የቆሻሻ ናዳው ሰለባዎች | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 17.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የቆሻሻ ናዳው ሰለባዎች

በተለምዶ ቆሼ የሚባለው ስፍራ፦ለዓመታት ምናልባትም በብዙዎች ዘንድ የማይታወቅ ስፍራ ነበር። ቅዳሜ የተከሰተው አስደንጋጭ የመደርመስ አደጋ ዜና ግን በመላው ዓለም መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል። ክፉ ክስተት። በውል የታወቀው የሟቾቹ ቁጥር ሐሙስ እለት 115 መድረሱ ተጠቅሷል። ብዙዎች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች እልህ ቁጭታቸውን አንጸባርቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:39

የሟቾቹ ቁጥር ጨምሯል

በተለምዶ ቆሼ የሚባለው ስፍራ ፦ለዓመታት ምናልባትም በብዙዎች ዘንድ የማይታወቅ ስፍራ ነበር። ቅዳሜ ምሽት ላይ የተከሰተው አስደንጋጭ ዜና ግን በመላው ዓለም መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል። ክፉ ክስተት። ለግማሽ ምዕተ-ዓመት የአዲስ አበባ ቆሻሻ ማከማቻ እንደሆነ በተነገረለት በረጲ አካባቢ የሚገኘው፤ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በደረሰው የቆሻሻ ክምር መደርመስ በዕለቱ 15 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ። አፍታም ሳይቆይ ቁጥሩ በእጥፍ አድጎ ሰላሳዎቹ ውስጥ ገባ። አሁንም አሁንም ከቆሻሻ ክምሮቹ ውስጥ አስክሬን መቁጠሩ ቀጠለ። በውል የታወቀው የሟቾቹ ቁጥር ሐሙስ እለት 115 መድረሱ ተጠቅሷል። ብዙዎች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች እልህ ቁጭታቸውን አንጸባርቀዋል። ተጠያቂ ነው የሚሉትን አካልም ነቅሰዋል። የእልቂቱ ሰበብ ነው የሚሉትንም ጠቅሰዋል። 


የዩናይትድ ስቴትሱ ተነባቢ ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስት «ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እድገት ትኩራራለች። በቆሻሻ ክምሩ የሚገኙ አስክሬኖች የሚናገሩት ግን ሌላ ታሪክ ነው» በሚል ርእስ ረቡዕ እለት አንድ ጽሑፍ አስነብቧል። ጽሑፍን ብዙዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተቀባብለውታል።  

የቤት ካርታ ኖሯቸው ስማቸው ያልተመዘገቡት ስላልተቆጠሩ ነው እንጂ በቆሼ የቆሻሻ ክምር ውጧቸው እስከወዲያኛው ያሸለቡ ሟቾች ቁጥር ከሚነገረው በላይ ነው የሚሉ ፅሑፎች ተነበዋል።በእርግጥም የእለት ጉርስ ፍለጋ ወጥተው ያገኟትን ቆጣጥረው ሲመለሱ እናት ከእነህት በቆሻሻ ክምር ተውጠው የቀሩባቸው፣ ከአንድ ቤተሰብ አምስት እና ስድስት አባላት ያለቁባቸው እና ሌሎች በርካታ ልብ የሚነኩ ታሪኮች ተደምጠዋል። 

አንዲት የቤተክርስቲያን አገልጋይ ዘማሪ ወጣት ከበሮ ይዛ የተነሳችው ፎቶ ባለበት ምስል የተጻፈው ደግሞ የበለጠ ያሰቅቃል። ጽሑፉ ወጣቷ ዘማሪ ሦስተኛ ልጇን የወለደችው አደጋው ከመድረሱ 2 ቀን በፊት እንደኾነ ይጠቅሳል። «ያ ክፉ አደጋ አራስ ልጇን እያጠባች ቀሪ ሌሎች ሁለት ልጆቿን እና ባለቤቷን እንዲሁም ሙሉ ቤተሰቧን ቀጥፏል» ሲል ይነበባል። ፍጹም ጎሳዬ ከምስል ጋር አያይዞ ያቀረበው ጽሑፍ ነው።

ሀና ረጋሳ አደጋውን በተመለተ በምስል የተደገፉ የተለያዩ አሳዛኝ ታሪኮችን በፌስቡክ ገጿ በተከታታይ አስነብባለች። የዐስር እና የአንድ አመት ከስድስት ወር ህፃናት ልጆቿን ደጀሰላም ጧፍ በመሸጥ ታስተዳድር የነበረች እናት ሁለት ልጆቿን ከነባለቤቷ አጥታ በብቸኝነት ሐኪም ቤት እንደምትገኝ አስነብባለች። 

«የእህቱን አስክሬን ለመውሰድ እየተጠባበቀ» የሚገኝ ወጣት እንደነገረኝ ባለችው ታሪክ ደግሞ፦ እህቱ «አደጋው በደረሰ ሰአት ለመውጣት ችላ ነበር። ነገር ግን ልጇን ለማውጣት በመመለሷ ምክንያት ሆድዋ ውስጥ ከነበረው ፅንስ እና የመጀመሪያ ልጇ ጋር ዳግም ላትመለስ» ማሸለቧን ገልጣለች።

«የባለቤቱን አስክሬን በፓውዛ ና በስካቫተር እርዳታ በመታገዝ የአስራ ስድስት አመት ታዳጊ ልጁን እጁ ለይ በነበረው ብራስሌት እና አንገቱ ለይ በነበረው የብር ሃብል ተለይቶ ሟች ባለቤቱ ከእህቷዋ ና ከአምስት አመት ልጇ ጋር እና በእንግድነት አብሮ ከነበረ ግለሰብ ጋር አስክሬናቸው ሊገኝ ችሏል» ስትልም ሽመልስ ስለተባለ ወጣት ሰቆቃ በምስል አስደግፋ አስነብባለች።

ቆሼ በተባለው ሥፍራ በየቀኑ 4 ሺህ ቶን የቆሻሻ ክምር ይጣል እንደነበር የአልጀዚራ ዘገባ አትቷል። መንግሥት በቦታው ተቋርጦ የነበረውን የቆሻሻ ክምር መጣል ሂደት ዳግም መጀመሩም ለአደጋው መንስኤ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪን ጠቅሶ ጣቢያው ዘግቧል። 

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ በፌስቡክ እና በትዊተር የተሰራጨ የሸገር 102.1 ኤፍ ኤም የጽሑፍ ዘገባ ደግሞ፦ «ዳግም ቆሻሻ እንዳይጣልበት ሆኖ ተዘግቷል የተባለው የረጲው ቆሼ እንደገና ቆሻሻ መቀበል ጀምሯል» በማለት አስነብቦ ነበር። እንዳይከፈት ሆኖ የተዘጋው ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ መልሶ ለቆሻሻ መጣያነት እንዲውል በከተማዋ አስተዳደር የተወሰነው የሰንዳፋ ላንድ ፊል አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች ቆሻሻው እንዳይመጣብን ሲሉ በማገዳቸው መሆኑን ጠቅሶ ነበር፡።

ጌታቸው በሱዬ፦ «ያለ ገበሬው ፍቃድ እና ስምምነት ነበር ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተገነባ የቆሻሻ ማሥወገጃ አለን ብለው ሲደሰኩሩ የነበሩት፡፡ በ11ኛው ሠዓት» ሲል ትችቱን ከስምንት ወራት በፊት አስነብቦ ነበር። ሸገር፣ ተቋርጦ የነበረው የቆሻሻ መጣል ሒደት እንደ አዲስ መጀመሩ «የአካባቢውን ነዋሪ የበሽታ ስጋት ላይ» መጣሉን በወቅቱ ጠቅሶ ነበር። በአካባቢው የሚገኙ ተማሪዎች ምንነቱ ባልታወቀ ኹኔታ እየታመሙ ራሳቸውን በመሳት ይወደቁ እንደነበርም በተደጋጋሚ ተገልጧል። የበሽታ ስጋት ተደርጎ ይታይ የነበረው የቆሻሻ ክምር ግን ቀን ጠብቆ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀጥፏል። 

የቆሼው አደጋ ከመከሰቱ አስቀድሞ ከባድ ፍንዳታ እና ጩኸት መስማታቸውንም የገለጡም አሉ። ጥላዬ ታረቀኝ ዘ ኢትዮጵያ፦ «ትልቁ ጥያቄ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ ነበረ መባሉ ነው እናም ምን ፈነዳ ?» ሲል በፌስቡክ ጥያቄ አቅርቧል።

በዚህም አለበዚያ ለአደጋው መድረስ ተጠያቂው መንግሥት ነው፤ ስርአት ያለው የቆሻሻ አወጋገድ ፖሊሲ ስለሌለው እና በቦታው ላይም ነዋሪዎች ለአደጋ ተጋልጠው ሲኖሩ በቸልታ መመልከቱ ያስከተለው እልቂት ነው ሲሉ የኮነኑት ጥቂት አይደሉም። አደጋውን በተመለከተ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሐዘን መግለጫ ከማውጣት ባሻገርም መንግሥትን ለአደጋው ተጠያቂ አድርገዋል። 

የከተማዋ አስተዳደር ባለስልጣናት ለደረሰው አሰቃቂ አደጋ በቸልተኝነት ተጠያቂዎች ናቸው ያሉ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ፥ ባለሥልጣናቱ ራሳቸውን ከሥልጣናቸው እንዲያነሱ ጠይቀዋል። 

በአንጻሩ ደግሞ አደጋ ሲደርስ «የአዞ እንባ ነው የምታነቡት፤ ቀደም ሲል ሰዎቹ በአስቸጋሪ ኹኔታ እየኖሩ ዞር ብላችሁ አላያችሁም ሲሉ ትችታቸውን የሰነዘሩም አሉ። የመሬት መደርመስ በየትኛውም ሀገር የሚከሰት አጋጣሚ ነው ሲሉ ድርጊቱን ከመንግሥት ቸልተኝነት ጋር መያያዙን የተቃወሙ አሉ። የለም ይኽ የመሬት መደርመስ ሳይሆን «የቆሻሻ ክምር» መደርመስ ነው «በየትኛውም ሀገር ተሰምቶ አይታወቅም» ሲሉ ተቃውሞውን በሌላ ትችት የተቃወሙም አሉ።

አደጋው መድረሱ እንደተሰማ በርካቶች መንግሥት የሐዘን ቀን እንዲያወጅ ወትውተዋል።  የአደጋው ሰበብ የኾነው አካልን «የሐዘን ቀንን አውጅ ብሎ» መወትወት ተገቢ አይደለም ሲሉ የተቃወሙ ጽሑፎችም ተነበዋል።  

በቆሼ አካባቢ በደረሰው አሰቃቂ የቆሻሻ ክምር መንሸራተት አደጋ የጀርመን ኤምባሲ ለተጎጂዎች እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መሪር ሐዘኑን በመግለጥ ሰኞ እለት ኤምባሲው ሰንደቅ ዓላማው በግማሽ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጉ ብዙዎችን አስደምሟል።  መንግሥት ከረቡዕ ጀምሮ የሦስት ቀን ሐዘን ያወጀው ማክሰኞ እለት ነበር።

ባለፈውም ሊቢያ በረሃ ላይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በአይሲስ ካራ ሲቀሉ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አስቀድሞ ሐዘኑን በመግለጥ ማናቸውንም ትብብር እንደሚያደርግ ሲያስታውቅ መንግሥት የሟቾቹን ዜግነት እናጣራለን ከማለቱ ጋር በማገናኘት ለኅብረተሰቡ ሲበዛ ቸልተኛ ነው  ሲሉ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ምሬታቸውን አሰምተዋል። 

አዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ቅዳሜ ምሽት የደረሰውን የቆሻሻ መደርመስ የተመለከተ ዘገባ በዶይቸ ቬለ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ አቅርበን ነበር። ጽሑፍን ግማሽ ሚሊዮን ግድም ሰዎች ተመልክተውታል። ከ450 በላይ አስተያየቶች  ደርሰውናል። የተወሰኑትን ለማቅረብ እንሞክራለን።

መሀሪ ታምራት፦ «አንድ እውነት እንነጋገር» ሲል ጽሑፉን ይጀምራል። መንግስት ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነ ሁሌም የምናወራው አሁንም እየወተወትነው ያለ ጉዳይ ነው። እኛስ ዜጎቹ? ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብስ? ቆሼ የሚባል መንደር ተመስርቶ የሰው ልጅ ቆሻሻ ተንተርሶ ሲያድር አንድ ቀን እንኳን ድምፁን ያላሰማው ይሄ ሁሉ አዲስ አበቤስ? ጋዜጠኞችስ? ደራሲያንስ? ሙዚቀኞችስ? ባለሐብቶችስ? ፖለቲከኞችስ? እኛስ? ሰው ቆሻሻ ተንተርሶ ማደሩን እንደተራ የሕይወታችን አካል የቆጠርን እኛስ? ወግ ስናሳምር የአንድ ህፃን ሕይወት ለመቀየር እንኳን ያልሞከርነው እኛስ?» ሲል አጠይቋል። «ለአገር መቆርቆር ኢህአዴግን በጥሩ አማርኛ መሳደብ ነው?» በማለትም ችግሩን ወደራሳችንም መጠቆም አለብን ሲል ተችቷል።  

አኑ አኒሻ ደግሞ፦ «እድገታችን የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ አቅም የለውም ወይ...?» ሲል  በመጠየቅ «በ25 ዓመታት ውስጥ ያልሞትንበት ምክንያቶች የሉም» በማለት በሶማሌ ክልል በኦጋዴን  እና በጋምቤላ ክልል ሞት የተለመደ መሆኑን ይጠቅሳል። «ድንበር ዘልቆ ልጆቻንን መነጠቅ የተለመደ እየሆነ መምጣቱን የሙርሲ ህዝብ ምስክር ነው» ሲል በስደት መታረድና በባህር መስጠም የኛ  ነው ሲል ገልጧል። «ዛሬ ደግሞ እነርሱ በሚደፉት ቆሻሻ ሕይዎታችንን ደፉት። አሁንስ የማንሞትበት ቀን ናፈቀን!!!» ሲል ጽሑፉን አጠቃሏል።

ያያ ገላ ማን ከበደ፦ «ፈጣሪ ግን ለምን በኢትዮጵያውያን ላይ ችልተኛ ሆነ? በጦርነት፥በርሃብ፥ በእርስበርስ ግጭት፥ በባለስልጣናቱ ግድየለሽነትና ስግብግብነት በስንቱ ነው ይህ ህዝብ የሚሰቃየው፤ የእስርና የኑሮ ውድነቱን ሳላነሳ» ብሏል።  

ዖማር ኤስፊሃን፦ «ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው!????» ሲል ተፈራ ንጋቱ፦  «መጨረሻችን ምን ይሆን ? ያሁኑ ባሰ» ብሏል። «ኢትዮጵያ  የሚሰማ መንግሥት የላትም» ያለው ዳንኤል ዓለሙ ነው። ቤቲ ግርማ፦ «ከጨዋ መንግስት የሚጠበቅ ተግባር እየተሠራ ነው» ስትል፤ አባቢያ ቤካን ደግሞ፦«አሳፈሪ መንግስት» ሲል አጭር አስተያየት አስፍሯል። «አይ ድህነታችን ኑራችንም ሞታችንም አሰቃቂ»  የሚል አስተያየት ያሰፈረው ደግሞ ዘመን ጸጋዬ ነው። ካሌብ ማቴዎስ መኮንን፦ «መርከቧ ከሰጠመች በኋላ እንዴት ልትድን ትችል እንደነበር ሁሉም ያውቃል» ሲል ተችቷል። እግዚአብሔር ሆይ በቃ በለን!!!!» በጤና ይበልጣል የቀረበ ተማጽኖ ነው። ለሞቱት ነፍስ ይማር ያሉ እና ለሐዘንተኞች መጽናናትን የተመኙ በርካቶች ናቸው 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች