የቀድሞዋ የሕወሃት ታጋይ የማዕከላዊ እስርቤት ሰቆቃ | ኢትዮጵያ | DW | 16.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የቀድሞዋ የሕወሃት ታጋይ የማዕከላዊ እስርቤት ሰቆቃ

ጥር 21፣2006 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በድንገት ትፈለጊያለሽ ተብለው ተጠሩ :: " ከኤርትራ የደህንነት ሰራተኞች ጋር ግንኙነት አለሽ " የሚልም የሃሰት ክስ መስርተው አካላዊ እና የሥነ ልቦና ጥቃት ፈጸሙብኝ ይላሉ ወይዘሮ አዜብ :: ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ በየማረሚያ ቤቶቹ ተንቀሳቅሰው የሕግ ታራሚዎችን እንዲጎበኙ ጠይቀዋል ::

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:51

የቀድሞዋ ታጋይ የማዕከላዊ ሰቆቃ

የደርግ ሥርዓትን በመጣል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት መስዋዕትነት ብንከፍልም ግፍ እና ጭቆናው ግን አሁንም አልቀረም ሲሉ በስለላ እና በሽብር ወንጀል ክስ ተፈርዶባቸው በቅርቡ ከእስር የተፈቱ አንዲት የቀድሞ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ታጋይ እና የትግራይ ፖሊስ ባልደረባ ገለጹ :: ከኤርትራ መንግሥት የደኅንነት ሰራተኞች ጋር ግንኙነት አለሽ በሚል ተጠርጥረው ከ 4 ዓመታት በፊት የ 7 ዓመት ፍርድ የተበየነባቸው ወይዘሮ አዜብ ተክላይ በተለይ ለዶቼቨለ እንደገለጹት አብሬው ለነጻነት የታገልኩት ኢሕአዲግ በማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ከፍተኛ አካላዊ እና የሥነልቦና ጉዳት የሚያስከትል ሰቆቃ ፈጽሞብኛል ብለዋል:: 

በእኔ ላይ ከፍተኛ ግፍ እና በደል የፈጸመብኝ በደንብ የማላውቀው ደርግ ሳይሆን አብሬው ለሕዝቦች ነጻነት የታገልኩት ድርጅቴ ኢሕአዲግ ነው የሚሉት የቀድሞዋ የሕወሃት ታጋይ እና የትግራይ ፖሊስ ባልደረባ ገና በለጋ ዕድሜያቸው በ 15 ዓመታቸው የ 5ተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው ነበር በፍልሚያ ከተሰዉት ታላቅ እህታቸው ጋር መሳሪያ አንግበው በረሃ ወርደው ትግሉን የተቀላቀሉት :: በ1983 ዓ.ም ኢሕአዲግ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ብሔር ብሔረሰቦችን በሰራዊቱ ውስጥ ለማመጣጠን በሚለው መርሃ-ግብሩ ከሰራዊቱ የተገለሉት የቀድሞዋ ታጋይ ወይዘሮ አዜብ ከ 1986 ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም ትግራይ ክልል አዲግራት ወረዳ በሚገኘው ፖሊስ ጽ/ቤት ውስጥ በረዳት ኢኒስፔክተርነት አገልግለዋል :: ሕይወቴን ለከፍተኛ እንግልት እና ሥቃይ ዳርጎታል ያሉትም ክስተት የተፈጸመው ሙያቸውን ለማሻሻል እዛው ትግራይ ኩዊሃ በሚገኘው የፖሊስ ማሰልጠኛ የመቶ አለቅነት ኮርስ ለመከታተል በተላኩበት ወቅት ነበር :: 


ወይዘሮ አዜብ የክስ ሂደታቸው በፍርድ ቤት በሚታይበት ወቅትም በቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያቤት በኩል የደህንነት መስሪያ ቤት ወደ ኤርትራ የተደዋወሉት የሥልክ መልዕክት መኖር አለመኖሩን አጣርቶ ምንም ማስረጃ ሊያቀርብ አለመቻሉን ገልጸዋል :: በማዕከላዊው ምርመራ ወቅት ሕገ መንግሥታዊ እና የሰብአዊ መብቴ ተጥሶ "ውሻ ነሽ" የሚሉ እና ሌሎችም ክብርን የሚያዋርዱ ስድቦች እና ዘለፋዎች ሲደርሱብኝ ተበሳጭቼ ነበር የሚሉት ወይዘሮ አዜብ ዛሬ አካላዊ ጉዳት እና የማይሽር የሥነ ልቦና ጠባሳ ጥለውብኝ ያለፉት ከፍተኛ ድብደባዎች እና ሰቆቃዎች ያለማቋረጥ ከተፈጸሙብኝ በኋላ ግን ደርግ ሥርዓቱ ተወገደ እንጂ ግፍ አፈና እና ጭቆናው ዛሬም በገሃድ መደገሙን ለማመን ተገደድኩ ብለዋል ::

ያለምንም ማስረጃ በስለላ እና የሽብር ወንጀል ክስ 7 ዓመታት ተፈርዶባቸው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከጋዜጠኛ እና ደራሲ ርዕዮት ዓለሙ ጋር መቆየታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አዜብ እንደ አደገኛ አሸባሪ እንጂ እንደ ሕግ ታራሚ ይቆጠሩ እንዳልነበርም ያስታውሳሉ :: ከትግራይ ድረስ ለመጠየቅ የሚመጡ ዘመዶቻቸው ሳይቀሩ እንዳያገኛቸው በማድረግ ተደጋጋሚ በደል እንደተፈጸመባቸውም ገልጸውልናል::

በሽብር የተከሰሱ ሰዎች በማረሚያ ቤት ሰቆቃ ተፈጸመብን ሲሉ እውነት አይመስለኝም ነበር የሚሉት ወይዘሮ አዜብ በምርመራ ወቅት እሳቸውም በተፈጸመበቸው ድብደባ በእግራቸው በሌላው የሰውነት አካላቸው እንዲሁም በሥነልቦናቸው ላይ ጭምር ከባድ ጉዳት መፈጸሙን በማየታቸው ሃቁን ለመረዳት መቻላቸውን ይናገራሉ:: ሕጻን ልጃቸውን እንኳ ሳይሰናበቱት በድንገት ታፍነው የማዕከላዊ ሥቃይ ሰለባ የሆኑት ወይዘሮ አዜብ በማያውቁት ወንጀል እናታቸውን ጭምሮ 5 ቤተሰብ ከሚያስተዳድሩበት ሙያቸው መፈናቀላቸውም አሳዝኖኛል ብለዋል:: በአሁኑ ወቅት ሌሎችም በርካቶች በወንጀል ምርመራ በሚፈጸምባቸው ድብደባ እንዳይወልዱ የተደረጉ እና ልዩ ልዩ አሰቃቂ ጉዳት የተፈጸምባቸው ቤተሰባቸው በችግር የተበተነ እና ልጆቻቸውም ጎዳና የወድቁ መኖራቸውን አውግተውናል:: በቅርቡ በይቅርታ የተፈቱት የቀድሞዋ የሕወሃት ታጋይ ኢሕአዲግ ከእንዲህ ዓይነቱ ሥህተቱ የማይታረም ከሆነ ሕዝቡ እንደ ቀድሞ በመሳሪያም ባይሆን በሃሳብ እንደሚታገለው አስታውቀዋል :: በኢትዮጵያ ቀሪ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ብሎም በየማረሚያ ቤቶቹ ተንቀሳቅሰው የሕግ ታራሚዎችንም እንዲጎበኙ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ጥሪ አስተላልፈዋል :: በእስር ቆይታቸው ወቅት የሞራል ድጋፍ ለሰጧቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖችም አመስግነዋል ::

እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic