የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ነጋሶ ጊዳዳ ቀብር | ኢትዮጵያ | DW | 05.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ነጋሶ ጊዳዳ ቀብር

ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ፍራንክፈርት-ጀርመን ዉስጥ በሕክምና ሲረዱ ያረፉት የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ነጋሶ ጊዳዳ ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ ተቀበሩ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:37

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ቀብር ተፈፀመ

የዶክተር ነጋሶ አስክሬን ዛሬ ከቀትር በኋላ ጴጥሮስ ወ ጳዉሎስ መካነ-ቀብር ከማረፉ በፊት በመኖሪያ ቤታቸዉና ሚሊኒንየም በተባለዉ አዳራሽ ሽኝት ተደርጎለታል።በአዳራሹ በነበረዉ ሥርዓት ፕሬዝደንት ሳሕለወርቅ ዘዉዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን፣ ሌሎች ባለስልጣናት፣ ባለቤታቸዉና ዘመድ ወዳጆቻቸዉ ተገኝተዋል።በሽኝቱ ላይ ንግግር ካደረጉት አንዱ የትምሕርት ቤት ጓደኛቸዉና ኋላ የፖለቲካ ጓዳቸዉ አቶ አስራት ጣሴ ጨካኝና አምባገነን ያሏቸዉ የኢትዮጵያ የቀድሞ ገዢዎች ነጋሶን ሞቱንም ርካሽ ለማድረግ ሞክረዉ ነበር ብለዋል።

እንደ አዳራሹ ሁሉ በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት፣የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸዉና ወዳጆቻቸዉ ተገኝተዋል።ዶክተር ነጋሶ ከ1983 ጀምሮ ሁለት መስሪያ ቤቶችን በሚንስትርነት፣ከ1987 እስከ 1994 ድረስ ደግሞ ኢትዮጵያን በፕሬዝደንትነት መርተዋል።አንጋፋዉ ፖለቲከኛ ከገዢዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መሪዎች ጋር በሐሳብ ተለይተዉ የመንግሥት ሥልጣን ከለቀቁ በኋላም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ፣ የተቃዋሚዉ የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበር ሆነዉ ሰርተዋል።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለእዉቁ ፖለቲከኛ ክብር ነገን ብሔራዊ የሐዘን ቀን አዉጇል።ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ባልትዳርና የ3 ልጆች አባት ነበሩ።76 ዓመታቸዉ ነበር።

ነጋሽ መሐመድ

ሰለሞን ሙጬ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic