የቀጠለዉ የሱዳን ተቃዉሞ | አፍሪቃ | DW | 05.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቀጠለዉ የሱዳን ተቃዉሞ

ከወራት በፊት ኦማር አልበሽርን ከስልጣን ያስወገደዉ የሱዳን ህዝባዊ ተቃዉሞ ግጭትና ሞት እያስከተለ አሁንም ቀጥሏል። ይህን ተከትሎ  በስልጣን ላይ ያለዉ የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ከተቃዋሚ ሀይሎች ጋር ያለዉን ድርድር ወደጎን በማድረግ በትናንትናዉ ዕለት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:33

በፀጥታ ሀይሎች የተገደሉ የሟቾች ቁጥር 60 ደርሷል

ከወራት በፊት ኦማር አልበሽርን ከስልጣን ያስወገደዉ የሱዳን ህዝባዊ ተቃዉሞ ግጭትና ሞት እያስከተለ አሁንም ቀጥሏል። ይህን ተከትሎ  በስልጣን ላይ ያለዉ የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ከተቃዋሚ ሀይሎች ጋር ያለዉን ድርድር ወደጎን በማድረግ በትናንትናዉ ዕለት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቦ ነበር። በዛሬዉ ዕለት ደግሞ የእንነጋገር ጥሪ አቅርቧል። የተቃዋሚ ሀይሎች ግን ጥሪዉን አለመቀበላቸዉን እየገለፁ ነዉ።
ለ3 ዓሥርተ ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩትን ኦማር አልበሽርን ያለፈዉ ሚያዚያ 03 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ከስልጣን ያወረደዉ የሱዳን  ህዝባዊ ተቃዉሞ  አሁንም ቀጥሏል። አልበሽርን  ተክቶ  በሀገሪቱ  ስልጣኑን  የተቆጣጠረዉን  ወታደራዊ  የሽግግር መንግስትን ተቃዉመዉ አዉራ ጎዳናዎችን የሚያጨናንቁ  የተቃዉሞ ሰልፈኞች አልበሽር ከወረዱ ከወራት በኋላም ቀጥለዋል። የሱዳን የሰራተኞች  ማኅበርን  ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩት  ይህ ተቃውሞ  ወታደራዊ  የሽግግር መንግስቱ  በሲቪል አስተዳደር እንዲተካ  የሚጠይቅ ሲሆን፤ የሱዳን የፀጥታ ሀይሎች ተቃዉሞዉን ለመበተን በሚያደርጉት ተኩስ የሚሞተዉ ሰላማዊ ሰዉ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጌዜ እየጨመረ መጥቷል። በዚህ ሁኔታ በሱዳን የጦር የኃይል የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር ሰሞኑን  በካርቱም አደባባይ የተገደሉትን 20 ሰዎች ጨምሮ የሟቶች ቁጥር ወደ 60 ማሻቀቡን የጀርመኑ የዜና ወኪል በዛሬዉ ዕለት ዘግቧል።


የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ በፈጸሙት በዚህ ጥቃት ወታደራዊ  የሽግግር መንግስትቱ  በሀገር ዉስጥም ይሁን በዓለማቀፉ ህበረሰብ  ዘንድ ዉግዘት እየደረሰበት ይገኛል።
ይህንን ተከትሎ ምክር ቤቱ  ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ሲያደርገው የነበረውን ድርድር   በመተው በዘጠኝ ወራት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ  በትናንትናዉ ዕለት ጥሪ አቅርቦ ነበር። ያም ሆኖ ግን ተቃዉሞዉ ቀጥሏል። የኢድ አልፈጥር በዓል እየተከበረ በነበረበት በትናንትናዉ ዕለት ሳይቀር የካርቱም አደባባይ የሽግግር መንግስቱን በሚያወግዙ ሰልፈኞች ተጥለቅልቆ ነዉ የዋለዉ።
በዉስጥና  በዉጭ ጫና የበረታበት የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ-መንበር አብዱል ፋታኅ  አል-ቡርሐን፤ በዛሬዉ ዕለት በሀገራቸዉ የቴሌዥን ጣቢያ ቀርበዉ በሰጡት መግለጫ ደግሞ  ከብሄራዊ ጥቅም ባሻገር  በማንኛዉም ጉዳይ  ከተቃዋሚዎች ጋር  ለመነጋገር  መንግስታቸዉ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል።
«ሰዎች ተቀምጠው ተቃውሟቸውን ሲገልጹባቸው የነበሩ አደባባዮች እና ቦታዎች ዐቢይ ኹነቶችን አስተናግደዋል። እነዚህ የህዝቡ ስሜቶች እና ማኅበራዊ ሕይወቱ የታየባቸው ድርጊቶች የሱዳኖችን ባህል እና የማንነታቸውን እውነተኛ ጥልቀት አሳይተዋል። እኛ በሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤት ያለን፣ ለሌላ ዓላማ ሳይሆን ለህዝቡ ጥቅም ስንል የሱዳን አብዮትን ፍላጎቶች በተለያየ መልኩ ሊገልጽ የሚችለውን የህጋዊ አስተዳደር ምሥረታን እውን ለማድረግ ለድርድር እጃችንን ዘርግተናል። መእመመልካሙን ሁሉ እመኛለሁ።»  በማለት ነበር  ባለስልጣኑ የገለጹት።
 የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ-መንበር አብዱል ፋታኅ  አል-ቡርሐን ከእንነጋገር ባሻገር በፀጥታ ሀይሎች ለደረሰዉ ጥቃትም ይቅርታ ጠይቀዋል።


«ባለፉት ጥቂት ቀናት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰኑ ስጋቶችንና አስቸጋሪ የፀጥታ ሁኔታንና  የደህንነት ስጋቶችን ለመቋቋም  ባደረገጉጓቸዉ ጥረቶች ሳቢያ  አሳዛኝ ሁነቶችን ተመልክተናል። ጥቃት የደረሰባቸዉ ሰዎች ሲወድቁና ሲጎዱ ተመልክተን አዝነናል። ለተከሰተዉ ነገር ይቅርታ እንጠይቃለን። ለሞቱት ሰማዕታት ነብሶችና የቆሰሉትም በቶሎ እንዲያገግሙ እንፀልያለን።»
የወታደራዊ ባለስልጣኑ የይቅርታም ይሁን የእንነጋገር  ጥሪ ግን አወንታዊ ምላሽ ያገኘ አይመስልም። የሱዳን የሰራተኛ ማህበርም ይሁን ሌሎች በተቃዉሞ ዉስጥ ያሉ ሀይሎች ከሽግግሩ መንግሥቱ  ምንም አይነት ንግግር እንደማይፈልጉ ነገር ግን ሥልጣኑን እንዲለቅ እየወተወቱ  ነዉ። ከሁለት ቀናት በፊት አንድ የ17 ዓመት ወጣትን  የፀጥታ ሀይሎች  በጥይት ሲመቱት እንደ ተመለከተ የሚናገር አንድ የካርቱም ከተማ ነዋሪ እንደሚለዉም ሰላምና መረጋጋት የሚመጣዉ የወታደራዊ ሹማምንቱ ከስልጣን ሲወርዱ ብቻ ነዉ።
«ትግላችን እንቀጥላለን። እናዉቃለን ጉዞዉ ቀላል አይደለም። ነገር ግን  በሱዳን ህዝብ እንተማመናለን። እኛ የተባበርን ነን። ወታደራዊ መንግስት እንዲመራን አንፈልግም። ይኽን አጋጣሚ በመጠቀም ለወታደራዊ ባለስልጣናቱ በግልፅ ማስተላለፍ የምፈልገዉ መልዕክት ለሰላም ለፍትኅና ለለዉጥ ሲባል በተቻለ ፍጥነት ስልጣኑን ይልቀቅ።» ብለዋል።
በሱዳን ከተቃዉሞ አመፁ ጋር ተያይዞ ከተገደሉ ሰዎች በተጨማሪ በርካቶች ለእስር መዳረጋቸዉ  ይነገራል። በዛሬዉ ዕለትም በቅርቡ ከስደት የተመለሱት የሱዳን ህዝቦች የነፃነት ንቅናቄ አማፂ ቡድን መሪ  ያሲር አማን  በሱዳን የፀጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን የንቅናቄዉ ቃል አቀባይ ገልፀዋል። እናም በሀገሪቱ የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞና ቀዉስ ማቆሚያ ያለዉ አይመስልም። 

ፀሐይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic