የቀጠለው የቦይንግ 737 የመረጃ ሳጥን ምርመራ | ኢትዮጵያ | DW | 20.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የቀጠለው የቦይንግ 737 የመረጃ ሳጥን ምርመራ

ወደ ናይሮቢ ለመጓዝ  ከአዲስ አበባው ቦሌ  ዓለም ዓቀፍ  አውሮፕላን  ማረፊያ  ተነስቶ  ቢሾፍቱ አቅራቢያ  የተከሰከሰው  የኢትዮጵያ  አየር  መንገድ  አውሮፕላን  የመረጃ ሳጥን  የያዛቸው መረጃዎች በተሳካ ሁኔታ መገልበጣቸው ተነግሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:01

«የመጀመሪያው ደረጃ ዘገባ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል»

በእስካሁኑ የምርመራ ሂደት የተሰበሰቡ መረጃዎች  የአደጋው መንስኤ ከኢንዶኔዢያው የላየን አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ጋር አንዳንድ ግልጽ መመሳሰሎች መገኘታቸውም ተገልጿል። የኢትዮጵያ  የትራንስፖርት  ሚኒስትር  ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ  በተለይ  ለ«DW» እንደገለፁት የምርመራው የመጀመሪያው ደረጃ ዘገባ እና የሚገኙ ተጨማሪ ውጤቶች  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል። በአደጋው አስከፊነትም የሟቾችን አስክሬን በ «DNA» ምርመራ የመለየቱ ሂደት እስከ 6 ወር ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም ገልጸዋል። አክለውም ሚኒስትሯ ለቤተሰቦች እና ሕጋዊ አካላት የአደጋው ሰለባዎችን ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አዘጋጅቶ መስጠት ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ፤ የሕይወት ኢንሹራንስ ጉዳዮችም ዓለም አቀፍ አሰራሮችን ተከትለው እንደሚፈጸሙም አስታውቀዋል።   

ከጥቂት ቀናት በፊት ለ 157 ተሳፋሪዎች አሰቃቂ ሞት መንስኤ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አሳዛኝ የአደጋ ክስተት ዛሬም ድረስ የዓለም ህዝብ እና መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ቀጥሏል:: በተለይም አደጋው ኢንዶኔዥያ ላይ ተከስክሶ የ 189 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው የላየን አየር መንገድ ቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይነት አለው የሚለው መረጃ በፌደራል አቪየሽን አስተዳደር በኩል መሰራጨቱ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያውን ቦይንግ ጨምሮ በርካታ አገራት ተመሳሳይ ስሪት የሆኑ የቦይንግ አውሮፕላኖች ከበረራ እንዲታገዱ እስከማድረግ ደርሰዋል:: የአውሮፕላኑን አካል ጨምሮ የሟቾችን አስክሬን ማግኘት እና መለየት በሚቸግር ሁኔታ አሰቃቂ አደጋ ከደረሰ ከአንድ ቀን ብርቱ ፍለጋ በኋላ የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ አንዳች ፍንጭ ይሰጣል ተብሎ የሚገመተው ጥቁሩ የመረጃ ሰንዱቅ ማለትም ብላክ ቦክስ ከሁለት ቀናት ፍለጋ በኋላ መገኘቱ አንዳች ተስፋን ቢፈነጥቅም በአደጋው አስከፊነት ምክንያት መጠነኛ ጉዳት ደርሶበታል መባሉ ደግሞ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል:: የአንድን አውሮፕላን የበረራዉን አጠቃላይ ሁኔታ ከፍታውን ፍጥነቱን አቅጣጫውን አውሮፕላኑ በምን ሁኔታ እንደነበረ እና ሌሎችንም ዝርዝር መረጃዎች የሚገልጽ ዳታ እና የአብራሪውን የመልዕክት ልውውጥ ድምጾች ቀርጸው እና መዝግበው የሚይዙት የጥቁሩ የመረጃ ሰንዱቅ ወይም ብላክ ቦክስ ክፍሎች በአደጋ ጊዜ መንስኤውን ለመመርመር በሚደረገው ሂደት እጅግ ተፈላጊ መሆናቸው ይታወቃል::

:  ከአዲስ አበባው ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ሲበር ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መረጃ ሳጥን ለምርመራ ወደ ፈረንሳይ መላኩን ከሰሞኑ መንግሥት ገልጾ ነበር:: የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በተለይ ለ DW ይፋ እንዳደረጉት ለምርመራ የተላከው አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን መረጃ ሳጥን እና የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል መቅረፀ ድምፅ ሙሉ መረጃው በተሳካ ሁኔታ መገልበጥ መቻሉ የታወቀ ሲሆን በቀጣይ በሚደረግ ዝርዝር ትንተና መሰረትም የሚገኘው ቀጣይ ውጤት በአንድ ወር ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ነው ያሉት:: ሚኒስትሯ በእስካሁኑ የምርመራ ሂደት የኢትዮጵያው አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ
መንስኤ ከኢንዶኔዥያ ጃካርታ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከተከሰከሰው የላየን አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ጋር የሚመሳሰል ሆኖ መገኘቱንም ይፋ አድርገዋል:: የበረራ መመዝገቢያ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያም ሆነ በላየን አየር መንገዶች የአውሮፕላን አደጋዎች ላይ  ተመሳሳይ ምልክቶች እንደተስተዋለባቸው ሚኒስትሯ ጨምረው አብራርተዋል:: የመረጃ ሳጥኑ የያዛቸው ልዩ ልዩ መረጃዎችም በሙሉ በተሳካ ሁኔታ ተገልብጠው ለኢትዮጵያ መንግስት መሰጠታቸው ነው የተገለጸው:: የመጀመሪያው ደረጃ ሪፖርት እና የሚገኙ ተጨማሪ ውጤቶችም  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል::
ከአሁኑ ቀደምም እንደ ጎርጎራውያን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET 409 ከቤሩት አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ነድዶ ሜዲትራኒያን ላይ በመውደቁ 89 መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ማለቃቸው ይታወሳል። በወቅቱ የሊባኖስ የምርመራ ቡድን የበረራ ስህተት ለተፈጠረው አደጋ መንስኤ ነው ቢልም በአንጻሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኑን የፍንዳታ አደጋ እንደደረሰበት በመግለጽ የአደጋውን አጣሪ ቡድኑን የምርመራ ውጤት ሲያጣጥለው መቆየቱ ይታወሳል::በዚሁ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሊባኖሱ አደጋ የምርመራውን ሂደት ባከናወነችው ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ደስተኛ አልነበረችም ነው የሚባለው:: ይህ ከሆነ የአሁኑን የቴክኒክ ምርመራ ዳግም ለምን ለፈረንሳይ መስጠት አስፈላጊ ሆነ ? እንደሚባለው ጀርመን የመረጃ ሳጥኑን መመርመሪያ ሶፍትዌሩ እንደሌላት በመግለጿ ወይስ ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ ጋር በጀመረችው የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ምክንያት? " የአደጋውን መንስኤ የምርመራ ሂደት በተሳካ መልኩ እንዲከናወን እና ለአቪየሽን ኢንዱስትሪውም ዳግም ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ በማድረግ ረገድ አስተማሪ በሆነ መልኩ ውጤት እንዲኖረው ለማድረግ ካለን ጽኑ ፍላጎት አንጻር ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ብሎም ከቅርበት አኳያ የትኞቹ ሃገራት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ፈጣን በሆነ ጊዜ እና አስተማማኝ በሆኑ ባለሙያዎች ምርመራውን ሊያግዙን ይችላሉ የሚለው ቀዳሚው ጥያቄያችን ነበር:: በደረስንበት ጥናት መሰረትም ፈረንሳይ የተሻለች ሆና ስላገኘናት ምርመራውን በሃላፊነት እንዲያከናውን ለፈረንስዩ የበረራ ደኅንነት ምርመራ ባለሥልጣን ሰተናል:: ያንንም በማድረጋችን ደግሞ የምንፈልገውን ጠቃሚ መረጃ በፍጥነት የማግኘቱ ውጥናችን ተሳክቶልናል" ብለዋል የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ::

በኢትዮጵያ የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ እንደ ኖርዌይ ያሉ ሃገራት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቻቸው ከበረራ በመታገዳቸው በደንበኞቻቸ ላይ ለደረሰው መጉላላት እና አየር መንገዶቻቸው ለገጠማቸው ኪሳራ የቦይንግ ካምፓኒን የካሳ ክፍያ የጠየቁበት ሁኔታ እንዳለ እየተሰማ ነው:: በኢትዮጵያስ በኩል በዚህ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም
በሟቾች የ DNA ማረጋገጫ የምርመራ ሂደት ለአደጋው ሰለባዎች ቤተሰቦች እና ህጋዊ ተቋማት የሟቾችን የምስክር ወረቀት አዘጋጅቶ የመስጠት ጉዳይ እንዲሁም ከሕይወት መድህን ዋስትና ኢንሹራንስ ጋር በተያያዘ ምን እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ነው ስንል ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር:: " ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ በተደጋጋሚ ከሚነሱልን ጥያቄዎች አንዱ ለቤተሰቦች እና ለሚመለከታቸው ሕጋዊ አካላት በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን በተመለከተ የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አዘጋጅቶ የመስጠቱ ሂደት ሲሆን መንግሥት ለጉዳዩ አጽንዖት በመስጠት ከጠቅላይ አቃቢ ህግ ጋር በመሆን ህጋዊ ሰነዶቹን ለሚመለከታቸው ሁሉ ከሁለት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደምንሰጥ አስታውቀናል:: ሟቾቹ ወደ 35 የሚጠጋ ሃገራት ዜጋ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እስካሁን የተገኙትንም አስክሬኖች ማንነት ለመለየት አዳጋች በመሆኑ በ DNA ምርመራ ለመለየት የተጀመረውን ስራ ለማቀላጠፍም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እና እምነት ከተጣለባቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው:: የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ጉዳዮችም ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና አሰራሮችን ተከትለው የሚፈጸሙ ይሆናል " ሲሉ ሚኒስትሯ አብራርተዋል::

የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙሊንበርግ በበኩላቸው የቦይንግ ካምፓኒ በአደጋው ዙሪያ በሚደረገው የምርመራ ሂደት አስፈላጊውን ትብብር እና ድጋፍ እንደሚሰጥ ነው የገለጹት። በአውሮጳ ህብረት በተለያዩ የዓለም ሃገራት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በዩናይትድስቴትስ እንደራሴዎች ጭምር በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ ተከትሎ ቦይንግ 737 ማክስ 8 እና 9 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ የበረራ አገልግሎት እንዲያቋርጡ ከፍተኛ ግፊት ሲደረግ ቆይቷል:: ከአሁን ቀደም ኢንዶኔዥያ ውስጥ ተከስክሶ የ 189 ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የላየን አየር መንገድ አውሮፕላን እና በቅርቡ ለ 157 ተሳፋሪዎች አሰቃቂ ሞት ምክንያት በሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ መካከል የሚመሳሰሉ አዲስ ማስረጃ እና ግልጽ የሳተላይት መረጃዎችን አግኝቻለው ያለው የፌደራል አቪየሽን አስተዳደርም የቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ እንዲታገዱ ነው ያሳሰበው :: ይህን ተከትሎም ግዙፉ የአሜሪካው ቦይንግ የአውሮፕላኖች አምራች ኩባንያ ቦይንግ 737 ማክስ 8 እና 9 የተሰኙ ከ 371 የሚልቁ አውሮፕላኖቹን በረራ እንዳያደርጉ በመጨረሻ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ተሰምቷል:: እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ከ 50 በላይ ሃገራት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ከበረራ ማገዳቸው ታውቋል:: የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስሯ ወይዘሮ ዳግማዊት እስካሁኑ የምርመራው ሂደት እንዲሳካ እና ቀልጣፋ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እና ትብብር ላደረገው የፈረንሳይ መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic