የበረሃዋ ብዕረኛ | ወጣቶች | DW | 23.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

     የበረሃዋ ብዕረኛ

መጻፍ ብሎም ማሳተም ይቅር እና ማንበብ እንኳን በዓረብ ሀገር ላለን ለብዙዎቻችን ሩቅ በሆነበት ፤ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሐን መድረኮች አጫጭር ሀሳቦችን ከመለዋወጥ እና ከማጋራት እምብዛም ባልዘለለው በዚህ ዘመን ከሳዑዲ ዓረቢያ የበረሀ ምድር ለኩሽና አገልጋይነት ከተሰማራች ኢትዮጵያዊ ወጣት የተገኘ የበረሃ ቴምር ነው የሄዋን ትንሳዔ፡፡

 በሰኔ ወር 2009 በሳዑዲ ዓረቢያ ርዕሰ መዲና ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ ለአዳራሹም ሆነ ለሳዑዲ ዓረቢያ ባልተለመደ መልኩ አንድ የአማርኛ ልብ ወለድ መጽሐፍ አስመረቀ፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ የሄዋን ትንሳዔ  የገጽ ብዛት 311 ህትመት ሪያድ ዓረቢያን ማተሚያ ቤት፡፡ ደራሲ ዳያን ዲንቃ፡፡

ዳያን ዲንቃ ኢታና ትባላለች በ1982 ሀምሌ ወር በመቀሌ ከተማ ነው የተወለደችው ፡፡ የስሟ ማሳረጊያ የሆኑትን አባቷን አቶ ዲንቃ ኢታናን ገና በጨቅላነቷ በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ በተከሰተበት ወቅት ከቤተሰቡ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት እንደ ተለየቻቸው ትስማ እንጂ  በህይወት ስለመኖራቸውም ሆነ ስለ ኑሮአቸው ምንም እውቀትም ሆነ ወቅታዊ መረጃ የላትም፡፡ አብዛኛው የልጅነት ህይወቷ የተቆራኘው ከእናቷ እና ከእናቷ እናት አያቷ ጋር ነበር፡፡ የእናቷ ንባብ ወዳድነት ከተንጸባረቀባቸው ነገሮች አንዱ የዳያን ስም አወጣጥ ነው ፡፡ አንባቢ እናቷ የውበት ወጥመድ የሚለው የዳንዔላ ስቲል መጽሀፍ ውስጥ እጅግ ጠንካራ ሴት ገጸ ባህሪ የሆነችውን ዳያን ስም ለልጇ ስም መጠሪያ አደረገችው፡፡ የገሀዱ ዓለም ዳያን ከስነ ጽሁፏ ዓለም ዳያን ምንን ተጋርታ ይሆን?

የልጅነት ህይወቷ በብዙ ንባብ እና በብዙ ዝምታ የተሞላ ነበር ፡፡ ዳያን እንደምትለው በብቸኝነቷ እና በዝምታዋ መሀል ብዙ ገጸባህርያትን እየቀረጸች በምናቧ ከነርሱ ጋር ስታዝን ስትደሰት ፣ ስታወራ እና ስታወጋ ሲያዳምጧትም ሆነ ስታዳምጣቸው ነበር ውሎዋ እና አዳሯ፡፡

ይህ የልጅነት የሀሳብ እና የምናብ ምጥቀቷ ወደ ስነጽሁፉ ዓለም እንድታዘነብል ምክንያት ሆኗታል፡፡ የስነ ጽሁፍ ተሰጦዋንም ለማጎልበት መቀሌ ዩኒቨርስቲ ገብታ በቋንቋ እና ስነጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝታለች፡፡ ወደ አረብ ሀገር ከተሰደዱ ባለ ዲግሪ ኢትዮጵያዊያን አንዷ ናት ፡፡ በትግርኛ ቋንቋ ከሌላ ሰው ጋር በጋራ ካሳተመችው የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ በተጨማሪ የሄዋን ትንሳዔም ከአማርኛው ትርጉም የተወሰነ ልዩነት ቢኖረውም መጀመሪያ በትግሪኛ ነበር የጻፈችው፡፡

በሄዋን ትንሳዔ መጽሐፏ ዳያን በኢትዮጵያ በፌደራልም ሆነ በክልል እንዲሁም ቀይ ባህርን ተሻግራ በዓረብ ሀገራት ሴቶች በሴትነታቸው የሚደርስባቸውን ጭቆና እና ተጽዕኖ በስነ ጽሁፋዊ

ለዛ ቀምራ ነው ለተደራሲያኗ ያቀረበችው፡፡ ገጸ ባህሪዋ ሳራ ሀገር ቤት እያለች ያዘጋጀችውን የፊልም ጽሁፍ  በገንዘብ እንዲደግፍላት ተስማምቶ የተቀበላት ድርጅት ስራ አስኪያጅ ለሌላ ነገር ተመኝቷት ውጥኑ ሲፈርስ ይታያል በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ ወደ ዓረብ ሀገር የተሰደደችው ሳራ ባጋጣሚ በአሰሪዎቿ ቤት ባገኘችው የእረፍት ጊዜ የኢትዮጵያን ቴሌቪዠን ስታይ ያው ሰውዬ ስለ ሴቶች እናትነት ሚስትነትና እህትነት ሲዘበዝብ እንዲሁም ከፍተኛ ድጋፍ እና እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሲሰብክ ትሰማለች በምልሰት ወደ ኋላ ሄዳም ታወጋናለች፡፡በዳያን የሄዋን ትንሳዔ መጽሐፍ ላይ ያለችው ሳራ የተሰኘችው ገጸ ባህሪ አፍቃሪ ስነ ጽሁፍ ሆና ነው የተቀረጸችው ፡፡ ምናልባትም የዳያን የተወሰነ ስብዕና ሳትወስድም አልቀረችም፡፡ የሄዋን ትንሳዔዋ ሳራ የ6 ወይንም 7ኛ ክፍል ተማሪ ሆና ፍቅር አእስከ መቃብርን ታነባለች፡፡ መጽሐፉን ስትጨርስ ግን በእልህ እና በንዴት እንዲሁም በእንባ ተጠምቃ ነበር፡፡ ያስለቀሳት ደግሞ የበዛብህ መሞት ነበር፡፡ ትንሿ ሳራ ሰብለ እና በዛብህ ተጋብተው ልጅ በልጅ ሆነው እንዲኖሩ ነበር እቅዷ ፡፡ዳያን አድጋ ወደ ድርሰቱ ዓለም ገብታ በጻፈችው ልብ ወለድ ታሪክ ግን ባቢ ያለችውን ምርጥ እና ተወዳጅ ገጸባህሪ ጨክና ትገድለዋለች፡፡ዳያን በስነ ጽሁፍ ጉልምስናዋን እና በምናብ ምጥቀቷን ባሳየችበት የሄዋንትንሳዔ መጽሐፏ በርካታ ነገሮችን ዳሳለች፡፡ በመጽሐፉ ዝግጅት ባለው አጭር እና ጠባብ ጌዜም ቢሆን የቋንቋ ሀያሲ ሆኖ የተሳተፈው የሪያዱ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት መምህር ነብዩ ሰለሞን በምርቃቱ ላይ እንደተናገረው የዳያን የሄዋን ትንሳዔ ከስነጽሑፋዊ ፋይዳው በተጨማሪ አዝናኝ በሆነ መንገድ የሚያስቀምጣቸው ጭብጦች ጠቃሚ መልዕክት ያስተላልፋል ፡፡ዳያን ከልጅነቷ ጀምሮ የምትመኘው ነገር ቢኖር በህብረተሰቧ ውስጥ የምታስተውላቸውን ማህበራዊ ችግሮች ተቀርፈው ማየት ብቻ ሳይሆን ለዚህም እሷ ራሷ በምትችለው ሁሉ ተሳታፊ ሆና መገኘት ነው፡፡

መጻፍ ብሎም ማሳተም ይቅር እና ማንበብ እንኳን በዓረብ ሀገር ላለን ለብዙዎቻችን ሩቅ በሆነበት በዚህ ዘመን ፤ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሐን መድረኮች አጫጭር ሀሳቦችን ከመለዋወጥ እና ከማጋራት እምብዛም ባልዘለለው በዚህ በኛ ዘመን ከሳዑዲ ዓረቢያ የበረሀ ምድር ለኩሽና አገልጋይነት ከተሰማራች ኢትዮጵያዊ ወጣት የተገኘ የበረሃ ቴምር ነው የሄዋን ትንሳዔ፡፡ አቶ አብዱል ባሲጥ ጀማል የሪያድ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው። የማዳም ኩሽና ሳሎን እና መኝታ ቤት ፤ የማዳሞች ድግስ  የቤት ሰራተኞች የጋራ ወግ ፤ እስር ቤት ፣ ሺሻ እና በርጫ ድለላ እና ድብድብ ፣ ፍቅር እና ጠብ መራራቅ እና መቀራረብ ከአዲስ አበባ እስከ አረብ ምድር ሁሉንም ያገኛሉ በዳያን የሄዋኗ ትንሳዔ መጽሀፍ፡፡

ዳያን  የብዙ ስነ ልሳን ባለቤት ናት የአፍ መፍቻዋ የሆነውን ትግርኛ ከነ ሰምና ወርቁ አማርኛን ከትናንሽ እርማት ጋር ፣ አረብኛን በንግግር ደረጃ እንግሊዘኛንም እንዲሁ በትምህርት ካዳበረቻቸው ቋንቋዎች መካከል ናቸው፡፡ ይህ ውስጧ የዳበረው የቋንቋ ክህሉት በአማርኛ ጽሁፏ ላይ ይንጸባረቃል፡፡ ለምሳሌ የትግርኛ  ወይንም የአረብኛ የሆኑ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን ወደ አማርኛ አምጥታቸው እናገኛለን፡፡ እናቴ ትምህርት ላይ የነበራት እምነት ትልቅ ነበር ይህ ነው የምለው የማወርሳችሁ ነገር የለኝም እናንተን ለማስተማር ግን እጄንም ገልብጬም ቢሆን እሰራለሁ የሚል አርፍተ ነገር ገጽ 23 ላይ እናገኛለን እጄን ገልብጪ ወይንም በአይበሉባዬ ሰርቼ የሚል አባባል በአማርኛ ቢያንስ በእኔ አካባቢ የተለመደ ያለመሆኑን አውቃለሁ፡፡ አንድ ቦታ ላይ የሚንጣጣን የከሰል ፍም ለመግለጽ ሸጠጠጠጠጠጠጠ የሚል ቃል እናገኛለን እንዲህ እንዲህ ያሉ በርካታ ስነ ቃሎች ፣ ምሳሌያዊ እና ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ዳያን ዲንቃ በየምዕራፎቹ መግቢያ አጫጭር ግትሞችን አስቀምጣለች ገሚሶቹ የራሷ ፣ ገሚሶቹ ምንጫቸው የተጠቀሰ አንዳንዶቹም ምንጫቸው ያልታወቀ በሚል የተቀመጡ ናቸው፡፡

የሔዋን ትንሳዔ ዋነኛ ገፀ ባህርይ ሳራ ተስፋዊት የመጀመሪያው መጨረሻ በሚለው የመጨረሻው ምዕራፍ ገጽ 311 ላይ ካስቀመጠችው አንቀጽ አንድ አርፍተ ነገር ልምዘዝና ዝግጅቴን ላጠናቅ ፡፡ ፍላጎቴ ትላለች ሳራ ፍላጎቴ የምመኛትን ፣ የምፈልጋትን ዓለም በብዕሬ ፈጥሬ ማየት እና ማሳየት ነው፡፡ ቢያንስ መጪው ትውልድ እኔ በምፈጥራት ዓለም ይኖራል የሚል ህልም አለኝ ፡፡ ህልምሽ እንዲሳካ ምኞታችን ነው ሳራ፡፡

ስለሺ ሽብሩ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic