የቃጠሎ ጥቃት በስደተኞች መጠለያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 17.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የቃጠሎ ጥቃት በስደተኞች መጠለያ

በጀርመን ኒደር ዛክሰን ግዛት ዛልስሄምንዶርፍ ዉስጥ በሚገኝ የስደተኞች መኖርያ ላይ ቃጠሎ ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦች የፍርድ ብይን ዛሬ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ባለፉት 25 ዓመታት ለተካሄዱት እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች በፍርድ ሂደት ብይን ያገኙት ጥቂቶች ናቸዉ።


የስደተኞች መኖሪያ ተቃጥሎ ነበልባሉ እሳት መስኮቱን እየሰባበረ ቡልቅ ቡልቅ እያለ ይንቦገቦጋል። የእሳት ቃጠሎዉ የተነሳዉ በመኖሪያ ቤቱ ኮሪደር ላይ ቤንዚን መያዣ ጀሪካን በእሳት በመለኩሶ ነበር። የሚቃጠለዉን የስደተኞች መኖሪያ ከመንገድ ላይ ከቅርብ ርቀት ሆነዉ የሚከታተሉ አንዳንድ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ያጨበጭባሉ አልያም ሌሎች አደጋዉን አይተዉ እንዳላዩ ፊታቸዉን አዙረዉ ይሄዳሉ። እዚያ አካባቢ በሚገኘዉ ከተማ በድሪስደን የስደተኞች መንደር ስደተኞችን ከሚረዱት አንዱ የሆነዉ እንደዳንኤል ሞሊቶር ያሉ ሰዎች ደግሞ የግድያ ዛቻ በተደጋጋሚ ይደርሳቸዋል።


« ሁለት ጊዜ ማስፈራርያ ደርሶኛል አንደኛዉ እኔን ቢሰቅለኝ ደስ የሚለዉ ነዉ። እኔን ለማግኘት ግን እኔን መጀመርያ ዛፍ ላይ መስቀል ይኖርባቸዋል።»


ይህ ዓይነቱ ዛቻ በየጊዜዉ ያለ ምንም ሃፍረት በግልፅ የሚታይ ጉዳይ ሆንዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ በምሥራቃዊዉ የጀርመን ክፍል ብቻ ሳይሆን በምዕራቡም ማለት በባየርን፤ በቫደንቩተንበርግ እንዲሁም በኖርድ ራይን ቬስት ፋለን ግዛትም የሚታይ ነዉ። በፊደራል ጀርመን የወንጀል ነክ ጉዳዮች ከመጠን በላይ መጨመሩን በጥናት የተደገፈዉ መዘርዝር ያሳይል። ከጎርጎረሳዊዉ 2011 ዓ,ም ጀምሮ ተገን ጠያቂዎች በሚኖሩበት የስደተኞች መጠለያ ጣብያ 18 ጥቃት የታየ ሲሆን፤ ባለፈዉ የጎርጎርዮሳዊ 2015 ዓ,ም 900 ጥቃት መድረሱ ተመዝግቦአል። እንዲያም ሆኖ ክስ ተመስርቶባቸዉ ለፍርድ የቀረቡ ወንጀለኞች እጅግ ጥቂት ናቸዉ።


በጀርመን የዛክሰን ግዛት መከላከያ ማዕከል« OAZ» በምሥራቅ ጀርመን የሚታዩ እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን ይቃወማል፤ ይከላከላልም። ትልቁ የመርማሪዎች ችግር ይህን ወንጀል ፈጻሚዎቹ ገጽታቸዉን መቀያየራቸዉ ነዉ ሲሉ፤ የዛክሰን መከላከያ ማዕከል« OAZ» ዋና ተጠሪ ቤርንድ ሜርቢትዝ ይገልፃሉ።
«የቀኝ አክራሪዎች የሚለዩት በሚያደርጓቸዉ ትልልቅ ጃኬቶች እንዲሁም ጥቁር ቡትስ ጫማቸዉ ነዉ። እንዲህ ያለዉን ነገርን የሚያደረጉት አናይም። ካየንም በጣም ብዙ ጊዜያችን ነዉ።»

Infografik Gewalt gegen Flüchtlingsunterkünfte 2015/2016 Deutsch

በጎርጎረሳዊዉ 2015 / 16 ዓ,ም በጀርመን በሚገኝ የስደተኛ መጠለያ የደረሰ የቃጠሎ ጥቃት


በተደጋጋሚ ከወንጀሉ ጋር በተገናኘ የሚያዙት ግለሰቦች፤ በፖሊስ ያልተመዘገቡ እና ነጥብ ያልተያዘባቸዉ፤ እስካሁንም በወንጀል ተጠርጥረዉ የማይታዉቁ ሲሆኑ፤ አብዛኛዉን ጊዜ ከማኅበረሰቡ መካከል የወጡ ከ 18 እስከ 35 ዓመት እድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ ናቸዉ።


«ትክክለኛ ነገር አላደረኩም» የሚል አስተሳሰብ በተወሰነ የማኅበረሰቡ ክፍል እየቀነሰ መጥቶአል ሲሉ እንዲህ ዓይነቶቹ ወንጀሎች በሚታዩባቸዉ ቦታዎች የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ይገልጻሉ። ከአንድ ዓመት በፊት በዛክስን አንሃልት ትሮግሊትዝ ዉስጥ የሚኖር ሰዉ ስለተቃጠለዉ የስደተኞች መኖሪያ ሲናገር፤
«ይህ ነገር በጣም መጥፎ ነዉ። ግን ይህ ጥቃት የህዝብን መሰላቸት ያመላክታል፤ ምክንያቱ ደግሞ የስደተኞች ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ ነዉ። ማንኛዉም ሰዉ እዚህ ደህንነት አይሰማዉም።»
ከእንደዚህ ዓይነቱ ራስን ከእዉነት አርቆ የመፈረጅ አነጋገር ስደተኞችን የሚረዳዉ የአማዶ አንቶንዮ ተቋም ባልደረባ አኔታ ካንን በጣም ነዉ ያሳዘናት።
« ተከታትለን እንደተመለከትነዉ ፤ እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት የሚደርሰዉ በተወሰኑ ቡድኖች ላይ ነዉ። ይህም ጥቃቱ በስደተኞች ላይ ነዉ የሚፈፀመዉ። ይህ ዓይነቱ ጥቃት ደግሞ የከፋ የዘርኝነት አመለካከትን በተቀሩት ህዝብ መካከል ዉስጥ ያስነሳል። »
አኔታ ካን በብዛት ጥቃት በሚታይባቸዉ ቦታዎች ላይ ሌላ ገጽታ እንዳለ፤ ማለትም ስደተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀራረቡ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችም እንዳሉ መረጃ መኖሩን ገልፀዋል። ሆኖም ይህን ዓይነቱ ጥቃት ቆሞ ሁኔታዉ በቶሎ ወደ ጥሩ ሁኔታ ይቀለበሳል የሚል ተስፋ የላቸዉም።


ከ 25 ዓመት ጀምሮ በስደተኞችና በተገን ጠያቂዎች መጠለያ ላይ በመጀመርያ የደረሰዉ ጥቃት በሆይረስቤርዳ፤ በሮስቶክ፤ በአሻፍንቡርግ፤ ሽፓየር እና ኢምንሃዉዘን ከተሞች ላይ ነዉ። በኖርድ ራይን ቬስት ፋለን ግዛት ሀንክስ በሚባል ቦታ በጎርጎረሳዊዉ 1991ዓ,ም ሁለት የስድስት እና የስምንት ዓመት ሴቶች ልጆች ላይ ከባድ የቃጠሎ ጉዳት ደርሶአዋል። በ1996 ዓ,ም በሽሊዝቪግ ሆልሽታይን ግዛት ሉቤክ ዉስጥ በተገን ጠያቂዎች መኖሪያ ላይ በተጣለዉ የቃጠሎ ጥቃት 10 ሰዎች ሕይወታቸዉ አልፎአል። እስካሁን በዚህ ጉዳይ የተፈረደበት አልያም ኃላፊነትን የወሰደ ሰዉ የለም።
በራይንላንድ ፋልዝ ግዛት በሉድፊክስሃፈን ከተማ በጎርጎርዮሳዊዉ 2000 ዓ,ም ላይ በደረሰ ጥቃት ከባድ የሰዉነት ቃጠሎ የደረሰባቸዉን ሕጻናት ማትረፍ አልተቻለም። ከዚያም ቀጥለዉ ባሉት ዓመታቶች የእሳት ቃጠሎ ጥቃቱ ቀጥሎአል። ቀኝ አክራሪዎች በስደተኞች መጠለያ ጣብያ የሚያደርሱትን ጥቃት በፖሊስ፤ በአቃቤ ሕግና ተገን ጠያቂዎችን በሚረዳዉ አሜዱ አንቶንዮ ተቋም በመቶ ገፆች ላይ ተዘርዝሮ ይገኛል። ስደተኞች በብዛት መምጣት ከጀመሩ ጊዜ ጀምሮ ጥቃትና የወንጀል ድርጊት እየበዛ ሄዷል።
ባለፈዉ ዓመት ነሐሴ ወር በኒደርዛክስን ግዛት ዛልስሄምንዶርፍ ገጠር ዉስጥ ጥቃት የደረሰ ሲሆን የዚች አነስተኛ ገጠር ከንቲባ እንደገለፁት ከሆነ በጥቃቱ እስካሁን ከቀኞች የደረሰ ስለመሆኑ የሚታይ ምንም ዓይነት ማስረጃ አልተገኘም።

እንዲያዉም በርካታ ስደተኞችን የሚረዱ እንዳሉ ነዉ የተመለከተዉ። እጅግ ጭካኔ የተሞላ ጥቃት አድራሾቹ ዒላማ ያደረጉት ስደተኞች በዉስጡ የሚኖሩበትን ሕንፃ ነዉ። ጓዳ ሠራሽ ተቀጣጣይ ቦምብ ቤቱ ላይ ሲጣል እሳቱ በተለይ ሕጻናት ክፍል ነበር ያረፈዉ። እንደ እድል ሆኖ ግን በዚህ ጥቃት ማንም አልሞተም ማንም አልተጎዳምም። ይህን ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት አሁን ፍርድ ፊት እንደሚቀርቡ ተገልጿል። እንዲህ ያለዉ ጥቃት ለስደተኞች እጅግ አስከፊ ሁኔታን ይፈጥርባቸዋል ያሉት ፤ የጥቃት ሰለቦችን በሚረዳዉ «እዝራ» በተሰኘዉ ድርጅት የሚያገለግሉት ፍራንክ ዞብል እንደሚሉት፤ « አብዛኞቹ የመኖሪያ ቦታቸዉን ለቀዉ መዉጣትን ይፈራሉ። በነጻ የመዘዋወር መብታቸዉ ሙሉ በሙሉ ተጥሶአ።» በዚህም ይላሉ ዞብል ፤ ስደተኞቹ በጀርመን ማኅበረሰብ ዉስጥ ተዋህደዉ የመኖራቸዉ ነገር የማይቻል ነዉ።

ዎልፍጋንግ ዲክ / አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic