የቀድሞ የሊሴ ተማሪዎች ግንኙነት | ወጣቶች | DW | 17.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

የቀድሞ የሊሴ ተማሪዎች ግንኙነት

ከትምህርት ቤት ቆይታቸውም በኋላ የሊሴ ተማሪዎች እንደ ቤተሰብ ግንኙነታቸውን አጥብቀው ለአመታት ያቆያሉ። እንዴት? የሊሴ ትምህርት ቤትንስ ምን ለየት ያደርገዋል?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:59

የሊሴ ተማሪዎች

ሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የሚኖሩ የሊሴ ገብረ ማርያም የቀድሞ ተማሪዎች ለየት ባለ መልኩ መልሰው የሚገናኙበትን መንገድ ለረዥም ጊዜ ከተመካከሩ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 2 ቀን 2010 ዓም ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩት ተገናኝተዋል። ዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደውን ስብሰባ ወይም ድግስ  ካስተባበሩት አንዱ የሆኑት ዮፍታሄ ገብሩ ከስብሰባቸው በፊት እንደገለፁልን የመልሶ ግንኙነቱ አላማ በአንድ በኩል ያሳለፉትን ጊዜ መለስ ብሎ ለማስታወስ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለቀድሞ አስተማሪዎቻቸው ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደሆነ ገልጸውልናል።
ተማሪዎቹ የተሰባሰቡት በፌስ ቡክ አማካኝነት ነው። የሊሴ ተማሪዎች ይህን አይነት ድግስ ሲያዘጋጁ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም። ከሁለት ዓመት በፊት በነበራቸው ስብሰባ 600 የሚጠጉ የቀድሞ ተማሪዎች አዲስ አበባ ላይ ተገኝተዋል። በዚህም ዓመት በርካቶች አዲስ አበባ ላይ እንደሚሰባሰቡ ከአስተባባሪዎቹ አንዷ የሆነችው ፂዎን ባህሩ ተስፋ አላት። ምክንያቱም የዘንድሮው ግንኙነት ከመገናኘት ያለፈ አላማ አለው።ፂዎን 24 ዓመቷ ነው። በዛሬው ምሽት የድሮ አብሯደጎቿን መልሶ ማግኘት እና የድሮዎቹንም መተዋወቅ ትሻለች። 


እኢአ በ1947 ዓም አዲስ አበባ ላይ የተመሰረተው አለም አቀፉ የፈረንሳይ ትምህርት ቤት በርካታ ተማሪዎችን አስተምሮ ጥሩ ቦታ እንዳደረሰ ይነገርለታል። በዝነኛው ትምህርት ቤት ማንኛውም ፈረንሳይኛ መናገር የሚችል እና የሚፈልግ መማር ይችላል። ክፍያው እንደ እየዜግነቱ ይለያያል። ኢትዮጵያውያን 78 000 ብር ሲከፍሉ ፈረንሳውያን 88 000  ሌሎች የውጭ ሀገር ዜጎች ደግሞ 120 000 ብር በዓመት ይከፍላሉ። 
ከ 50 ዓመታት በፊት የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ከነበሩት መካከል በአዲስ አበባ የዶይቸ ቬለ ወኪል ጌታቸው ተድላ ኃልለ ጊዮርጊስ ይገኝበታል። «በወቅቱ የነበረው ትምህርት ሁሉን አቀፍ ነበር» ይላል። 
የሊሴ ትምህርት ቤት ጊዜዋን  እንደሌሎቹ ድሮ እያለች ሳይሆን ዛሬ ላይ ሆና መናገር የምትችለው አናያ ሙሉጌታ ናት ። እሷ እንደገለፀችልን በአሁኑ ወቅት ወደ ፈረንሳይ ሄደው ነፃ ትምህርት የሚያገኙት እጅግ በጣም ጥሩ ነጥብ የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ብቻ ናቸው። አናያ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ትምህርት ቤቷንም ታደንቃለች። « ሊሴ የተማረ ማንኛውም ተማሪ ጥሩ ቦታ ላይ ነው የደረሰው» ትላለች ።ይህም ወጣቷን ያበረታታታል። 


ዮፍታሄ የድሮ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውን ለማግኘት ከቦስተን ነው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ባለፈው ሳምንት የተጓዙት።  ከ 25 ዓመት ገደማ በፊት ነው ትምህርታቸውን ከሊሴ ትምህርት ቤት ያጠናቀቁት። « ለ13 ዓመት አብሮ ማሳለፍ ማለት ወንድ እና እህት ሆኖ ማደግ እንደማለት ነው»  ስለዚህ ግንኙነቱ እንደቤተሰብ የሚቀጥል እንደሆነ ይናገራሉ።
የሊሴ ተማሪዎች ትውስታቸውን ለመለዋወጥ ወይም እንደ አሁኑ የቀድሞ መምህራኖቻቸውን ለማመስገን ጭምር ይሰባሰቡ እንጂ የሊሴ ተማሪዎች  ገና ከድሮ ጀምሮ ይገናኙበት የነበረ ትልቅ ማህበርም እንዳለ የዶይቸ ቬለ ባልደረባችን ጌታቸው ገልፆልናል። 
ከድረ ገፅ ባገኘነው መረጃ መሠረት በዓለም ዙሪያ 460 የሊሴ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ከነዚህም አንዱ ለሆነው የሊሴ ገብረ ማሪያም ትምህርት ቤት የፈረንሳይ መንግሥት በየዓመቱ 4 ሚሊዮን ዮሮ ያወጣል። 

ልደት አበበ 

Audios and videos on the topic