1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ማዕከላት የማስገባት ሥራ ሊጀመር ነው

ረቡዕ፣ ኅዳር 11 2017

በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች በአራት ወራት ውስጥ ትጥቅ በማስረከብ ወደ ማዕከላት ሊገቡ ነው ተባለ። በዚህ ሳምንት በሚደረገው የመጀመርያው ዙር የቀድሞ ተዋጊዎችን ከነበሩበት የዉጊያ ዕዝ የማላቀቅና የመበተን ሥራ መቀሌ ውስጥ የፊታችን ቅዳሜ የሚደረግ ሲሆን የ320 ተዋጊዎች የትጥቅ ርክክብ ይደረጋል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4nD6m
የተሀድሶ ኮሚሽን
320 የቀድሞ ተዋጊዎች በዚህ ሳምንት የትጥቅ ርክክብ ያደርጋሉምስል Solomon Muchie/DW

የቀድሞ ታጣቂዎችን የመበተን ሥራ ሊጀመር ነው

 

320 የቀድሞ ተዋጊዎች በዚህ ሳምንት የትጥቅ ርክክብ ያደርጋሉ

ተጠሪነቱ ለመከላከያ ሚኒስቴር የሆነው ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ትጥቅ የፈቱ፣ የሰላም ስምምነት የፈረሙ ድርጅቶች ውስጥ አባል የነበሩ እና በስድስት ክልሎች የሚገኙ 371, 971 የቀድሞ ተዋጊዎችን በ18 ወራት ውስጥ ትጥቅ በማስፈታት ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን፤ በዚህም በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች፣ በዕድሜ የገፉ እና ጤነኛ የሆኑ 75 ሺህ ተዋጊዎችን በአራት ወራት ውስጥ በትኖ ወደ ማዕከል እንደሚያስገባ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ዛሬ ለጋዜጠኞች ገልፀዋል። 

«ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ እስከ ነገ ሙሉ ቀን ድረስ በመከላከያ ሚኒስቴር ተወካዮች የሚመራ የትጥቅ ርክክብ - የመጀመርያዎቹ 320 ወደ ካምፕ የሚገቡ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስረከብ፣ የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል።»

ሦስት የቀድሞ ተዋጊዎችን ማቆያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል

በትግራይ ክልል በመቀሌ፣ ዳጋ ሐሙስ እና አድዋ ከተሞች የመከላከያ ካምፕየነበሩ ማዕከላት የቀድሞ ተዋጊዎችን ለማስልጠን እና ለማቆያነት ተመርጠዋል ተብሏል። የተቋሙ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዲየር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው እንዳሉት በትግራይ ክልል የትጥቅ ርክክብ ከአንድ ዓመት በፊት መጀመሩንና በዚህም የሜካናይዝድ፣ የአየር ኃይል እና የቡድን ማሣሪያዎች ርክክብ መደረጉን ገልፀዋል። በዚህ ወቅት የሚደረገውን የመሣሪያ ርክክብም የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴ አባላት ይታዘባሉ።

«አሁን የሚገባው 75 ሺህ ትጥቅ ማስረከብ ግዴታ ነው። 75 ሺህ ቁጥር ግን ሁሉም ሰው ትጥቅ ያለው ነው፣ ትጥቅ ያስረክባል ማለት አይደለም» ብለዋል። 

የተሀድሶ ኮሚሽን
በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች በአራት ወራት ውስጥ ትጥቅ በማስረከብ ወደ ማዕከላት ሊገቡ ነው ተብሏል።ምስል Solomon Muchie/DW

ለመሆኑ ይህ ሥራ ለምን በዚህ ደረጃ ዘገየ?

በፕሪቶሪያ ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት ይህ ሥራ ለሁለት ዓመታት የዘገየው ለምንድን ነው በሚል ዶቼ ቬለ ላቀረበው ጥያቄ የሥራ ኃላፊው ምላሽ ሰጥተዋል። «ለምን ዘገየ እስካሁን? በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው ሐብት ነው። አሁን ባለው በሀገራችን አቅም ሊሸፈን የሚችል አይደለም። ሁለተኛው መተማመን ያስፈልጋል»። 

የሥራ ዘመኑ እንዲራዘም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቡን ያስታወቀው ብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የሕወሓት መከፋፈል ለዚህኛው ሥራ እንቅፋት እንደማይሆን ይልቁንም የኤርትራ ሠራዊት አሁንም በክልሉ ውስጥ መሆኑ ችግር መሆኑን ሌላኛው ምክትል ኮሚሽነር ተስፋለም ይህደጎ በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

«በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በተለይ ደግሜ በትግራይ ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት ያልወጣ አለ። ይህ በፌዴራል መንግሥት የሚታይ ይሆናል»።

አጠቃላይ አሉ የተባሉት የቀድሞ ተዋጊዎች ምን ያህል ናቸው?

በስድስት ክልሎች 371, 971 የቀድሞ ተዋጊዎች መኖራቸውን ያስታወቀዉ የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ከዚህ ውስጥ 274 ሺህ 800 ያህሉ በትግራይ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን እና ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልገው 761, 490 ዶላር ከተገኘ በአራት ዓመታት ውስጥ ሁሉም እንዲበተኑ እንደሚደረግ ገልጿል።

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች ሁለት ዓመት ገደማ በተካሄደው ጦርነት በውል ቁጥራቸው ያልተገለፀ ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን ሲያጡ፤ 29  ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የኢኮኖሚ ውድመት መድረሱ፣ ያንንም ለመልሶ ለመገንባት 19.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስቀድሞ ተገልጾ ነበር።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ