የቁጠባ ርምጃዎችና የሥራ ዕድል | ዓለም | DW | 01.05.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የቁጠባ ርምጃዎችና የሥራ ዕድል

ዓለም ዓቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ILO መንግስታት የሚወስዱት የቁጠባ ርምጃ በርካቶችን ለሥራ አጥነት ሊዳርግ ይችላል የሚል ስጋቱን አሰማ። የዓለም ሠራተኞች ቀን በሚታሰብበት ዕለት ዋዜማ ILO ይፋ ባደረገዉ መግለጫ እንዳመለከተዉ በዓለም ዓቀፍ

ደረጃ የሥራ አጡ ቁጥር ካለፈዉ ዓመት ዘንድሮ ሊጨምር ይችላል። መዘዙም አፍሪቃ ዉስጥ ማኅበራዊ አለመረጋጋትን ሊያስከትል እንደሚችል ድርጅቱ ከወዲሁ አስገንዝቧል።

በእንግሊዝኛዉ ምህፃረ ቃል ILO የተሰኘዉ ዓለም ዓቀፍ የሠራተኞች ድርጅት የፋይናንስ ቀዉስ የገጠማቸዉ የተለያዩ መንግስታት የሚወስዱት የቁጠባ እንዲሁም የሥራ ገበያዉ ማሻሻያ ርምጃ አሉታዊ መዘዝ ያስከትላል ባይ ነዉ። ILO በዘገባዉ መሥራት በሚችሉበት ማለትም ከ25 እስከ 49 የእድሜ ክልል የሚገኙ በአደጉ ሐገሮች የሚኖሩ ዜጎች ከሥራ ገበታ ዉጭ እንደሚገኙ፤ ለረዥም ዓመታት ሥራ በመፈለግ የዋተቱ ወገኖችም መንፈሳቸዉ መላሸቁን ዘርዝሯል። ወጣት ሥራ አጦች ቁጥራቸዉ መበራከቱን፤ ይህም በተለይ በአፍሪቃና በመካከለኛዉ ምስራቅ ለማኅበራዊ አለመረጋጋት ስጋት እንደሆነም ጠቅሷል።

ድርጅቱ በመግለጫዉ መንግስታት የሚወስዱት የቁጠባ ርምጃ በያዝነዉ የአዉሮጳዉያን 2012 ዓ,ም የሥራ አጡን ቁጥር ወደ202 ሚሊዮን እንደሚደርስም ተንብዩዋል። ይህ ሁኔታ ከወዲሁ መፍትሄ ካልተፈለገለት ሌላ የክስረትና የቀዉስ ዓመት መከተሉ አይቀርም፤ የሚሉት የድርጅቱ ዳይሬክተርና የጥናቱ ፀሐፊ ራይሞንድ ቶረስ የሥራ ፈላጊዉ ህዝብ ቁጥርም ከፍ ይላል ነዉ ያሉት፤

«ምንም ካልተደረገ የILO ትንበያ በዚህ ዓመት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በስድስት ሚሊዮን፤ በሚቀጥለዉ ዓመት ደግሞ በተጨማሪ አምስት ሚሊዮን እንደሚጨምር ያሳያል።»

የፋይናንስ ቀዉስ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ መድረሱ ከተነገረበት ከዛሬ አራት ዓመት ወዲህ በተለያዩ ሐገሮች 50 ሚሊዮን የሥራ ቦታዎች ሲታጠፉ፤ ባለፈዉ የአዉሮጳዉያን ዓመት መጨረሻ ደግሞ የሥራ ያለህ የሚለዉ ወገን 200 ሚሊዮን መድረሱ ተገልጿል። የኤኮኖሚ መዳከም የገጠማቸዉ የተለያዩ ሐገሮች ከገቡበት ክስረት ለመዉጣት የሚወስዷቸዉ ጠንካራ የቁጠባ ርምጃዎች የመንግስትን ወጪ በመቀነስ ሳይገቱ የህዝቡን የሥራ እድልም የነኩ በመሆናቸዉ ለቁጠባ የታቀደዉ ስልት የታለመለትን ዉጤት እንዳላሳየም ቶረስ ጠቁመዋል፤

«የቁጠባዉ ርምጃ ተጨማሪ የኤኮኖሚ እድገት አላመጣም። የነበረዉ እይታ የመንግስት በጀትና የመንግስት የንዋይ ፍሰት ሲቀነስ፤ የግል የመዋዕለ ንዋይ እና የባለሃብቶች ገንዘባቸዉን ሥራ ላይ የማዋል ፍላጎት ከፍ ይላል የሚል ነዉ። ይህ ግን አልሆነም።»

ይህ በመሆኑም በተለያዩ የአዉሮጳ ሐገሮች አሉታዊ ዉጤቱ ተባብሶ መታየቱን ያመለከተዉ የILO ዘገባ መዘዙ ወደሌሎች የዓለም ክፍሎችም እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሷል።

የILOን ስጋት ያጠናከሩ የየመንግስታቱን የቁጠባ እቅድ የተቃወሙ ሰልፎች በተለያዩ ሐገሮች ዛሬ ተካሂደዋል። የዓለም የሠራተኞች ቀንን ተንተርሰዉ በተለያዩ የአዉሮጳ ሐገሮች የቁጠባ እቅዱን የተቃወሙ ሠልፎች ተካሂደዋል፤ ፓሪስና አቴንስ ከተሞች ላይ ደግሞ ከዚሁ በተገናኘ ሠልፈኞች መሪዎችን ለመገልበጥ አስፈራርተዋል። እስያ ዉስጥ ሠልፈኞች የደሞዝ ጭማሪ ሲጠይቁ፤ ኤንዶኔዢያ ጃካርታ ላይ በሺዎች የተገመቱ ሠራተኞች ከተሻለ ክፍያ በተጨማሪ የሥራ ዋስትና እንዲሰጣቸዉ አመልክተዋል። ሩሲያ ዉስጥ ባለፈዉ ምርጫ ፕሬዝደንትነታቸዉን ያስፀደቁት ቭላድሚር ፑቲን አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ከተገመተዉ ሠልፈኛ ጋ በመቀላቀል አደባባይ ወጥተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic