የቐጠር አሚር የጀርመን ጉብኝት | ዓለም | DW | 17.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የቐጠር አሚር የጀርመን ጉብኝት

የጀርመን ርእሰ ብሔር ዮአኪም ጋውክ ፣ ከቐጠር አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ ኧል ታኒ ጋር ፣ ባደረጉት የ 20 ደቂቃ ውይይት ራሱን እስላማዊ መንግሥት እያለ ለሚጠራው አሸባሪ ሚሊሺያ ጦር፣ ያቺው ሀገር እርዳታ ትሰጣለች ስለመባሉ ቢያነሱም ፤አ ሚሩ ማስተባበላቸው ተነገረ።

አሚሩ ለአሸባሪ ቡድን አገራቸው ርዳታ እንደማትሰጥ ነው የተናገሩት። ከመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልና ርእሰ-ብሔር ጋውክ ጋር አሚሩ ከተወያዩ በኋላ ፤ በ IS ላይ በሚወሰደው ዓለም አቀፍ ርምጃ ቐጠርም ተባባሪ መሆኗን አስገንዝበዋል።

ጀርመን ፤ ለቐጠር የተለያዩ ጦር መሳሪያዎችን «ሊዮፓርድ የተሰኘውን ታንክ ጭምር በሽያጭ የምታቀርብ ሀገር በመሆኗ ፤ ጦር መሳሪያው ከማይፈለጉ ወገኖች እጅ እንዳይገባ የሚያሳስባት መሆኑንem ሳትገልጽ አልቀረችም። ለቐጠር ጦር መሣሪያ መሸጡን ፣ ክርስቲያን ዴሞክራቱ ፓርቲ ፤ አረንጓዴዎችና የግራ ፈለግ ተከታይ ፓርቲዎችም ይነቅፋሉ።

ጋውክ ፣ በተጨማሪ፣ በዚያች ሀገር የሰብአዊ መብት ይዞታ በተለይ የውጭ ተወላጆች የሆኑ የስታዲየም ግንባታ ሠራተኞች ስለሚደርስባቸው በደል አንስተው እንደነበረ ቢታወቅም ፤ አሁን ሁኔታው መሻሻሉን ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ ኧል ታኒ ተናግረዋል። ቐጠር፣ እ ጎ አ በ 2022 የዓለምን የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር እንድታዘጋጅ ያቀረበችውን ማመልከቻ ተቀብሎ የዓለም የእግር ኳስ ፌደሬሽን (FIFA) መወሰኑ የሚታወስ ነው።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ በኢራቅና በሶሪያ፣ I S በተሰኘው እጅግ አክራሪ ታጣቂ ኅይል ውስጥ፣ የጀርመን ዜግነት ያላቸው አጥፍቶ ጠፊዎች ቁጥር ከፍ ብሎ መገኘት የጀርመንን ፌደራል መንግሥት እጅግ እንዳሳሰበው ተነገረ።

አንድ የጀርመን ተመራማሪ ቡድን ባደረገው ጥናት መሠረት ፤ እስካሁን አጥፍቶ በመጥፋት የተወሰዱ ቢያንስ 5 ርምጃዎች የተፈጸሙት ከጀርመን ፌደራል ሪፓብሊክ ወደ መካከለኛው ምሥራው በተጓዙ ሰዎች ነው። የሌሎች አጥፍቶ ጠፊዎች ሁኔታም በምርመራና ማጣራት ላይ መሆኑ ተመልክቷል። ከ «ዙዑድ ዶይቸ ትዛይቱንግ» NDR እና WDR የተውጣጣው መርማሪ ቡድን እንዳለው ፣ በ IS ትእዛዝ፤ የአጥፍቶ መጥፋት ርምጃዎቹ ከሞላ ጎደል ሁሉም፣ ኢራቅ ውስጥ በኩርዶች አውራጃዎችና በመዲናይቱ በባግዳድ ነው የተፈጸሙት። የምዕራቡ ዓለም የስለላ ድርጅቶች እንደሚሉት I S ሆን ብሎ ፣ ለፕሮፖጋንዳ እንዲያመቸው፤ ከአውሮፓ የሚሄዱትን ወንዶች ነው በአጥፍቶ መጥፋት ተግባር የሚያሠማራቸው።

ተክሌ የኋላ