የቅርቡ የአሸባብ ጥቃት እና የአፍሪቃ ህብረት ጦር | አፍሪቃ | DW | 26.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቅርቡ የአሸባብ ጥቃት እና የአፍሪቃ ህብረት ጦር

የሶማሊያ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ትናንት መዲና ሞቃዲሾ የሚገኘዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ተረጋግጧል። በዚሁ ጥቃት ከአፍሪቃ ሕብረት ወታደሮች ጋር በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ ሶስት ወታደሮችን ጨምሮ ቢያንስ 9 ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል።

ትናንት ሞቃዲሾ ውስጥ ለደረሰው ጥቃት የሶማሊያ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ወዲያው ነዉ ኃላፊነት የወሰደዉ። አክራሪ ቡድኑ እንዳስታወቀው ኢላማው የምዕራብ ሃ ገራት ኢምባሲዎች እና የተባበሩት መንግሥታት ቢሮዎች የሚገኙበት የአፍሪቃ ህብረት የጦር ሰፈር ነበር። በዚህ የጦር ሰፈር በሶማሊያ የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በምሕፃሩ አሚሶም ይገኛል።« ስምንት ታጣቂዎች ፤ ሀልነ በሚባለዉ እና የአሚሶም የጦር ሰፈር መጨረሻ ራቅ ብሎ ከበስተ ጀርባ በሚገኘዉ በኩል የገቡት። እነዚህም ስምንት ታጣቂዎች መግቢያዉን የሚጠብቁ የአሚሶም ወታደሮች ሳያስተውሏቸው በድብቅ ነዉ ወደ ጦር ሰፈሩ ሰርገው ገቡት። በኋላ ነዉ የአሚሶም ወታደሮች የአሸባብ ታጣቂዎች ግቢዉ ውስጥ እንዳሉ የተረዱት። ከዛም በሁለቱ ቡድናት መካከል ተኩስ ተከፈተ፤ አምስቱ ሲገደሉ ሶስቱ ደግሞ ራሳቸውን በፈንጂ አጋዩ። አራት የአፍሪቃ ህብረት የዩጋንዳ ወታደሮች ደግሞ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ነገር ግን አልሞቱም። »

ይላል ሞቃዲሾ የሚገኘው የዶይቸ ቬለ ወኪል መሀመድ ኡማር ሁሴን ። የአሚሶም የሶማልያው ቃል አቀባይ ኮሎኔል አሊ አደን ሑመድ - ለአሶሺየትድ ፕረስ እንደገለፁት ደግሞ፤ የጦር ኃይላቸው ሶስቱን የአሸባብ ታጣቂዎች ሲገድል ሁለቱ ደግሞ በነዳጅ ማጠራቀሚያ አቅራቢያ ራሳቸዉን በፈንጂ አጋይተዋል። ሶስት ወታደሮች ደግሞ በተኩስ ልዉዉጡ ተገድለዋል።

Somalia: Al-Shabaab-Miliz bestimmt Ahmed Umar zum neuen Anführer

የአሸባብ መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔን መገደል ሶማሊያውያን በቴሌቪዥን ሲከታተሉ

አሸባብ በድረ ገፁ ላይ ባወጣው የድምፅ መግለጫ መሰረት፤ የገና በዓል በማክበር ላይ በነበሩ የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮች ላይ ጥቃት የሰነዘረው በዚህ ዓመት ዩናይትድ ስቴትስ የቡድናቸውን መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔን በመግደሏ፤ ይህንን ለመበቀል መሆኑን ገልጿል። ቡድኑ በዚህም ጥቃት 14 የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮችን እና አራት የውጭ ሀገር ዜጎችን ገድያለሁ ብሏል።

ቁጥሩ የተጋነነ ይሁን አይሁንም አሸባብ በአፍሪቃ ህብረት ላይ ጥቃት ሲጥል የትናንቱ የመጀመሪያው አይደለም። እኢአ 2011 እንዲሁ ሞቃዲሾ ውስጥ ቡድኑ በከፈተው ተኩስ ቢያንስ 1o ሰዎች ተገድለዋል። ባለፈው ወር መጨረሻ ሞቃዲሾ የአይሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ አንድ የተመድ ተሽከርካሪ የተቀበረ ቦንብ ላይ ወጥቶ ሶስት ሰዎች ሞተዋል። አሸባብ በአንድ በኩል እየተዳከመ ነው ሲባል በሌላ በኩል ቡድኑ መሠረቱን ባደረገበት ሶማሊያም ይሁን በጎረቤት ሀገር ኬንያ በተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘሩ ይታይያል። ቢሆንም አሸባብ ይህን ያህል ጠንካራ አይደለም ይላል፤ መሀመድ ኡማር ሁሴን፤«እንደምናውቀው ከጥቂት ወራት በፊት አሸባብ ደቡብ ሶማሊያን በጠቅላላ በቁጥጥር ስር አውሏት ነበር። አሁን ግን ይህ ቦታ በጠቅላላ በአሸባብ ቁጥጥር ስር ነው የምንለው ቦታ የለም። ቀስ በቀስ ከሁሉም ቦታ እየተወገዱ ነው።»ከትናንትናው ጥቃት በኋላስ በሶማሊያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

«መንግሥትም እንዳስታወቀው የአሸባብ ታጣቂዎች በአንዳንድ የሶማሊያ ክፍል ይንቀሳቀሳሉ። ይሁንና ከዚህ በፊት እንደነበሩት አይደለም። እና ጠቅላላ በሞቃዲሾ በአሁኑ ሰዓት ያለው ሁኔታ የተረጋጋ ነው። ሰዎች እንደወትሮዉ የቀን ተቀን ተግባራቸውን እየፈፀሙ ይገኛሉ።»

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic