሚፈጠረው «ሴራቶኒን» የተባለ ንጥረ ቅመም ነው ይላሉ። 
ፕሮፌሰር ኢልማና እንደሚሉት የነብሳቱ የ«ሴሮቲኒን» መጠን ከመሰባሰባቸው በፊት ዝቅተኛ ሲሆን መንጋ በሚፈጥሩበት ወቅት ግን ከፍተኛ ነው።ስለዚህ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ እንዳይነካኩ ማድረግና የዚህን ንጥረ ነገር መጠን በነበረበት ደረጃ እንዲቆይ ማድረግ አልያም መቀነስ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አንዱ ዘዴ ነው። 

በቻይና የሳይንስ አካዳሚና በሄቤይ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሰራው አዲሱ ጥናት በነዚህ ነፍሳት የሚመነጩ 35 ውህዶች ላይ ምርምር አድርጓል። ከነዚህም ውስጥ ስድስቱ በተለይም «4-ቪኒላንሶሊኒ» ወይም «4VA» የሚል ሳይንሳዊ መጠሪያዎች የተሰጡት ንጥረ ነገር ለአንበጣ መንጋ መፈጠር ዋና ምክንያት መሆኑን ለይቷል። ይህም ወደፊት ሊፈጠር የሚችል የአንበጣ መንጋን ለመተንበይና ቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችል በምርምሩ ተጠቁሟል።ከዚህ በተጨማሪ የዘረ መል ቅንብርን ተጠቅሞ ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገር በማምረትና ነብሳቱ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ብዙ ሳይራቡ በቀላሉ ማስወገድ እንደሚቻልም ተመራማሪዎቹ አመልክተዋል።

ይሁን እንጅ ጥናቱ ተጨማሪ ምርምርና የመስክ ላይ ተግባራዊ ሙከራን የሚጠይቅ ነው።እንደ ፕሮፌሰር ኢማና የዚህ አይነቶቹ ጥናቶች ፍንጭ የሚሰጡና ለሌላ ምርምር የሚጋብዙ በመሆናቸው፤ ይህንን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎችም የገንዘብ ድጋፍ ከተቸራቸው ውጤት የሚያመጡ ምርምሮችን ሊያደርጉና ችግሩን በዘላቂነት ሊፈቱ ይችላሉ። ይህ መሰሉ ምርምር ነፍሳቱ መንጋ እንዳይፈጥሩ በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ በመሆኑ ሰብሎችን ከጉዳት ለማዳን የሚደረግ የኬሚካል ርጭትን ያስቀራል።ይህም ብዝኀ-ህይወትን ለመታደግና ለኬሚካል የሚወጣውን ወጭም ይቀንሳል። 

ለጊዜው ግን በኢትዮጵያ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ የከፋ ጉዳት ሳያደርስና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሳይዛመት በኬሚካል ርጭትም ቢሆን ችግሩን መቋቋም ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን አስምረውበታል።ከዚያ በኋላም ቢሆን ነብሳቱ በየአካባቢው እንቁላል ጥለው ሊሆን ስለሚችል በየጊዜው ቅኝት በማድረግ መቆጣጠር ያስፈልጋል። ለዚህም ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ፕሮፌሰር ኢልማና ጌቱ አሳስበዋል። 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን። 

ፀሐይ ጫኔ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic