የቁስ አካልን ምንጭ ምንነት ለማወቅ የሚደረገው ቀጣይ ምርምር፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 10.03.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የቁስ አካልን ምንጭ ምንነት ለማወቅ የሚደረገው ቀጣይ ምርምር፣

የአውሮፓ የአቶም ምርምር ድርጅት(CERN) የፍጥረተ-ዓለም ክሥተት፣ ከ 13,7 ቢልዮን ዓመት ገደማ በፊት እውን ሊሆን የቻለበትን ሁኔታ፣

default

በቤተ-ሙከራ ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እንደቀጠለ ነው። የሥነ-ፈለክና የኅዋ ፊዚክስ ጠበብት ፣ አንዱ ዓላማቸው በኅዋ ፣ ጥቁር ጉድጓድ የሚባለውን ምንነት ምሥጢር ማወቅ ነው። ምንም እንኳ፣ ፍጹም መጠን-የለሽ በሆነው ኅዋ ፣ 25 ከመቶው ጥቁር ጉድጓድ ነው ተብሎ ይታመን እንጂ፣ ይህን እስካሁን በትክክል ሊያረጋግጥ የቻለ የለም።

በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ የ CERN ዋና ሥራ አስኪያጅ ጀርመናዊው ሳይንቲስት Rolf-Dieter Heuer በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፣የተባለው «ጨለማ የዋጠው ነገር» በትክክል ምን እንደሆነ የሚያውቅ የለም። ስለሆነም፣ በ CERN የሚገኘው ብዙ የተነገረለት፣ የአቶም ቅንጣቶችን በኃይለኛ ፍጥነት የሚያጋጨውም ሆነ የሚጨፈልቀው Large Hadron Collider የተባለው ማሺን ፣ የኅዋን የጨለማ ምሥጢር ፣ ለማወቅ ትንሽ ፍንጭ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። እስካሁን የሥነ-ፈለክና የፊዚክስ ጠበብት፣ እንደሚሉት፣ ሰዎች እስካሁን ፍጹም መጠን ከሌለው ኅዋ የሚያውቁት 5 ከመቶውን ብቻ ሲሆን ቀሪው የማይታየውም ሆነ ያልተደረሰበት ከፊል፣ «ጨለማና ጨለማዊ ኃይል የሚሰኝ » ነው። ይህም በኅዋ 25 ከመቶውን፣ በአንዳንድ አካባቢም 70 ከመቶውን ይሸፍናል ተብሎ ነው የሚታሰበው። «የጨለመውን ነገር፣ በቤተ-ሙከራ ለማወቅ ከበቃን ፣ ስለኅዋ የሚኖረን ዕውቀት 30 ከመቶውን የሚያካትት ይሆናል» ሲሉም፣ ሮልፍ -ዲተር ሆየር ተናግረዋል። ከ 3 ሳምንት ገደማ በኋላ፣ በ CERN የሚከናወነውን የአቶም ቅንጣቶች የማጋጨትም ሆነ የመጨፍለቅ እርምጃ ውጤት በዚያው የምርምር ማዕከል በ ሺ የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ አያሌ አብያተ-ሙከራ ይመራመሩበታል። ባጠቃላይ በ 7 «ቴራ ኤሌክትሮን ቮልት» (TeV) የሚከናወነውን በተደጋጋሚ የአቶም ቅንጣቶችን የማጋጨት እርምጃ፣ አነስተኛ ፣ የቅድመ-ፍጥረተ ዓለም ዓይነት ፍንዳታዎችን በማስከተል፣ ቀጥሎ ምን እንደሚከናወንም ሆነ እንደሚፈጠር ፣ ፍንጭ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በሂደቱ ላይ ጠበብቱ ምርምራቸውን ይቀጥላሉ። LHC በሚል ምኅጻር የታወቀው ይኸው መሣሪያ በጳጉሜ 2000 ዓ ም፣ በታላቅ ጉጉትና ፌስታ ነበረ ሥራውን እንዲጀምር የተደረገው። ይሁንና ከ 9 ቀናት በኋላ ሥራው ለ 14 ወራት ተቋርጦ እንደነበረ የሚታወስ ነው። እንደገና ተግባሩን የጀመረው፣ LHC ፣ ለቀጣይ ልዩ ምርምር ሲባል ፣ ባለፈው ታኅሳስ ሥራው ከተገታ ወዲህ እንደገና ፣ ካለፈው ወር አንስቶ ፣ ተግባሩን ማከናወን እንዲቀጥል ተደርጓል።

በሺ የሚቆጠሩት ሳይንቲስቶች ዓላማ፣ Higgs Boson የተሰኘውን ፣ ማለትም ከ 30 ዓመት ገደማ በፊት እስኮትላንዳዊው የፊዚክስ ምሁር ፒትር ሂግስ፣ በነባቤ ቃል፣ የፍጥረተ ዓለም መሠረት የመጨረሻ ኢምንት ቅንጣት ስለመሆኑ ያወሱትን ወይም «የአግዚአብሔር ቅንጣት»(“God Particle”)የሚባለውን ለማግኘትና ቅንጣቶች እንዴት ቁስ አካልን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ማወቅ ነው ።

ይህ በአንዲህ እንዳለ፣ ምድራችን ጥቁር ጉድጓድ በሚሰኘው የተፈጥሮ ሰልቃጭ ኃይል ተመጥጣ ትጠፋለችና በዓለም ውስጥ እጅግ ኃይለኛው የአቶም ቅንጣት ጨፍላቂው መሣሪያ (Large Hadron Collider)ተግባር እንዲገታ፣ ካርልስሩኸ ለሚገኘው የጀርመን ከፍተኛ ህገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት አቤት! ያሉት አንዲት ጀርመናዊት ሴት፣ ላቀረቡት ክስ እንደርሳቸው ፍላጎት አወንታዊ ብይን ሳይሰጥ ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ፣ ክስ አቅራቢዋ፣ ሥጋታቸውን በሚገባ የሚያብራራ አሳማኝ ምክንያት አላቀረቡም በማለት ነው፣ ጥያቄአቸውን ውድቅ ያደረገው።

ሴትዮዋ፣ የጀርመን መንግሥት በ CERN የሚካሄደውን ምርምር እንዲያስቆም በኮሎኝ ከተማ ለአንድ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ማመልከቻም ፣ ተመሳሳይ ዕጣ ነው የገጠመው።

ከሳሽ፣ አሁን የሚገኙት በጀርመን ሀገር አለመሆኑም ተገልጿል።

ሌሎች የ CERN ተጻራሪዎችም ፣ የኅዋ ጥቁር ጉድጓድ እጅግ ኃይለኛ የስበት ኃይል ምድራችንን ይሰለቅጣታል ወይም በነባቤ-ቃል የሚታሰብ አንድ ልዩ ቅንጣት፣ ምድርን ወደ ሙጫነት ሊለውጣት ይችላል የሚለውን ሥጋታቸውን በማንጸባረቅ፣ ምርምሩን ለማስቆም አስበው አንደነበረ ተመልክቷል ::

ቁስ አካል ፣ ሥር መሠረቱ ፣ ምንጩ፣ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ለማግኘት ፣ ጀርመናውያን የበኩላቸውን ምርምር ሲያካሂዱ 50 ዓመታት አልፈዋል። Deutsches Elektronen Synchrotron(DESY) እየተባለ የሚጠራው ተቋም ከ 50 ዓመት በፊት ሐምበርግ ውስጥ በአንድ የቀድሞ አኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ 300 ሜትር ርዝማኔ ባለው መሿለኪያ ውስጥ መጀመሩን ፣ ያኔ፣ የተቋሙ ባልደረባ በመሆን ሥራውን ያካሂዱ የነበሩት የፊዚክስ ሊቅ Erich Lohrmann ፣ አሜሪካውያን በዚህ የምርምር ዘርፍ ብዙ ከገፉ በኋላ ነበረ፣ አውሮፓውያን የተነሣሡት ይላሉ።

«አውሮፓውያን እኩል ለመራመድ ሲሉ ነው CERN ን ያቋቋሙት ፣ ከዚያም የ DESY ተቋም ቀጠለ።»

ከ 50 ዓመት ገደማ በፊት ያኔ አዲስ በተቋቋመችው የጀርመን ፌደራል ሪፓብሊክ ፣ መሠረታዊ የምርምር ተቋም ለመገንባት ተችሎ ነበር። የኤሌክትሮንስ ማሽከርከሪያው መሣሪያ 100 ሚሊዮን ማርክ ያስወጣ ሲሆን ፣ ያኔ ብዛቱ «ጉድ!» ያሰኘ እንደነበረም የመጀመሪያው የተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ቪሊባልድ የንችከ ያስታውሳሉ።

«ገንዘቡን ለሥራ በማዋሉረገድ ከባድ እንደሚሆን እንገነዘብ ነበር። ፕሮጀክቱ ከተለመደው በላቀ ሁኔታ ከባድ ወጪ የሚያስወጣ ነበረ። መሠረታዊውን የምርምር ተግባር የሆነው ሆኖ፣ በልበ ሙሉነት ማከናወን ነበረብን። አለበለዚያ ሥራውን ለመምራት ከቶውንም የማይችል በሆነብን ነበር።»

እ ጎ አ ታኅሳስ 18 ቀን 1959 ዓ ም፣ በሃምበርግ ማዘጋጃ ቤት ተመዝግቦ ሥራውን የጀመረው DESY በአሁኑ ጊዜ በውጭ ሃገራት ለምሳሌ ያህል CERN ንን በመሳሰሉ ተቋማት በሚካሄድ ምርምር ይተባበራል። ከ 2 ዓመት በፊት በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ሞቃት ወራት በዚያው በሃምበርግ ሌላ ዐቢይ የምርምር መሣሪያ፣ የአውሮፓውያን ዘመናዊ የ«ራጅ» መሣሪያ መተከሉና በጀርመን የትምህርትና የምርምር ሚንስትር ወ/ሮ አኔተ ሻቫን ተመርቆ መከፈቱ ይታወሳል። 3 ኪሎሜትር ያህል ርዝማኔ ያለው ይኸው ልዩ የምርምር ማእከል አንድ ቢልዮን ያህል ዩውሮ ማስወጣቱ የሚታወስ ነው።

ይኸው የምርምር ጣቢያ ሥራውን በትክክል የሚጀምረው እ ጎ አ በ 2014 ዓ ም ይሆናል። ሥራው ፣ በአቶም ፊዚክስ ሳይሆን በቁስ አካል ፣ በሥነ-ህይወትና በረቂቅ ሥነ ቴክኒክ (ናኖቴክኖሎጂ) ላይ ይሆናልይሆናል የሚያተኩረው።

አኔተ ሻቫን---

«መሠረቱ ተጥሏል። እዚህ የተገነባው ፤ በዓለም ውስጥ እፁብ ድንቅ ነው።»

ተክሌ የኋላ
ነጋሽ መሐመድ