1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የቀጠለው የኬንያ ተቃውሞ

ሐሙስ፣ ሰኔ 20 2016

ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ሀገር አቀፍ ተቃውሞ የቀሰቀሰውን የቀረጥ ሕግ ውድቅ ቢያደርጉም በኬንያ የተጠናከረ ተቃውሞ ተጠርቷል። ሕጉን ተቃወመው አደባባይ ከወጡት የተወሰኑት መሰረዙ ለጥያቄያቸው መልስ ነው በሚል በዛሬው ተቃውሞ እንደማይሳተፉ ቢገልጹም ገሚሱ ግን ግባቸው የፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ከሥልጣን መነሳት መሆኑን በመግለጽ በተቃውሟቸው ገፍተዋል።

https://p.dw.com/p/4hbIP
ናይሮቢ ተቃውሞ
በዛሬው ዕለት ሐሙስ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓም ናይሮቢ ከተማ ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች ከፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ሲሸሹምስል Daniel Irungu/EPA

የቀጠለው የኬንያ ተቃውሞ

 

«በእራሴ እና በፓርላማ አባላት እንዲሁም በበርካታ ኬንያውያን ስም በዚህ በጣም ባልተገባ ሁኔታ የሚወዷቸውን ላጡ ቤተሰቦች ሃዘኔን እገልጻለሁ። አምናለሁ እናም በዚህ በ2024ቱ የፋይናንስ ሕግ ላይ አልፈርምም። ይህን ተከትሎም ሕጉ ውድቅ እንዲሆን የጋራ አቋማችን እንዲሆን ከእነዚህ የፓርላማ አባላት ጋር ተስማምቻለሁ።»

ኬንያውያን ከዳር እስከዳር በአንድ ቆመው የተቃውሞ ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ የዜጎችን ቁጣ የቀሰቀሰው የቀረጥ ጭማሪ ሕግ ትናንት በፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ውድቅ ቢደረግም ዛሬም ግን የተቃውሞው እንቅስቃሴ መቀጠሉ እየተነገረ ነው። ሩቶ አክለውም የመንግሥትን በጀት በተመለከተ የባለሥልጣናት የጤናም ሆነ የመኪና ግዢ እንዲሁም ከስብሰባዎች ጋር በተገናኘ የሚደረጉ ወጪዎች ላይ ቅነሳ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት። እንዲህ ባሉ የሁሉንም ዜጎች በር በሚያንኳኩ ጉዳዮች ላይም መንግሥታቸው ሕዝቡን የማወያየት ኃላፊነት እንዳለውም አንስተዋል።

የቀጠለው ተቃውሞ

ዛሬም ኬንያውያን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ዜጎችን ለከፋ የኑሮ ውድነት ዳርጓል ያሉትን የፕሬዝደንት ሩቶን አስተዳደር መሞገታቸውን ቀጥለዋል። በዋና ከተማ ናይሮቢ ብዛት ያላቸው የኬንያ ጦር ኃይል አባላት ጸጥታ ለማስከበር ተሰማርቷል። በእነሱ ጥበቃ የተዘጉ መንገዶች ሲኖሩ፤ የከተማዋ የንግድ ሱቆችም በተመሳሳይ አለመከፈታቸን ከስፍራው የወጡ የቪዲዮ ዘገባዎች ያመለክታሉ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አወዛጋቢው የቀረጥ ሕግ መሰረዙን ፕሬዝደንቱ ለሕዝቡ በይፋ ካሳወቁ በኋላ አንዳንዶች ተቃውሞው ግቡን መትቷል በሚል ዳግም ሰልፍ አያስፈልግም ሲሉ ገሚሱ ፕሬዝደንቱ ከሥልጣናቸው ካልተነሱ ወደቤታቸው እንደማይገቡ እየዛቱ ነው። ሰሞኑን አደባባይ ከወጣው ቁጥሩ አነስ ያለ ሕዝብም የተጠናከረውን የጸጥታ አስከባሪዎች ስምሪት ከቁብ ሳይዎጥር ዛሬም በናይሮቢ ጎዳናዎች ላይ ድምጹን ሊያሰማ ወጥቷል።

«ፕሬዝደንቴ እንዲሆኑ አልፈልግም፤ ሌላው ቀርቶ ለምን መረጥኳቸው ብዬም ተጸጽቻቸለሁ። መልቀቅ አለባቸው።» ትላለች ለተቃውሞ ከወጡት ወጣቶች አንዷ። ሌላዋም ቀጠለች።

«ምክንያቱም እራሳቸውን ብቻ እያበለጸጉ ነው፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አብዛኛው ኬንያዊ በድህነት እየማቀቀ ነው። ዛሬም ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ዜጎች አሉ፤ የጤና አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ አሉ።»

ፖሊስ ዛሬም ናይሮቢ ከተማ ውስጥ የወጡትን ሰልፈኞች ወደ ቤተመንግሥት እንዳይሄዱ ለመከላከል ፕላስቲክ ጥይት እና አስለቃሽ ጋዝ መተኮሱ ነው የተነገረው። ፖሊሶች ላይ ድንጋይ ወርውረዋል የተባሉ ቢያንስ ሰባት ሰዎችንም ማሰራቸው ተገልጿል።

የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ
የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያይም ሩቶ አወዛጋቢውን ሕግ ውድቅ ማድረጋቸውን ሲገልጹ ምስል atrick Ngugi/AP Photo/picture alliance

የኬንያውያን ቅሬታ

ኬንያውያን በዊልያም ሩቶ አስተዳደር ቃል የተገቡ መሠረታዊ ነገሮች እስካሁን ተግባራዊ አልተደረጉም ባዮች ናቸው። በፕሬዝደንት ሩቶ መንግሥት ቅር ከተሰኙት አንዱ ኬንያዊ ታክሲ ነጂ ጆን ንጉጊ ፕሬዝደንቱ ድምጽ የሰጣቸውን ሕዝብ በተራቸው ቢያደምጡት እንደሚበጅ ይናገራል።

«አየህ እሳቸው ሥልጣን ከያዙበት ከመጀመሪያዋ ቀን አንስተው ይህንን ያንን አድርጋለሁ ብለው ለሕዝብ ተናግረዋል። ሆኖም ግን አላደረጉም። አሁን እንደምታየው ፕሬዝደንት ሆነዋል፤ ነገር ግን እኛንም ማድመጥ ይኖርባቸዋል፤ ጩኸታችንን በተለይም ወጣቶችን ድምጽ መስማት አለባቸው። ይህ ተቃውሞ የወጣቶች ብቻም አይደለም፤ የወላጆቻችን፤ የአዛውንት ሴቶች ጭምር ነው።»

ሥልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ የነገሩንን ሁሉ አንዱንም ተግባራዊ አላደረጉም በሚል በፕሬዝደንቱ ላይ ቁጣቸውን ከሚገልጹት ኬንያውያን አንዱ ወደቤተመንግሥቱ መግቢያውን  እንደሰጠናቸው መውጫውም በእጃችን ነው ይላል።

«ለዚህ መንግሥት መንገር የምፈልገው መግቢያውን ሰጠንህ፤ መውጫውን ደግሞ እናሳይሃለን። ሚስተር ፕሬዝደንት! ሚስተር ፕሬዝደንት! ታየናለህ!»

የፀጥታ ኃይሎች የኃይል እርምጃ

እስካሁን ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው በጸጥታ ኃይሎች ጥቂት ሕይወታቸው ያለፈው ቁጥር በትክክል ባይታወቅም ፕሬዝደንቱ ትናንት በይፋ ስድስት ሰዎች ያለ አግባብ መገደላቸውን በመጥቀስ ድጋሚ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንደማይቀጥል ተናግረዋል። ሩቶ የሀገሪቱ ምክር ቤት አወዛጋቢውን የቀረጥ ሕግ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ተከትሎ ፓርላማውን ሳይቀር ሰብሮ እስከመግባት የጠነከረውን የሕዝቡን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የኬንያን ጦር ኃይል ሳይቀር ለግዳጅ እንደሚያሰማሩ ዝተው ነበር። በዛሬው ዕለት በምዕራባዊ ኬንያ በምትገኘው ሆና ባይ ከተማ ሰልፍ ወጥተው ጉዳት የደረሰባቸው ሰባት ሰዎች ሀኪም ቤት መወሰዳቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።  

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋኅ መሐመድ