የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት | ባህል | DW | 23.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት

ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመቱ በተለያየ መስክ በመከበር ላይ ይገኛል። ቅዱስ ያሬድ በአውሮጳ ሙዚቃ ገናና ስም ያላቸው የሙዚቃ ቀማሪውች ከመፈጠራቸው ከሺህ ዓመታት ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረ ሊቅ ነው።

እነ ሞዛርትና ቤትሖቨንም ሆኑ «የአውሮጳ የሙዚቃ አባት» የሚሰኘው ዮሐን ሰባስቲያን ባህ ብቅ ከማለቱ ሺህ ዓመት ገደማ ቀድሞ ነው በአፍሪቃ ምድር የተወለደው፤ ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ። አብዛኛው የዓለም ክፍል በሙዚቃ ብርሃን እጦት በጭለማ ይዳክር የነበረበት የስድስተኛው ክፍለ ዘመን መንደርደሪያ። በአንፃሩ ኢትዮጵያ በአክሱም ሥልጣኔዋ ጫፍ ደርሳ ከድንቅ ኪነ-ሕንፃዎቿና ሀውልቶቿ ስር ረቂቅ ዜማዎችንም ማጣጣም የጀመረችበት ወርቃማ ዘመን። ያ ዘመን ኢትዮጵያ የዜማ ሊቁ ቅዱስ ያሬድን ያገኘችበት ልዩ ዘመን ነበር ።

ቅዱስ ያሬድ ግዕዝ፣ ዕዝል ዓራራይ ሲል በሦስት ዓበይት ክፍሎች ውስጥ ቀምሮ ያስቀመጣቸው የዜማ ስራዎቹ ሺህ ዓመታትንም ተሻግረው ቢሆን ዛሬም ድረስ ያለ አንዳች ለውጥ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይደመጣል። የማኅበረ ቅዱሳን አባልና አገልጋይ የሆኑት የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ዲያቆን ብርሀኑ አድማስ ቅዱስ ያሬድን እንዲህ ይገልጡታል።

የቅዱስ ያሬድ ድንቅ የዜማ ድርሰቶች መጽሐፈ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ በሚል ዓብይ ርዕስ ስር ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬና መዋስዕት በሚል ተቀምጠው ይገኛሉ። ወ/ሮ አምሳለ ሙሉጌታ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጥበባት ኮሌጅ ተባባሪ ዲን ናቸው፤ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤትም ያስተምራሉ። እሳቸውም ቅዱስ ያሬድን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ

የዜማ ሊቁ ቅዱስ ያሬድን አስመልክቶ ብዙውን ጊዜ ለእራሳችን ነገር ዋጋ አንሰጥም ሲል በቁጭት የሚገልፀው ግርማ ይፍራሸዋ ነው። ግርማ በረቂቅ ሙዚቃ ጥበብ አገራችን ካፈራቻቸው ጥቂት የዘመናችን የዜማ ልሂቃን መካከል አንዱ ነው።

ግርማ ይፍራሸዋ

ግርማ ይፍራሸዋ

ግርማ ከስድስት ወራት በፊት የሙዚቃ ስራዎቹን በተመለከተ እዚህ ጀርመን አገር በመጣበት ወቅት የዜማ ሊቁ ቅዱስ ያሬድን የሚዘክር ፅሁፍ አቅርቦ እንደነበረ ገልጿል። በጽሁፉም ቅዱስ ያሬድ ዜማን በምልክት በማስፈር ለዓለም ፈር ቀዳጅ እንደነበር ለታዳሚያኑ አውስቷል፤ ምንም እንኳን እንደ እሱ አባባል ታዳሚያኑ አባባሉ ባይዋጥላቸውም ማለት ነው።

ተመራማሪዎች ከጥንት ጀምሮ ከአገር ወደ አገር ስለሚዘዋወሩ የያሬድ ዜማዎች በእነዚህ ተመራማሪዎች በኩል ወደ ውጭ ሾልኮ ሊሆን ይችላል ይላል ግርማ። ሆኖም ይህ አባባል በጥናት ሊደገፍ ይገባል ሲልም አክሏል። ልክ እንደ ግርማ ይፍራሸዋ ሁሉ በተለያዩ ታላላቅ የሙዚቃ አቀናባሪዎች መታሰቢያ ላይ ለመታደም የቻለ ወጣት ነው፤ የሙዚቃ ባለሙያውና ተመራማሪው ሠርፀ ፍሬስብኃት። ቅዱስ ያሬድ የስራውን ያህል አላከበርነውም ሲል ቁጭቱን በእዚህ መልኩ ያንፀባርቃል።

ሠርፀ ይህ የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ብዙ ነገሮችን ልናደርግ ይገባል ሲል አፅንኦት ሰጥቶበታል። እንደ ሠርፀ ሁሉ ባለሙያዎቹ በአጠቃላይ የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች በዓለም ደረጃ እውቅና ያለማግኘታቸው ሰበቡ አንድም እኛ ያን ያህል ትኩረት ያለመስጠታችን በሌላ መልኩ ደግሞ ዓለም የጥበብ ትሩፋቶቹን አይቶ እንዳላየ የመሆኑ ምክንያት ነው ሲሉ ይስማማሉ። ሠርፀ የቅዱስ ያሬድ ዜማዎችን ጨምሮ ዓለም ለኢትዮጵያና ለጥቁሮች ባህል ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም ሲል ቅያሜውን እንዲህ ይገልጻል።

የረቂቅ ሙዚቃ ባለሙያው ግርማ ይፍራሸዋ እነሾፐንን ጨምሮ ታላላቅ የዓለማችን የሙዚቃ አቀናባሪዎችን ለመዘከር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት በተካሄዱ የተለያዩ ታላላቅ ዝግጅቶች ላይ በክብር እንግድነት ታድሞ ስራዎቹን ለማቅረብ የቻለ ባለሙያ ነው። በተጋበዘባቸው ዝግጅቶች ላይ ምዕራባውያኑ ለሙዚቃ ጠቢባኖቻቸው የሚሰጡትን ክብር በእዚህ መልኩ ያብራራል።

ዲያቆን ብርሃኑ በእዚህ በያዝነው ዓመት 1500 ዓመት ለሞላው የዜማ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ በተለያዩ ቦታዎች የመታሰቢያ ስርዓቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ሆኖም የዜማ ሊቁ ስራዎች በጥልቀት እንዳልተሰራባቸውና የማስተዋወቅ ስራም ገና መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

በዓለም የታላላቅ ሰዎችና የድንቅ ስራዎች መዛግብት ላይ ቅዱስ ያሬድ ያለመስፈሩ ሁናቴ የማስቆጨቱን ያህል በአገር ውስጥ የሊቁን ዜማዎች የማስተዋወቁ ስራም በቂ አይደለም ሲል ሠርፀ ተመሳሳይ ሀሳብ ያንፀባርቃል። የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህርና ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጥበባት ኮሌጅ ተባባሪ ዲን ለቀረበው አስተያየት የተለየ መልስ አላቸው።

ዲያቆን ብርሃኑ ቅዱስ ያሬድን ጨምሮ በኢትዮጵያ ያሉ ሀብቶችን በማስተዋወቁ ረገድ ድርሻው የሁሉም መሆኑን በመግለጽ መልዕክታቸውን በእዚህ መልኩ ያስተላልፋሉ።

ሙሉ ዝግጅቱን ለማዳመጥ ከታች ያለውን የድምፅ ማጫወቻ ይጠቁሙ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic