የቀጠለው የቻርልስ ቴይለር ችሎት | ኢትዮጵያ | DW | 18.07.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የቀጠለው የቻርልስ ቴይለር ችሎት

በጦር እና በስብዕና አንጻር በተፈጸመ ወንጀል ሰበብ የተከሰሱት የላይቤርያ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር በኔዘርላንድስ የ ዘ ሄግ ከተማ በተሰየመው ልዩ የሲየራ ልዮን የጦር ወንጀል ተመልካች ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በዚህ ሳምንት ችሎት ቀርበው ሰነበቱ።

default

ቴይለር በችሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ቃላቸውን ሰጥተዋል። የሲየራ ልዮን ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የቴይለር ችሎትን በጸጥታ ሰበብ ነው ወንጀሉ ከተፈጸመባት ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ርቆ በዘ ሄግ መመልከት የያዘው።

የስድሳ አንድ ዓመቱ ቴይለር እአአ ከሰኔ 2007 ዓ.ም ወዲህ በእስራት ዘ ሄግ ይገኛሉ።

Prozess gegen Charles Taylor in Den Haag


ብዙዎች ቴይለርን ተወዳዳሪ እንደሌላቸው ጭራቅ ይቆጥሩዋቸዋል፤ አንዳንዶች የአፍሪቃ ሚሎሴቪች ይሉዋቸዋል። ሌሎች ደግሞ በአፍሪቃ ከሚካሄዱት ብዙዎቹ ጦርነቶች ትርፍ ካካበቱት መካከል እንደ አንዱ ይመለከቱዋቸዋል።
ሀገራቸውን ላይቤርያ ወደርስበርስ ጦርነት ማጥ ውስጥ ያስገቡት ቻርልስ ቴይለር በአስራ አንድ የተለያዩ ነጥቦች፡ ማለትም በነፍስ ግድያ፡ በቁም ስቅል ማሳየት፡ በክብረ ንጽህና መድፈር፡ በወሲባዊ ብዝበዛ፡ ህጻናትን ለውጊያ በመመልመሉና በጎረቤት ሲየራ ልዮን እጅና እግር ይቆርጡ በነበረው ዘግናኙ የጭካኔ ተግባራቸው ሲቭሉን ህዝብ ሆን ብሎ ያሸበሩትን እጅግ ይፈሩ ለነበሩት የተባበረው ዓብዮታዊ ግንባር ዓማጽያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በመስጠታቸውና በምላሹ ዓማጽያኑ ማዕድኑን አልማዝ እንዲያቀርቡላቸው ያደርጉ ነበር በሚል ነው የልዩው ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ስቴፈን ራፕ ክስ የመሰረቱባቸው። የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር በዚሁ በአንድ አፍሪቃዊ የመንግስት መሪ ላይ በሚካሄደው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ችሎት ላይ በአንጻራቸው የተሰነዘረውን የጭካኔ ተግባር በጠቅላላ በዚህ ሳምንት ቃላቸውን በልዩው ፍርድ ቤት ፊት በሰጡበት ጊዜ በድጋሚ ሀሰት ሲሉ አጣጥለውታል። አስራ አራት ልጆችና የልጅ ልጆች እንዳሉዋቸው የገለጹት ቴይለር ለስብዕና ፍቅር ያላቸውና ዕድሜአቸውን ሙሉ ለፍትህና ለትክክለኛ አሰራር የታገሉ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት።
« ጥፋተኛ አይደለሁም። »
ዋነኛው ብሪታንያዊው ጠበቃ ከርትነይ ግሪፊትስ በሲየራ ልዮን እአአ ከ1991 እስከ 2002 ዓም በተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ወቅት የተፈጸመውን እጅግ አስከፊ የጦር ወንጀልን እንዲመለከት ለተቋቋመው እና የቻርልስ ቴይለርን ችሎት በዘ ሄግ ኔዘርላንድስ ለሚመለከተው የጦር ወንጀል ተመልካች ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ደምበኛቸው ጥፋተኛ እንዳልሆኑ አስታውቀዋል። ሰዎች ሳይወግኑ በቴይለር አንጻር የተሰነዘረውን ክስ በትክክለኛ መንገድ እንዲመለከቱትም ግሪፊትስ አክለው ተማጽነዋል።
«ብዙዎች በአንጻራቸው አስቀድመው ስለፈረዱዋቸው ሚስተር ቴይለር ጉዳያቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት ብዙ ችግር እንደሚገጥማቸው ተረድተነዋል። ይሁንና፡ ከህዝብ የምንጠይቀው የሚቀርቡ መረጃዎችን ባልወገነ መንገድ እንዲመለከቱና ቴይለር የሚሉትን እንዲያደምቱ ነው የምንጠይቀው። » የቀድሞው የላይቤርያ ፕሬዚደንት በጦር ወንጀል እንዳልተሳተፉ፡ በአንጻሩ ባካባቢው፡ በተለይ ከሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ የሚበልጥ ህዝብ ለተገአለባት ሲየራ ልዮን ሰላም ለማውረድ ጥረት እንዳደረጉ እና በሲየራ ልዮን ይንቀሳቀሱ በነበሩት የተባበረው ዓብዮታዊ ግንባር ዓማጽያንም ላይ ፍጹም ተጽዕኖ እንዳላሳረፉ ጠበቃቸው ግሪፊትስ እንዲህ ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
« ህጻናትን በውትድርና ተግባር የሚሰማሩበት ተግባር የቻርልስ ቴይለር ፈጠራ አይደለም። »
የልዩው ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ስቴፈን ራፕ እስካለፈው የካቲት መጨረሻ ቴይለር ይረዱዋቸው ነበር የተባሉት የተባበረው ዓብዮታዊ ግንባር ዓማጽያንን የፈጸሙት የጭካኔ ተግባር ምን ያህል አስከፊ እንደነበርና ቴይለር ለዚሁ ተጠያቂ እንደሆኑ ለማሳየት በጠሩዋቸው ዘጠና አንድ ምስክሮችት አማካይነት ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ የክስ ማስረጃቸውን አጠናቀዋል።
« ዘጠና አንድ በብዛት ከሲየራ ልዮንና ከላይቤርያ የመጡ ምስክሮችን አቅርበናልል። ከነዚህም ሰላሳ ሰባቱ በቻርልስ ቴይለር እና በትዕዛዝ በሲየራ ልዮን በትዕዛዝ በተፈጸሙት አስከፊ የጭካኔ ተግባራት መካከል ግንኙነት መኖሩን መስክረዋል። እና የተከሳሽ ጠበቆች ለዚሁ ለቀረበው ማስረጃ አንጻራዊ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። »
የቴይለር ጠበቃ ግን ደምበኛቸው ራሳቸውን ከቀረበባቸው ክስ ነጻ እንደሚያወጡ በርግጠኝነት ተናግረዋል። ዓቃቤ ህግ ራፕ የጠበቃውን ግሪፊትስ አስተሳሰብ አይጋሩትም።
« ይህን እኛ ልንተነብይ አንችልም። ይህን ስል ግን ጉዳያችንን የሚደግፈውን ማስረጃ ቃል እንደገባነውአቅርበናል። ምንም እንኳን ምስክሮቻችን አደጋ ላይ ሊወድቁ ቢችሉምና ለወደፊቱ ስጋት ቢኖራቸውም ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኟ በመሆናቸው በጣም ተደስተናል። »
በሲየራ ልዮን ለተካሄደው የጭካኔ ተግባር ቻርልስ ቴይለር ብቸኛው ተጠያቂ አለመሆናቸው ይታወቃል። ይሁንና፡ የተባበረው ዓብዮታዊ መሪ ፎዳይ ሳንኮህ በእስር ቤት እያሉ በመሞታቸው፡ ሌሎችም የቡድኑ ወንጀለኞች አንድም በመሸሸጋቸው ወይም ሳይሞቱ ሞቱ በመባሉ ሰበብ ፍርድ ፊት ቀርበው ለፈጸሙት ወንጀል በቀጥታ ተጠያቂ ባለመሆናቸው፡ የሲየራ ልዮን ዜጎች አሁን በ ዘ ሄግ የሚካሄደውን የቻርልስ ቴይለርን ችሎት በቅርብ በመከታተል ላይ ይገኛሉ። ይኸው ችሎት ትልቅ ትርጓሜ መያዙን በመዲና ፍሪታውን ተሰይሞ የነበረው ልዩ የሲየራ ልዮን ጦር ወንጀል ተምካች ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ ፒተር አንደርሰን ገልጸዋል።
« በዚህ አካባቢ ለብዙ ጊዜ ትልቅ ስልጣን ያላቸው ግለሰቦች ቅጣት ይደርስብናል ብለው አይሰጉም ነበር። የሚነካቸው አልነበረምና። አሁን በልዩው ፍርድ ቤት አማካይነት አሁን ይህንን አሰራር ቀይረናል። ማንም ብትሆን፡በፍርድ ልትቀጣ ትችላለህ፤ የሀገር መሪ ብትሆንም። በዚህ ሀገር ወንጀልን በመታገሉ ረገድ ትልቅ መሻሻል እያደረግን እንገኛለን። »
የቻርልስ ቴይለር ጠበቃ ምስክሮቹን የሚያቀርብበት ጊዜ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር ሊወስድ እንደሚችል ተገምቶዋል። የቀድሞው የላይቤርያ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለርም ጠበቆቻቸው ከቀረበባቸው ክስ ነጻ እንደሚያደርጉዋቸው እርግጠኛ መሆናቸው ተገልጾዋል። ይህ ተስፋቸው ገሀድ መሆን መቻሉ ግን እስኪታወቅ ድረስ ገና ብዙ ወራት ማለፋቸው እንደማይቀር ነው ከፍርድ ቤቱ አካባቢ የተገኙ ምንጮች የሚያመለክቱት።

አርያም ተክሌ/DW/ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች