የቆቦ ህዝባዊ ተቃዉሞ፤ ግጭትና ግድያ | ኢትዮጵያ | DW | 25.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የቆቦ ህዝባዊ ተቃዉሞ፤ ግጭትና ግድያ

ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ ለተቃዉሞ አደባባይ የወጡ የከተማ ነዋሪወች እና የፀጥታ ሀይሎች ተጋጭተዉ ከ አምስት በላይ ሰወች መሞታቸዉ ተገለፀ።ተቃዉሞዉ በወልደያ ከተማ የጥምቀት በዓልን ሊያከብሩ  በወጡ ሰዎች ላይ የተፈፀመዉን ግድያ ለማዉገዝ የተደረገ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:47

"በተቃዉሞዉ 7 ሰወች ተገድለዋል።" ነዋሪዎች

ሆኖም የጸጥታ ሀይሎች ወደ ከተማዋ ዘልቀዉ በመግባት ወጣቶችን ማሰር በመጀመራቸዉ  ህዝቡ  ከፀጥታ ሀይሎች ጋር ባደረገዉ ግጭት የአንድ የመከላከያ ሰራዊት አባልን ጨምሮ  7 ሰዎች መሞታቸዉንና በርካታ ንብረት መዉደሙን የአካባቢዉ ነዋሪወች ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

እንደ አካባቢዉ ነዋሪወች በቆቦ ከተማ ሰኞ እለት የተቀሰቀሰዉ ይህ ህዝባዊ ተቃዉሞ ከጅምሩ ሰላማዊና ሰሞኑን በወልደያ ከተማ የተፈፀመዉን ግድያ የሚያወግዝ ብቻ ነበር ።ያም ሆኖ ግን የፀጥታ ሀይሎች የተቃዉሞዉን ሰልፍ ለመበተን ጥይት መተኮሳቸዉንና ቆይቶም በሰልፉ የተሳተፉ ወጣቶችን ማሰር መጀመራቸዉን ይናገራሉ። በዚሁ ሳቢያ  በቆቦ ከተማ ነዋሪና በአካባቢዉ ገጠር ቀበሌዎችም ጭምር ተቃዉሞዉ እየጠነከረ መጥቶ በዛሬዉ እለት አንድ የፀጥታ ሀይልን ጨምሮ የ 7 ሰወች ህይወት መጥፋቱንና በርካታ ንብረት መዉደሙን ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢዉ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

"ዛሬ 3ኛ ቀኑ ነው:: ትላንት 8 ስዓት አካባቢ ነው ህዝቡ ሆ ብሎ የወጣው።የስርዓቱ ደጋፊዎችን ባለቡቲኮች፣ ባለህንጻዎች፣ ባለቦቴ መኪናዎች፣ ባለማደያዎች ነበሩ:: የእነርሱን አቃጥለዋል:: [ዛሬ] ማዘጋጃ ቤቱን፣ ፍርድ ቤቱንና ገቢዎች ቢሮን በማቃጠል ተጀመረ:። እስካሁን 7 ልጆች ሞተዋል። አጋዚው ህፃን ሲመታ አርሶ አደሮች አይተውት ገድለውታል። ሌሎቹ በተቃውሞ ወቅት ነው:።"

በተቃዉሞ አመፁ የታሰሩ 13 ያህል ወጣቶች በሀገር ሽማግሌወችና በሀይማኖት አባቶች ሽምግልና ተፈተዉ በአካባቢዉ አንፃራዊ መረጋጋት ታይቶ እንደነበር የገለፁት ነዋሪዉ መንግስትን ይደግፋሉ ያሉትንና ወጣቶቹን " ጠቁመዉ አሳስረዋል" ያላቸዉን የትግራይ ተወላጆች ንብረት ማዉደም መቀጠሉ ግን ዉጥረቱን እንዳባባሰዉ ገልፀዋል።እናም በአሁኑ ስዓት በከተማዋ ከተኩስ ድምፅ በስተቀር ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ነዉ ያሉት።
"ጠዋት ከ11 ሰዓት ጀምሮ የሂሊኮፕተር ድምጾች ነበሩ፣ መከላከያ የሚያወርዱ።ጥይትም እየተኮሱ ነበር።በጣም የተኩስ ድምፅ አለ።ከተማው የጦር አውድማ መስሏል።ስራ የሚባል የለም። ሙሉ ለሙሉ ከተማዋ ውስጥ እንቅስቃሴ የለም።" 

ሌላዉ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የአካባቢዉ ነዋሪ በበኩላቸዉ ህዝቡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከቦታዉ ለቀዉ እንዲወጡ እየጠየቀ ቢሆንም በከተማዋ ዉጥረቱ ተባብሶ በሄሊኮፕተር ጭምር ተጨማሪ ጦር ወደ አካባቢዉ እየገባ መሆኑን አስረድተዋል።በዚህም የተነሳ በከተማዋ ነዋሪወች ዘንድ ከፍተኛ ስጋትና ዉጥረት መንገሱን አመልክተዋል።

በግጭቱ ንብረት መዉደሙ አግባብ እንዳልሆነ የገለፁት ነዋሪዉ ይሁን እንጅ መሳሪያ ባልያዘ ህዝብ ላይ በመተኮስ የሰዉ ህይወት ማጥፋት ለንብረት ማካካሻ መሆን የለበትም ይላሉ።የተጠየቀዉ የመብት ጥያቄና የወደመዉም ንብረትም የሚተካ  በመሆኑ  ህይወት ሊያስከፍል አይገባም ሲሉ ድርጊቱን ይተቻሉ።እንደ ነዋሪወቹ ገለጻ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ብሄሮች በከተማዋ በሰላም አብረዉ በመኖራቸዉ በመካከላቸዉ ምንም አይነት ግጭት ተከስቶ አያዉቅም።የሰሞኑን ግድያ በመቃወምም የትግራይ ወጣቶች ለተቃዉሞ መዉጣታቸዉን ይገልፃሉ እናም ችግሩ የመንግስት የፖለቲካ አስተዳደር እንጅ የሁለቱ ህዝቦች አይደለም ሲሉ ያስረግጣሉ።

ጉዳዩን በተመለከተ የሰሜን ወሎ ዞንንም ይሁን የአማራ ክልል የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊወችን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት ባለመሳካቱ አስተያየታቸዉ ማካተት አልቻልንም።

 

 

 

ፀሀይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic